በጌታቸው ይልማ ደበላ
በኢትዮ ቴሌኮም የፕራይቬታይዜሽን እንቅስቃሴ ላይ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችና በግል ኩባንያዎች ላይ እየታየ ያለው ውክቢያ የመንግሥትን ጥንቃቄ የሚሻ ሆኖ ይታያል። ይህንን እንድንል ያስገደደን የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን አገሮች ዳይሬክተር የሆኑት ዑስማን ዲዮኔ የኢትዮ ቴሌኮምን በተወሰነ ደረጃ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ እየተደረገ ያለውን የጨረታ እንቅስቃሴ በተመለከተ አመለካከታቸውን እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 11 ቀን 2021 በዓለም ባንክ ድረ ገጽ ላይ ተስፋና ሥጋታቸውን ጨምረው የገለጹበትን ጽሑፍ ካየን በኋላ ነው።
ሐሳባቸው ብዙ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ ቢሆንም፣ በቀላሉ ለማቅረብ ተሞክሯል። የዳይሬክተሩ የመጀመርያ ሥጋት መንግሥት የኢንተርኔት የገንዘብ ልውውጥ አገልግሎትን የኢትዮጵያ ዜጎችና ኩባንያዎች ብቻ እንዲያከናውኑት መከለሉን ተችተዋል። ቀጥለውም አዲስ የሚገቡት የግል ቴሌኮም ኩባንያዎች የመንግሥት በሆነው የኢትዮ ቴሌኮም መሠረተ ልማት መጠቀም እንዳለባቸው የተቀመጠው ግዴታ አልተዋጠላቸውም። በሦስተኛው ደረጃ መንግሥት የመጫወቻውን ሜዳ ከማመቻቸት በዘለለ ለኢትዮ ቴሌኮም የተለየ ዕገዛ የማድረግ ዝንባሌ ከታየበት በፕራይቬታይዜሽኑ ላይ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ሥጋታቸውን አጋርተዋል። በጽሑፋቸው የዓለም ባንክ የጨረታ ሒደቱን ከማገዝ ባለፈ እ.ኤ.አ. በሴብቴምበር 2019 የተቋቋመውን የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣንን ለማጠናከር የቴክኒካዊ ድጋፍ እየሰጡ እንዳለም ጠቁመዋል።
በመቀጠል የኢትዮጵያ መንግሥት በምን መልኩ ጉዳዩን ቢይዘው ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች የሚያገኘውን ጥቅም ሳያጣ መጫወት እንዳለበት እናያለን። በቅድሚያ መረዳት የሚያስፈልገው የዓለም ባንክ የሚሰጠው የቴክኒክ ድጋፍ ጠቃሚ ቢሆንም፣ እነርሱ የሚሉትን በሙሉ መተግበር አገርን ለአደጋ መዳረግ ስለሚሆን እየተደረገ ባለው የጨረታ ሒደትና በጠቅላላ የቴሌኮም ፕራይቬታይዜሽን ጉዳይ ላይ መንግሥት ምን ማድረግ እንዳለበት በጥንቃቄ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል።
ከዚህ አንፃር በአሁኑ ጊዜ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ በተለይም የኢንተርኔት አብዮት በአገሮች ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ወታደራዊ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን ከግምት ያስገባ ዕርምጃ መከተል ይገባል። በሳይበር ጥቃት የፋይናንስ፣ ወታደራዊና የምርምር ምስጢሮችን መመንተፍ ተችሏል። እንደ ፌስቡክ ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎችን በመጠቀምም የመራጮችን ድምፅ በማዛነፍ እውነተኛ ምርጫ በአገሮች እንዳይደረግ በሩሲያና በጣሊያን ተከስቶ ሥጋትን ወልዷል። ይህም ሆኖ የዓለም የቴሌኮም ግስጋሴ ሰው አልባ ተሽከርካሪዎችንና ሙሉ የፋብሪካ ማሽነሪዎችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ፈጣን ዕድገት አሳይቷል። በአንፃሩ የእኛ የቴሌኮም አገልግሎት የሽፋኑ ዝቅተኛነት እንዳለ ሆኖ እጅግ ደካማ በመሆኑ ተገልጋዩ ከኤቲኤም ወይም ከባንክ ገንዘብ ለማውጣት፣ ታክስ ለመክፈል ሲፈልግ “ሲስተም የለም” መባል የተለመደ ሆኗል። በመሆኑም የኢትዮ ቴሌኮምን አገልግሎት በማሻሻልና የአገር ደኅንነትን በማረጋገጥ መካከል ሚዛንን ማስጠበቅ አስፈላጊ ነው።
ለዚህም አገልግሎቱን ለማሻሻል የዓለም ባንክ ከሚመክረው ኢትዮ ቴሌኮምን ወደግል ከማዞር ይልቅ፣ መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን ማየት ይኖርበታል። ከነዚህ አማራጮች ውስጥ አንዱ መንግሥት የቁጥጥር ኃይሉን እንደያዘ (መሠረተ ልማቱን እንደያዘ) የቴሌኮም ፈቃድ ወስደው የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሰጡ ተወዳዳሪዎችን ማስገባቱ ብልህ ውሳኔ ነው።
ነገር ግን የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ፍላጎት በዚህ ዕርምጃ ብቻ አይረካም። ሙሉ በሙሉ ወደ ግል እንዲዞር መወትወታቸው የሚጠበቅ ነው። ይህንን ለማምለጥ መንግሥት ማድረግ ያለበት የተወሰነውን የኢትዮ ቴሌኮም አክሲዮን ለኢትዮጵያውያን መሸጥ ነው። የሚፈልገውን የኢንቨስትመንት መጠን በመለየት በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ገንዘብና በውጭ ምንዛሪ በመጠን የተገደበ አክሲዮን የሚገዙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይቻላል። በቅርቡ የተቋቋመው የካፒታል ገበያንም በኢትዮ ቴሌኮም ኢንቨስትመንት ማስጀመር ለሌሎችም ኩባንያዎች አክሲዮናቸውን በዚህ መልክ እንዲሸጡ መደላድል ይፈጥራል።
የብሔራዊ ደኅንነትን ከማስጠበቅ ባለፈ የግሉ ዘርፍ የማይደፍራቸውን ራቅ ያሉ ገጠራማ አካባቢዎች የቴሌኮም ተጠቃሚ ለማድረግ ኢትዮ ቴሌኮም በመንግሥት እጅ መሆኑ ሌላው ጠቀሜታው ይሆናል። ሌላው ኢትዮ ቴሌኮም በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆንበትን የለውጥ ሒደት ማስጀመር ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም። የቴሌኮምን ፈጣን የዕድገት ግስጋሴን ያማከለ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን (5Gን ጨምሮ) ማከናወን ግድ ይሆንበታል። በቴክኒክና በአመራር ጥበብ ጠንካራ በሆነ የሰው ኃይል ራሱን ማደራጀት ይጠበቅበታል።
ሌላው ጥንቃቄ የሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣንን በማጠናከር ረገድ ብዙ መሥራት ይኖርበታል። ወደ ቴሌኮም አገልግሎት የሚገቡት ዓለም አቀፍ የግል ኩባንያዎች ከፍተኛ የሰውም ሆነ የሀብት አቅም ያላቸው በመሆኑ እነርሱን ለመቆጣጠርና አግባብ ባለው የንግድ ሥርዓት እንዲሠሩ ለማድረግ ረጅም ዝግጅት ይፈልጋል። የኒዮርክን ኮንቬንሽን እንደ ተቀበለ አገር ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎቹ ጋር ለሚፈጠረው የግልግል ዳኘኝነት ሁለንተናዊ ዝግጅት ማድረግ ካልተቻለ፣ በቀጣይ ብዙ ጉዳቶች በይገባኛል ጥያቄዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ ልትከፍል ትችላለች።
በመሆኑም በአገሪቱ የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ እስኪፈጠር፣ የጨረታውን ሒደቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚደረገው ምርጫ እስከሚጠናቀቅና አዲስ መንግሥት እስኪቋቋም የማዘግየት ሥልትን መከተል በግርግር ከሚፈጠር የውል ዝንፈቶች ለማምለጥ ይረዳል።
በመጨረሻም ከዳይሬክተሩ ሐተታ መረዳት እንደሚቻለው በጨረታ ሒደቱ ላይ ባንኩ የሚሰጠውን የቴክኒክ ድጋፍ ተጠቅሞ ጥልቅ መረጃ እንዳለው ነው። ይሁንና የባንኩ ሚና በጣም የተወሰነ ሆኖ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን የጨረታ ሒደቱን በከፍተኛ ምስጢር መያዝ ይገባዋል። የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ከተቋቋመ አጭር ጊዜ በመሆኑ የዓለም አቀፍ ጨረታ ግዥ ልምድ እጥረት የሚገመት ሲሆን፣ ከመንግሥት ተቋማት የግዥ ልምድ ያላቸውን ከፍተኛ ባለሙያዎችን በመጠቀም የጥንቃቄ አካሄድን እንዲመርጥ እንመክራለን።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡