Monday, December 4, 2023

ኢትዮጵያና ሱዳንን ለማደራደር የተጀመሩ ጥረቶችና በሁለቱ አገሮች መካከል የቀጠለው መካረር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ ወደምታነሳበት የኢትዮጵያ ድንበር የጦር ኃይሏን በጥቅምት ወር 2013 ዓም መጨረሻ አካባቢ በማሰማራት የድንበር አካባቢዎቹን ከተቆጣጠረች በኋላበሁለቱ ወዳጅ አገሮች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል። 

በአፍሪካ አገሮች መካከል እንዲህ ዓይነት ወታደራዊ ፍጥጫዎች ሲከሰቱ ፈጣን የመፍትሔ ዕርምጃ እምብዛም ሲወስድ የማይታወቀው የአፍሪካ ኅብረትበኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተከሰተውን የፖለቲካ ውጥረትና ወታደራዊ ፍጥጫ በውይይት ለመቀልበስ ከሚታወቅበት በተለየ ፈጣን የሚባል እንቅስቃሴ ጀምሯል። 

በቅርቡ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን የተመረጡት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐመት፣ አማካሪያቸው የሆኑትን መሐመድ አል ሀሰን ዋድ ላባት ልዩ መልዕክተኛቸው አድርገው ባለፈው ሳምንት ዓርብ ወደ ካርቱም ልከዋቸዋል። 

‹‹የአፍሪካ ኅብረትን አስቸኳይ መልዕክት ለሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት ለማድረስ አማካሪዬ የሆኑት መሐመድ አል ሀሰን ዛሬ ካርቱም ገብተዋል፤›› ሲሉ የኅብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ባለፈው ዓርብ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

በካርቱም የአንድ ቀን ቆይታ ያደረጉት የኅብረቱ ኮሚሽነር አማካሪና ልዩ መልዕክተኛ ከሱዳን የሽግግር መንግሥት ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጋር ተገናኝተው የኅብረቱን አስቸኳይ የተባለ መልዕክት ያደረሱ ሲሆን፣ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጋርም ተገናኝተው በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ስለተፈጠረው የድንበር ውዝግብ ተነጋግረዋል። 

ከድንበር ውዝግቡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸውን አለመግባባት ለመፍታት የጀመሩት ድርድር መቀጠል እንዳለበት መመካከራቸውን፣ የሱዳን መንግሥት የዜና አውታሮች ገልጸዋል።

ከአፍሪካ ኅብረት በተጨማሪ በርካታ የዓለም አገሮች መልዕክተኞቻቸውን ወደ ሱዳን እየላኩ የኢትዮ ሱዳን የድንበር ውዝግብ ወዳልተፈለገ መካረር ሳይሸጋገር በሰላም መፈታት እንዳለበት መምከራቸውን፣ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሱዳን ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆነውን አምባሳደሯን ወደ አገሯ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የጠራች ሲሆን፣ የተለያዩ የዓለም አገሮች መልዕክተኞቻቸውን ወደ ሱዳን በመላክ ላይ የሚገኙት ከዚሁ የሱዳን መንግሥት ዕርምጃ ጋር በተገናኘ ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ። 

ሰኞ የካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ብቻ የአውሮፓ ኅብረት ዲፕሎማትን ጨምሮ የፈረንሣይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የስፔን፣ የኔዘርላንድስና የስዊድን ዲፕሎማቶች ከሱዳን የሽግግር መንግሥት ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄነራል አብደልፈታል አል ቡርሃን ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈጠረው ውዝግብ በሰላም መፈታት እንዳለበትና ይህም በአስቸኳይ መከናወን እንዳለበት ተወያይተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሁለቱ አገሮች ልዩነታቸውን በአስቸኳይ በውይይት እንዲፈቱ ላቀረቡት ጥሪ ሁለቱም አገሮች በጎ ምላሽ የሰጡ ቢሆንምሀለቱ አገሮች ወደ ወይይት የሚገቡበት ሁኔታ ግን አሁንም አልታወቀም። 

ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የተፈጠረውን የጋራ ድንበር ውዝግብ በጦር ኃይል ለመፍታት መሞከር ትልቅ ስህተት መሆኑን የገለጸች ሲሆንአሁንም ቢሆን የድንበሩን ጉዳይ በቀላሉና በፍጥነት በውይይት መፍታት እንደሚቻልና ብቸኛው ፍላጎቷም ይህ እንደሆነ እያሳወቀች ነው፡፡

ነገር ግን ችግሩን በውይይት ለመፍታት የሚቻለው በመጀመሪያ ሱዳን በኃይል ከተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች ጦሯን ስታስወጣ ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች። 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ማክሰኞ የካቲት 16 ቀን 2013 .ም. በሰጡት መግለጫ፣ ይህንኑ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም በድጋሚ አጠናክረውታል።

ቃል አቀባዩ በሰጡት መግለጫ ከአፍሪካ ኅብረትና ከደቡብ ሱዳን በተጨማሪ፣ ሌሎች አገሮችም ኢትዮጵያና ሱዳንን ለማደራደር እየጠየቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአገሮቹን ሥጋትና ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ያሳዩትን ፍላጎት ኢትዮጵያ በእጅጉ እንደምታከብር የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ‹‹ነገር ግን ኢትዮጵያ ወደ ድርድር የምትሄደው ሱዳን ከጥቅምት 27 ቀን 2012 .ም. በፊት ወደ ነበረችበት ቦታ ስትመለስ ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እያቀረበች ላለው የሰላም ጥሪ የሱዳን መንግሥት የሰላም ፍላጎት ባያሳይም፣ ኢትዮጵያ ግን አሁንም ጉዳዩ በሰላም ይፈታል ብላ እንደምታምን ተናግረዋል።

‹‹ችግሩ ቀደም ሲል በነበረው የሁለቱ አገሮች የድንበር ጉዳይ ኮሚሽን የሚፈታበት መንገድ እንዲፈታ ፍላጎት አለን፤›› ያሉት ቃል አቀባዩ ዲና  (አምባሳደር)፣ ‹‹ወደ ነበራችሁበት ተመለሱና ወዲያውኑ እንነጋገራለን፣ በደቂቃዎች ውስጥም ድርድር እንጀምራለን ብለናቸዋል፤›› ሲሉ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥሪ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ ሱዳን የድንበር ውዝግብ ላለፉት 100 ዓመታት የነበረና የቆየ መሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩሱዳን በመቶ ዓመት ጊዜ ውስጥ አድርጋው የማታውቀውን በኢትዮጵያ ላይ ልትፈጽም የቻለችው ከሱዳን ሕዝብና መንግሥት በመነጨ ፍላጎት ነው ብላ ኢትዮጵያ እንደማታምን በድጋሚ ገልጸዋል። 

ሱዳን ወደዚህ ድርጊት ተገዳ የገባችው በሦስተኛ አገር ግፊት እንደሆነ ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት ባወጣችው ይፋዊ መግለጫ ያስታወቀች ሲሆንበስም ያልጠቀሰችውን የውጭ ኃይል ፍላጎት ተሸክሞኢትዮጵያ ላይ ጦር እንዲመዘዝ የወሰኑትም የሱዳን የጦር ኃይል አመራሮች እንደሆኑ ገልጻለች። 

ለዚህ የኢትዮጵያ ክስ የሱዳን መንግሥት ከበድ ያለ ምላሽ የሚሰጥ መግለጫ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወጥቷል።  በመግለጫውም የኢትዮ ሱዳን ድንበር በየትኛውም ጊዜ የውዝግብ ምንጭ ሆኖ እንደማያወቅ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ላይ የአመራር ለውጥ ካደረገ ወዲህ ችግሮች መከሰት እንደ ጀመሩ በመግለጽ፣ ጉዳዩ የአትዮጵያ መንግሥት አቋም ሳይሆን ከግለሰብ ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ አድርጎ ለመሣል ሞክሯል።

የሱዳን መንግሥት ጦሩን ያሰማራው በራሱ የግዛት ወሰን ውስጥ እንደሆነ የሚገልጸው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫየሱዳን ጦር የተሰማራባቸው አካባቢዎችም የሱዳን ግዛት አካል መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያውቀውና የሚቀበለው እንደሆነ ገልጿል።

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም የሱዳን ግዛት መሆናቸውን ባረጋገጠባቸው ቦታዎች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የይገባኛል የሚል አቋም ከያዘ፣ ማንኛውንም አኅጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ የሕግ አማራጮችን ተጠቅሞ መጠየቅ ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን የሱዳን መንግሥት ከሉዓላዊ የግዛት ወሰኑ አንድም ስንዝር አይለቅም፤›› ብሏል።

በዚሁ የሱዳን መግለጫ ላይ ከኢትዮ ሱዳን የድንበር ውዝግብ ወጣ ያለ ጉዳይ ተነስቷል፡፡ ይኸውም፣ ‹‹ሱዳን የኢትዮጵያ መንግሥትንም ሆነ በሱዳን ግዛት የተሰማራውን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር አታምንም፤›› የሚል ነው።

ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ማክሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የሱዳን መንግሥት በሱዳን የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል የሚጠረጥር መግለጫ ማውጣቱን በተመለከተ ተጠይቀው ነበር። 

‹‹የኢትዮጵያን ሰላም አስከባሪ መተናኮል ለሱዳን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆንባታልይህ የሱዳን ተግባር ለሰላም ከቆሙ ኃይሎች ጋር የሚያጋጭ ነው፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -