የአዲስ አበባ ጎዳናዎችና የእግረኛ መንገዶች በጣም መጨናነቅ የጀመሩት ከ2000 ዓ.ም. በኋላ ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ የከተማዋ መንገዶች እንዲህ ባልሰፉበት፣ ሕንፃዎችም እንዳሁኑ ባልበዙበት ጊዜ የእግረኛ መንገዶች እንዳሁኑ የሕገወጥም ሆነ ሕጋዊ ንግድ መናኸሪያም አልነበሩም፡፡ አልፎ አልፎ ጉሊት እንዲሁም በየሱቃቸው በር ‹‹እዚህ ጋ አለን›› የማለት ያህል ልብስ አልያም ዕቃ የሚያንጠለጥሉ ሱቆችም በርካታ አልነበሩም፡፡
ዛሬ ይህ ተቀይሯል፡፡ አብዛኞቹ የከተማዋ የእግረኛ መንገዶች ዓላማቸውን ስተው ለንግድ ማስፈጸሚያ ውለዋል፡፡ ተጨናንቀዋል፡፡ በየመንገድ ዳር ተከራይተው የሚሠሩ የንግድ ሱቆች የሚደረድሯቸው ዕቃዎች እንዲሁም በሸራ ተወጥረው በየመንደሩና በየአውራ ጎዳና የከተሙ መነገጃዎች፣ ሕገወጥ የሚባሉት የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ከከተሜው፣ ቁጥር መጨመር ጋር ተደምረው ዛሬ ለአዲስ አበባ አሉታዊ ገጽታ አላብሰዋታል፡፡
የሥራ ዕድል መፈጠሩ ለከተማዋ ሰላምም ሆነ የዜጎችን ኑሮ ለመቀየር ወሳኝ ቢሆንም፣ ከከተማዋ ያልተጣጣመና ለኑሮም፣ ለደኅንነትም ሆነ ለውበት ሥጋት የሆነ አሠራር ‹‹ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስ አበባ እናደርጋታለን›› ብሎ ዓላማ አስቀምጦ ለተነሳ የመንግሥት አካል የሚመጥንም አይደለም፡፡
በሸራ ተወጥረውና የእግረኛ መንገድ ዘግተው የሚሠሩ ሕጋዊ የሚባሉባት፣ ሱቅ ተከራይተው ዕቃቸውን ለማሳየት የእግረኛውን መንገድ የዘጉት ደግሞ ሕገወጥ ተብለው በደንብ ማስከበር ዕቃቸው የሚወሰድበት ሲቀዘቅዝ የሚሠሩ ሞቅ ሲል የሚሳደዱ በሺዎች የሚቆጠሩ የጎዳና ነጋዴዎች በተለይ በከተማዋ ዋና የትራንስፖርትና የእግረኛ መንገዶች ሥፍራዎች ላይ የሚነግዱባት አዲስ አበባ፣ ይህንን ሥርዓት በማስያዝ በኩል ተሸንፋለች፡፡
አንዴ የሰንበት ገበያ፣ አንዴ ራሳቸውን ሲያቋቁሙ እናደራጃለን፣ አንዴ ሥራ እንፈጥራለን እየተባለም፣ ከተማዋ ኋላ ለመመለስ የሚያስቸግራትን የቤት ሥራ እያከማቸችም ትገኛለች፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ‹‹ለጊዜው›› የሚላቸውና ወረዳ ድረስ በተዘረጋ መዋቅር በርካቶች በየመንገድ ዳር የተሠራ የሸራ ሱቅ ባለቤት ሆነዋል፡፡ በዚያው ልክ ክፍት ቦታዎች፣ የመንገድ ዳርቻዎች፣ አደባባይ አካባቢ ያሉ መንገዶች፣ የቀለበት መንገድ መሸጋገሪያ ደረጃዎች ሥር እና በዳርና ዳር፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች አጥሮች፣ የተቋማትና የሌሎችም ሥፍራዎች አጥሮች ለዚሁ ተግባር ውለዋል፡፡ አረንጓዴነትና ውበት ሳይሆን፣ ብርቱካናማና ሰማያዊ ላስቲኮች የከተማ ጎዳናዎችና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ጭምር መገለጫ እየሆኑ ነው፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ለተመልካቹም ፀያፍ ለከተማዋም አሉታዊ ገጽታን ላላበሰው የመንገድ ላይ መፀዳዳት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሸራ በተወጠሩባቸውም ሆነ የጎዳና ንግድ በሚካሄዱባቸው ሥፍራዎች መፀዳጃ የለም፡፡ ሙሉ ቀንም ዋሉ ግማሽ ቀን፣ አመሻሽ ላይም ሆነ ጠዋት የሚሠሩት ውኃ ሸንት ሲመጣ የሚፀዳዱት እዚያው አቅራቢያ ካለ መንገድ ነው፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ያሠራቸው መፀዳጃ ቤቶች መኖራቸው አስተዋጽኦ ቢያደርግም፣ ይህ በሁሉም ቦታ ተደራሽ አይደለም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ጉርድ የላስቲክ ዕቃ በማስቀመጥ የሚያስጠቅሙ አሉ፡፡ ሆኖም አብዛኛው ሥፍራ የተሟላ መፀዳጃ ስለሌለው በአካባቢው ከሚገኝ ሥፍራ ለመፀዳዳት ይገደዳሉ፡፡ ለዚህ የመገናኛ፣ የሜክሲኮ፣ የፒያሳ፣ የመርካቶና የተለያዩ ሥፍራዎች ጥጋ ጥግ ምስክሮች ናቸው፡፡
በሸራ በተወጠረ ዳስ ውስጥ ጫማ፣ የእጅ ሰዓትና ሎሎች ቁሳቁሶችን እንዲሁም ምግብ የሚሸጡና ራሰቸውን አልያም ከነቤተሰባቸው የሚያስተዳድሩም በርካታ ናቸው፡፡ በዚህ በተወጠረው ሸራ የሚነግዱት ሸራው የተወጠረበት በእግረኛ መንገድ ከመሆኑ አንፃር ሕጋዊ ናቸው? አይደሉም? የሚለው አንዱ ጥያቄ ቢሆንም፣ እንደ ሌሎች በፌስታል አንጠልጥለውና መንገድ ዘርግተው እንደሚሸጡት ተሳዳጅ አይደሉም፡፡
የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ሕጋዊ የሆኑትም ሆነ ያልሆኑት በኢትዮጵያ ሕጋዊ ተብለው፣ ሰነድ ለጥፈውና በሺዎች በሚቆጠር ብር ቤት ተከራይተው ከሚሠሩት ነጋዴዎች ባልተናነሰ ገበያ ውስጥ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ነገር ግን ሥርዓት ተበጅቶለት መልካም ግብይት ለማከናወን ችግር መሆኑ አልቀረም፡፡
በከተማዋ ዋና ጎዳናዎችና የእግረኛ መንገዶች ሳይቀር እየተከናወነ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ሥርዓት ስላልተዘረጋለት ለትራፊክ አደጋዎች መንስዔ ከመሆንና የእግረኛ መንገድ መጨናነቅ ከመፈጠር አልቀረም፡፡ የዚህ የመንገድ ዳር ንግድ ችግር የከተማ ውበት እንዲቀንስም ምክንያት ሆኗል፡፡ እንዲያውም ከተማዋ ትርምስምሷ የወጣችም ጭምር ካስመሰሏት የመንገድ ዳር ንግድ ሥርዓት ይጠቀሳል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ፒያሳ ሸራ ወጥረው ጫማ በመሸጥ ኑሯቸውን የሚገፉት አቶ አብዲሽኩር ድለንጎ አንዱ ናቸው፡፡ በአካባቢው ላይ ሸራ ወጥረው የንግድ ሥራ በመሥራት ኑሯቸውን ካደረጉ አሥራ አምስት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ አቶ አብዲሽኩር የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ልጆቻቸውን ለማሳደግና ኑሮን ለማሸነፍ ሌት ተቀን ደፋ ቀና በማለት ሥራቸውን እንደሚሠሩ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ሥራ መተዳደር ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ የንግድ ፈቃድ አውጥተው ሕጋዊ የሆነ አሠራር ለመሥራት በአካባቢው ወደሚገኘው ወረዳ ቢመላለሱም፣ ፈቃድ ሳያገኙ መቅረታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ሕግ አስከባሪዎች መጥተው የያዙትን ሸቀጣ ሸቀጥ እንደሚወስዱባቸው ገልጸዋል፡፡
የያዙትን ዕቃ ሳይሸጡ ሲቀሩ የልጆቻቸውን የዕለት ጉርስ ለመሙላት እንደሚቸገሩ የሚናገሩት አቶ አብዲሽኩር፣ በተለይም የቤት ኪራይ ሲደርስ የሚይዙትን የሚጨብጡትን እንደሚያጡ ይገልጻሉ፡፡
መንግሥት በንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን በመደገፍና ለንግድ የተመቻቸ ቦታ በማዘጋጀት የሚሠራ ቢሆን ኖሮ፣ እንደዚህ ዓይነት ሕገወጥ የንግድ አሠራሮችን በመጠኑም ቢሆን መቅረፍ እንደሚችልም ያክላሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በመንግሥት በኩል ያለው አሠራር በኑሮ ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ቢሆንም፣ ከሕጋዊ ነጋዴዎች ይበልጥ ሕገወጥ ሥራን እንዲከተሉ መንገድ መክፈቱን አስረድተዋል፡፡
ኑሮን ለማሸነፍና ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከመንገድ ዳር እየሠሩ ካሉትም ሌላኛው የመንገድ ዳር የንግድ ሥራው አመቺ ስላልሆነና ለአደጋ ስለሚያጋልጥም ወደፊት ትክክለኛ የቦታ ይዞታ አግኝተው መሥራት እንደሚፈለጉ ነግረውናል፡፡ በንግድ ሥርዓት ወጥ የሆነ አሠራር ኖሯቸው የንግድ ሥራቸውን መሥራት፣ ከዚያም አልፎ ቤተሰቦቻቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ እንደሚፈልጉም አክለዋል፡፡
አቶ ሰለሞን ኢብራሂም ከእህታቸው ጋር በመሆን ፒያሳ አካባቢ መንገድ ዳር ላይ ሸራ ወጥረው መሸጥ ከጀመሩ አራት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ለመንግሥት ግብር በመክፈል ጫማ፣ የልጆች አሻንጉሊት፣ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመሸጥ ሕጋዊ የሆነ አሠራር እየሠሩ ቢሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ ከቦታው ላይ ተነሱ ሕጋዊ አይደላችሁም እንደሚባሉ ተናግረዋል፡፡ እህታቸውም በዚህ ሥራ ከተሰማራች አሥር ዓመታትን እንዳስቆጠረችና ቤተሰቦቿን የምታስተዳድረውም በዚሁ ሥራ መሆኑን አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ተቀያሪ ቦታ ቢያመቻችና ሥራቸውን እንዲሠሩ ቢያደርግ፣ አብዛኛው ነጋዴዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በኑሯቸውም ሆነ በሥራቸው ለውጥ የሚያመጡ መሆኑንና በዚሁ ሥርዓት ከቀጠለ ግን የሕገወጥ የንግድ ሥራ በአገሪቱ ላይ ሊስፋፋ እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
መንግሥት በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች በማጤን እንዲሁም የተለያዩ መፍትሔዎችን በማበጀት በዘርፉ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት አለበት ብለዋል፡፡
በፒያሳ አካባቢ ከጓደኞቻቸው ጋር ሸራ ወጥረው ኑሯቸውን ይኖሩ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አብዲሳ ጉልቤ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት ጀብሎ በመሸጥ ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ ይገኛሉ፡፡ ለበርካታ ዓመታትም ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በሸራ በተወጠረች ዳስ ውስጥ አብረው እንደሚኖሩ የገለጹት አቶ አብዲሳ፣ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የዕለት ጉርስ ለማግኘት እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡
የንግድ ፈቃድ ለማውጣትና ሕጋዊ አሠራር ለመከተል አካባቢው ላይ በሚገኘው ወረዳ በተደጋጋሚ ሄደው ቢጠይቁም፣ ጥያቄያቸው መልስ እንዳላገኘ አቶ አብዲሳ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር ሌባና ፖሊስ በመጫወት ጊዜያቸውን ያለምንም ሥራ የሚያሳልፉበት ወቅት እንዳለም አብራርተዋል፡፡
ወረዳው የነጋዴውን ችግር ፈትቶ መልስ ለመመለስ እንደማይፈለግ፣ ይህም በነጋዴዎች ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት በወረዳዎችና በፈቃድ አውጪዎች በኩል ትልቅ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ አብዛኛው ነጋዴዎች ፈተና ውስጥ መግባታቸውንና መንግሥት በንግድ ዘርፍ ላይ ትኩረት በመስጠትና የቦታ ይዞታዎችን በማመቻቸት ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበትም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
የአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ንግድ ተሳዳጅና የማይሳደድ የሚሳተፍበት መሆኑ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ የከተማው ንግድ ቢሮም ሆነ እስከ ወረዳ ያሉት የሚያቁትና በየሠፈሩና በየእግረኛ መንገዱ የተወጠረ ሸራ በሺዎች ለሚቆጠሩ የከተማዋ ሥራ አጦች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሚል የተሰጠ ነው፡፡
እነዚህ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ አቅም ሲያገኙ በማደራጀትና ብድር እንዲያገኙ በማመቻቸት የሚነሱ ናቸው ተብሎ ከዚህ ቀደምም ተነግሯል፡፡ ሆኖም በከተማ አስተዳደሩ ባሉ መዋቅሮች ተመርጠው ሳይሆን ለራሳቸው ሥራ ፈጥረው በጎዳና የሚነግዱትን አስተዳደሩ ያስተናገደበትና ችግሩን የቀረፈበት መንገድ ባለመኖሩ አሁንም የከተማዋ ችግር ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ሁለቱም ለከተማ ውበት እንዲሁም የእግረኛ መንገድ ከመዝጋት አንፃር ያላቸው አሉታዊ አስተዋጽኦ ተቀራራቢ ቢሆንም፣ የደንብ አስከባሪ እጅ የሚያርፈው ሸራ ባልወጠሩት ላይ ነው፡፡
በከተማ አስተዳደሩ መዋቅር ሥር አሠራር ተዘርግቶ፣ በየአውራ ጎዳናው የእግረኛ መንገዶች፣ በየመንደሩ፣ በኮንዶሚኒየም አጥሮች ሸራ በመወጠር የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውና በራሳቸው ጎዳና ላይ የሚሸጡ እስከ መቼ ይዘልቃሉ? ከተማዋን ውብ ከማድረግ አንፃር ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች ጋር አብረው ይሄዳሉ ወይ? በሚሉና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ መልስ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ስልክ በመደወልና ቢሮ ድረስ በመሄድ ብንጠይቅም መልስ ማግኘት አልቻልንም፡፡