በዮናታን መንክር ካሳ
ከአንድ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ የናኘው ብስራት፣ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የራሷን ሳተላይት ወደ ህዋ ልታመጥቅ ነው የሚል ነበር፡፡ ይኸው ዜና፣ የዚያን ሰሞን የሚዲያው ሁሉ ዋነኛ ርዕስ ሆኖ ነበር። ‹‹ETRSS-1›› ተብላ የተሰየመችው ሳተላይት ከቻይና የምትመጥቅበትም ዕለት በጉጉት ሲጠበቅ ቆይቶ፣ የማምጠቁ ሥርዓት በቀጥታ ከቻይና ሲተላለፍ፣ እንጦጦ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ኦብዘርቫተሪ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት መርሐ ግብሩ ሲከናወን እዚያው በቦታው ነበርኩ፡፡
በእውነቱ፣ ዛሬ ላይ ሆነን ኢትዮጵያ ይህቺን ሳተላይት ከዓለም ሁሉ መጨረሻ ላይ ሆና በሰው ቴክኖሎጂ፣ በሰው ምድር፣ በሰው ማምጠቂያ እያደረገችም ይህን ያህል ግርምት የሆነብንን ክስተት፣ ከዘጠኝ አሠርታት ግድም በፊት በኢትዮጵያ ምድር ከጥቂት አገሮች ቀጥለን በአቪዬሽን መስክ ከነበርንበት ግስጋሴ ጋር ብናነጻጽረው፣ ምን ያህል ለብዙ ዘመናት እንዳንቀላፋን ወይም ወደ ኋላ እንደሄድን እንረዳለን፡፡
ከ85 ዓመት በፊት ከብዙ የዓለም አገሮች በአቪዬሽን መስክ መቅደም ብቻ ሳይሆን ‹‹ፀሐይ›› የተሰኘች አውሮፕላን በአገራችን መግጠም ሳይሆን መሥራት ችለን ለነበርን ኢትዮጵያውያን፣ ዛሬ በዚያው መስክ በሌላ አገር ቴክኖሎጂና ስሪት፣ በሌላ አገር ምድር ላይ በዕርዳታ ስለላክናት ሳተላይት የምንደነቅ መሆናችን የሚያስቆጭ መሆኑን የምንገነዘብበትን የከፍታ ታሪካችንን በማያወላዳ መንገድ የታሪክ ሰነዶችን መርምሮ ያቀረበልን መጽሐፍ ከሰሞኑ ታትሞ ለሕዝብ ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ፣ ብዙ ታሪካዊ ሰነዶችን ዋቢ ያደረገውና በካፕቴን ዘለዓለም አንዳርጌ የተጻፈውን ‹‹ፀሐይ›› የተሰኘውን መጽሐፍ በአካዴሚው ፕሬስ በኩል አሳትሞ ለንባብ አብቅቶታል፡፡ መጽሐፉ በ12 ምዕራፎች ተዋቅሮ በ370 ገጾች የተሰናዳ ሲሆን፣ 170 ፎቶግራፎችን አካትቷል። ጸሐፊው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሦስት አሠርታት በአብራሪነት ቆይታቸው፣ የሥራ መስካቸው ሊያስገኝላቸው የሚችለውን ሁሉ ዕድሎች ተጠቅመው በየአገሮቹ ዞረው ከቤተ መዛግብትና መጻሕፍት ታሪካዊ ሰነዶችን በማፈላለግ መርምረዋል፣ አመሳክረዋል፣ የሚመለከታቸውን የታሪኩ ባለቤቶችና በሕይወት ያሉ የቅርብ ዕማኞች በቃለ መጠይቅ ብዙ መረጃዎችን አሰባስበዋል፡፡
ጸሐፊው ስለ ኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ ለዓመታት በትጋት የሠሩት ምርምር እስካሁን ብዙ ባልተጻፈለት አስደናቂው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ፣ እስከ ዛሬ ከተጻፉት ሁሉ በላቀ ደረጃ የተደራጀ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ምሁራን ተገምግሞ የተረጋገጠ ሁነቶችን የያዘ መጽሐፍ አበርክተውልናል፡፡
ኢትዮጵያ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ በነበሯት ተራማጅና ለሥልጣኔ ጥልቅ ፍላጎት ባሏቸው መሪዎቿ አማካይነት፣ በዘመኑ በኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ መስኮች በጥሩ ግስጋሴ ላይ ከነበሩት በዋነኛነት የአውሮፓ አገሮች ጋር የዲፕሎማሲያዊና የኢኮኖሚ ግንኙነት በመፍጠር፣ የዘመኑን ግኝቶችና ሥሪቶች ወደ አገራቸው እንዲመጣ ያደርጉት የነበረው ጥረት ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተጀመረ ነው፡፡ ይኸው ጥረት በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ቀጥሎ፣ ኢትዮጵያ በዘመኑ ለዓለም ሕዝብ ሁሉ አዲስም፣ ድንቅም፣ ብርቅም፣ ውድም የነበረውን አይሮፕላን ወደ አገራቸው እንዲገባ ያደረጉት ጥረት ወደር የሌለው የዲፕሎማሲና ግላዊ የተግባቦት ችሎታቸውን ይመሰክራል፡፡ ወቅቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን ያልረጋበት፣ አፄ ምኒልክ ካረፉ በኋላ በመኳንንቱና በመሳፍንቱ መካከል የነበረው የሥልጣን ሽኩቻ ያየለበት እንደመሆኑም መጠን አልጋ ወራሹ ባላቸው ውስን ሥልጣንም ቢሆን፣ ቅንጦት የሚመስለውን የአውሮፕላን መምጣት ጉዳይ ቀዳሚ ጉዳያቸው አድርገው የተጉበትን መንገድ ስናስብ ዛሬ ላይ፣ ባልተቋረጠ የታሪክ ሰንሰለት በዘመኑ የገዘፈውን የኢትዮጵያ አየር መንገድና በወርቃማ ታሪኩ የሚታወሰውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል የቆሙበትን የፀና መሠረት አጉልቶ ያሳየናል፡፡
መጽሐፉ፣ በሰነድም ጭምር አባሪ አድርጎ ባቀረባቸው የታሪክ ሁነቶች ከምንረዳቸው አንኳር ቁም ነገሮች አንዱ፣ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ አገሮች በተለይም ከፈረንሣይ፣ ከጀርመንና ከስዊድን ጋር የነበራትን የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ትብብር እንዲሁም አገራችን በወቅቱ እንደ አንድ ሉዓላዊና የተከበረች አገር የነበራትን ተደማጭነትና ተፈላጊነት ያሳየናል፡፡ በዚህ ከፍታ ወቅት መላው አፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካና የእስያ ሕዝቦች በአስከፊ የቅኝ አገዛዝ ሥር የራሳቸው ነፃ መንግሥት እንኳን ያልነበራቸው መሆኑን ማስታወስ ይገባል፡፡
መጽሐፉ የኢትዮጵያን አቪዬሽን ታሪክ ከመሠረቱ አንስቶ በሰፊው ካስነበበን በኋላ፣ ስያሜውን የተዋሳትና ‹‹ፀሐይ›› ተብላ የተሰየመችውን አውሮፕላን ታሪክ ይተርክልናል፡፡ በሚያስገርም ግጥምጥሞሽ ይህችኑ አውሮፕላን ጣሊያን ድረስ ሄዶ የጎበኘበትን ግላዊ ማስታወሻውንም ያስነብበናል፡፡
ኢትዮጵያ እንዲህ እንደ ዛሬው ዓለም ሁሉ በሺ የሚቆጠሩ አነስተኛ ሳተላይቶችን ካስወነጨፈ በኋላ፣ በሌላ አገር ቴክኖሎጂና በሌላ አገር ለተወነጨፈች አነስተኛ የመሬት ቅኝት ፎቶግራፍ አንሺ ሳተላይት፣ የነበረውን መደመምና መደነቅ በታሪክ 85 ዓመት ወደ ኋላ ሄዶ ‹‹ፀሐይ›› የምትባል አውሮፕላን እዚሁ ጃንሜዳ ላይ በጀርመናዊው መሐንዲስ ቬበርና ኢትዮጵያውያን መካኒኮች አጋዥነት ተሠርታ፣ የተሳካ በረራ ያደረገች አውሮፕላን የሠራች አገር መሆኗንና በዓለማችን በረራ ለነጮች ብቻ እንደሆነ በሚታሰብበት ዘመን፣ የራሷን ጥቁር አብራሪዎች ማሠልጠኗን ላሰበ ሁነቱ ብዙ ተቃርኖና አግራሞትን ይጭራል፡፡ ይህ ታሪክ፣ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ምን ስንሠራ ነበር? ምንስ ወደ ኋላ አስቀረን? የሚሉ የቁጭት ጥያቄዎችን እንድንጠይቅ የሚያስገድደንን ዕምቅ ሐሳብ ለአንባቢያን ትቶልናል፡፡
አንኳር የታሪክ ሁነቶች
በኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ሒደት፣ በተለይም አፄ ምኒልክ ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ ከገነቡና፣ የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ፍላጎትና ሙከራ በዓድዋ ጦርነት ድል አድርገው ኢትዮጵያ የምትባል በማዕከላዊ መንግሥት የምትተዳደር አገር ከመሠረቱ በኋላ፣ ብዙም ሳይቆይ ሕይወታቸው በማለፉ፣ ወትሮውኑም በመሳፍንትና መኳንንቱ የውስጥ ለውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ያልረጋው ዙፋን፣ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንግሥናቸውን አደላድለው ኢትዮጵያን ማስተዳደር በቻሉበት ፈታኝ የታሪክ ሒደት ውስጥ፣ ትናንሽ አውሮፕላን በማስመጣትና ጥቂት ኢትዮጵያውያን አብራሪዎችና መካኒኮችን በማሠልጠን የተጀመረው የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ጅማሮ ያበረከተው አስተዋጽኦና ያሳረፈው አሻራ በታሪክ ከፍተኛ ምዕራፎችን የያዘ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ የታሪክን አቅጣጫ ሁሉ የቀየሩ ክስተቶችንም ያመጣ ሆኖ አልፏል፡፡
በዚህ ረገድ፣ በጥቅምት 1922 ዓ.ም. የአልጋ ወራሹ ጦር በወቅቱ በጌምድርን ያስተዳድሩ ከነበሩትና የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ባልና የእቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅ ከነበሩት ከራስ ጉግሳ ወሌ ጋር የነበረው የአንቺም ጦርነት ላይ፣ ለመጀመርያ ጊዜ አውሮፕላን ለስለላና ለጦርነት የዋለበትና በዚሁ ውጤትም የራስ ጉግሳ ወሌ ጦር በቀላሉ የተፈታበት (የተሸነፈበት)፣ በደሴ የተከሰተውና የመጀመርያው በኢትዮጵያ የተመዘገበ የአውሮፕላን አደጋ የአፄ ኃይለ ሥላሴ አጎት ሕይወት ማለፉ፣ አልጋ ወራሽ ተፈሪ፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ተብለው የዘውድ ሥርዓታቸው ሲከበር የመጀመርያዎቹ ኢትዮጵያውያን አብራሪዎች ከመምህሮቻቸውና ሌሎች የውጭ አገር ዜጎች ጋር በመሆን የሚያስደንቅ ትርዒት ማሳየታቸው፣ ጣሊያን አገራችንን በወረረችበት ወቅት፣ አውሮፕላኖቹ ለቅኝት እንዲሁም መሣሪያ፣ መድኃኒት፣ ቁስለኞችና ታላላቅ የጦር መሪዎችን በማመላለስ የሰጡትን ድጋፍ ስናስብ፣ የአገራችን አቪዬሽን ገና ከጅምሩ ወሳኝ በሆኑ የታሪክ ምዕራፎች ላይ የነበረውን ጉልህ ድርሻና አስተዋጽኦ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ይህ መጽሐፍ፣ እነዚህን ታሪካዊ ሁነቶችና ከዚህ ቀደም ያልተሰሙና ያልተጻፉ ወሳኝ የታሪክ ሀብታችንን በዝርዝር ያስነብበናል፡፡
የተዘነጉት ባለውለታዎቻችን
በዚህ አጋጣሚ መጽሐፉ በታሪክ ከሚያስታውሰን ዓበይት ቁም ነገሮች አንዱ፣ በዚያን ወቅት የመጀመርያውን አውሮፕላን በአገራችን ሰማይ አብርሮ በአገራችን ምድር ካሳረፈው ፈረንሣዊው ሙሴ አንድሬ ማዬ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን አብራሪዎቻችንን በማሠልጠን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአገራቸው መንግሥት ጋር የአውሮፕላን ግዢ ውል እንዲፈጽም ያደረጉ አብራሪዎች፣ በተለይም ጣሊያን አገራችንን በወረረችበት ጊዜ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በሚችሉት ሁሉ ሙያዊ ድጋፋቸውን ያደረጉልንን ኢትዮጵያውያንና እንደ ስዊድናዊው ቮን ሮዘን ያሉ የውጭ አገር ዜጎችና አብራሪዎችን የማይረሳ ውለታ ነው፡፡ ጸሐፊውም ሊያስታውሱ እንደሞከሩት እነዚህ በደግና በክፉ ዘመን ለአገራችን ባለውለታ የነበሩ ሰዎች በአቪዬሽን ተቋሞቻችን የሚገባቸውን ማስታወሻ ቢደረግላቸው፣ የአገራችንን የአመስጋኝነት ዕሴት ይጠብቃል ብዬ አምናለሁ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ወቅቱ ይጠይቅ የነበረውን ከፍተኛ ትጋት፣ ቆራጥነትና፣ መስዋዕትነትም ጭምር በሚያስደንቅ ብቃት ተወጥተው የአገራችንን የአቪዬሽን ጅማሬ ዕውን ያደረጉት የአገራችን ልጆች በስም እንኳን እስከማይታወሱ ድረስ ያለምንም ማስታወሻ መቅረታቸው ያስቆጫል፡፡ በዚህ ረገድ ሚሽካ ባቢቼፍ፣ አስፋው አሊ፣ ባህሩ ካባ፣ ተስፋ ሚካኤል፣ ደምሴና ሥዩም ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
በፆታ ያልተገደበ ቀዳሚነት
ዛሬም ድረስ በዓለም ላይ ስሙ የገነነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከበርካታ ስኬቶቹ መካከል በኩራት የሚነገርለት የሴቶች አብራሪዎች ጉዳይ ጀማሪ የነበሩትን የመጀመርያዋ አፍሪካዊት አብራሪ ወ/ሮ ሙሉ እመቤት እምሩ በድፍረት ከወንድ ጓደኞቻቸው ጋር የአውሮፕላን ልምምድ ያደረጉበትን ታሪክ አብራርቶ የነገረን ይህ መጽሐፍ፣ ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት ለፆታ እኩልነት ክብርም ዕድልም የሰጠች አገር እንደሆነች ያሳየናል፡፡ ዛሬ፣ አገራችን በታሪኳ ኋላ ቀርና ጨቋኝ እንደሆነች፣ ለዚህም የምዕራባውያን አስተሳሰብ መድኃኒቷ እንደሆነ ሊሰብኩን በሚፈልጉ የውጭ አገር የታሪክ ጸሐፊዎችና አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ይህን መሰሉ ታሪካችን ስለ አገራችን ትክክለኛውን ታሪክ እንድናውቅ ብቻ ሳይሆን አገር በቀል ከሆነው ባህላችን፣ ዕውቀታችንና ልምዳችን ብዙ እንድንማር ዕድል ይሰጠናል፡፡
እንደማጠቃለያ
ፀሐይ በቅርብ ጊዜ ከተጻፉ መጻሕፍት ሁሉ በላቀ፣ የታሪክ ሰነዶችን በመመርመርና ሚዛናዊ ትንታኔ በመስጠት፣ በተለይም በቴክኖሎጂው መስክ አገራችን ከአንድ ምዕት ዓመት በፊት ጀምሮ፣ በዘርፉ ካደጉት ጥቂት አገሮች ጋር ተስተካክላ ለመሄድና ከዚያም አልፎ በቴክኖሎጂ ለመመንደግ የነበራትን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የተመሰከረ አቅምም መለስ ብለን እንድናይ ያደርገናል፡፡ እንደ ጥሩ አንባቢና ዜጋ፣ ይህን መጽሐፍ አንብበን ስንጨርስ፣ በሦስት የጊዜ ዐውዶች ላይ ሆነን ራሳችንን መጠየቅና ማንቃት የምንችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ባለፈው ታሪካችን እንድንደነቅ፣ አሁን ልንደርስበት እየቻልን ባልደረስንበት እየተቆጨን፣ ከትናንቱ ታሪካችንና ከዛሬው ቁጭታችን ደግሞ ነገ ለላቀ ሥራ የምንነሳሳበትን ስሜት ያጭራል፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡