Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አናንቀላፋም!

ሰላም! ሰላም! አንዱ በቀደም ዕለት እየተንደረደረ መጥቶ፣ ‹‹እኛ አሁን የጀግኖቹ አያቶቻችን ልጆች እንባላለን?›› ሲለኝ ግራ ተጋብቼ፣ ‹‹ታዲያ ምን ልንባልሯል?›› ስለው፣ ‹‹እኛማ የእነሱ ልጆች ለመባል ብዙ የሚቀረን ይመስለኛል…›› ብሎኝ መልስ ሳይጠብቅ ሄደ። እሱ እንደዚያ ሆኖ የጠየቀኝን እንደ ተራ ነገር ከማየቴ በፊት ማሰላሰል ያዝኩ። ‹‹በአንድ ዕርምጃ የተጀመረ የሺሕ ኪሎ ሜትሮች ሩጫ ለምን በፍጥነት አላለቀም ባይባልም፣ መለስ ቀለስ እያልን ታሪካችንን ስናስተውል ብዙ የሚቀረን ነገር እንዳለ መገመት አያዳግትም…›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ እሱ ዘወትር እንደሚናገረው ታሪካችን በደማቅ ገድሎች የደመቀ ለመሆኑ ሁነኛው ማሳያ ታላቁ የዓድዋ ድል ነው፡፡ ይህ ታላቅ አኩሪ ገድል በተፈጸመባት ታሪካዊት አገር ውስጥ በመቅኖ ቢስ ሐሳቦች የተጠመዱ ጉዶች መኖራቸውም ይደንቀዋል፡፡ ዛሬም የአያቶቻቸውን የጀግንነት ታሪክ የሚያደምቁ ጀግኖች ቢኖሩም፣ መቅኖ ቢሶቹ ድምፃቸው ከጣሪያ በላይ መሰማቱ ያበሳጨዋል፡፡ እኔ መቼም የአገር ጉዳይ ሲነሳ ውስጤን ስለሚነዝረኝ የምሁሩን ወዳጄን ንግግር መስማት ያረካኛል፡፡ በተለይ የዓድዋ ጀግኖች ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል መነቃቃት የፈጠሩትን ተጋድሎ ሲነግረኝ፣ ራሴንና የዘመኔን ሰው እየገመገምኩ ብዙ እከፋለሁ፡፡ እኛ በዚያ ልዕልና ላይ ለመገኘት ብዙ እንደሚቀረን ሳስብም ይነደኛል፡፡ ፈጣሪ የባረካቸው የዘመናችን ጀግኖች ባይኖሩ ኖሮ ምን ይውጠን ነበር እያልኩም እብሰለሰላለሁ፡፡ አይደለም እንዴ!

ከዚህ ወጣ ብለን የወትሮውን ኑሮአችንን በተመለከተ እየተነጋገርን ድንግት ፖለቲካው ውስጥ ጥልቅ ስል፣ ‹‹አይ አንበርብር ማደግ ተስኖት ልምሻ የያዘው ፖለቲካ ውስጥ ገብተህ ልፈትፍት ብትል ማን ፈቅዶልህ… ከበፊት ጀምሮ እንዲህና እንዲያ እንላለን እንጂ ወሳኝ እንዳልሆንን የታወቀ ነው…›› የሚለኝ ነገረኛው ጓዴ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። እሱ እንኳን እንዲህፈረሱም ያው ሜዳውም ያውብዬ መንገድ ሰጥቼው ቀርቶ ሰርስሮ መግባት ይችልበታል። በዚህ መሀል ደግሞ ሐሳቤን የማካፍላቸው ሲገኙ፣ ‹‹እንደሚያወሩት አውርተህ፣ እንደሚያስቡት አስበህ፣ እንደሚስቁት ስቀህ ነገር የማታሳልፈው ለምን ይሆን…›› እያሉኝ ግራ እጋባለሁ፡፡ እንዲህ ተያይዘን እየተደነባበርን ስንጓዝ እኮ ዓለምን የሚዞራት የለውጥ ባቡር ጥሎን ከነፈ፡፡ እውነቴን እኮ ነው፡፡ ቆም ብሎ ማሰብ፣ መተራረም፣ በሐሳብ መነቃቀፍና መተማመን መቻል እንደ እንግዴ ልጅ አልወጣልን ብሎ 2013 ላያችን ላይ ተጋምሶ ቢያልቅብን ምን ይባላል? አዛውንቱን ባሻዬን ጠጋ ብዬ፣ ‹‹ምነው ይኼን ያህል እያደር ባሰብን?›› ስላቸው፣ ‹‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም…›› ብለው ወሽመጤን ቆረጡት። አወይ ቢጤ ማጣት!

ነገሩን ከላይ ከላይ እንደ ስልባቦት አንስቼ ጨዋታ መጀመሬ ጥንስሱ የት መሰላችሁ? ያው የፈረደበት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ነዋ። ጥንት የጋርዮሽ ሥርዓት ሲጀምር እርስ በርስ መጠቃቃት ቆሞ ሰላም ብቻ ይፈልግ የነበረው የሰው ልጅ፣ አሁን በደረሰበት ዘመን የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ፣ የነፃነት፣ የኔትወርክ፣ የመብራት፣ የውኃ፣ የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የመጠለያ… ችግር እርስ በርሱ አጠማመደው የሚሉ አሉ፡፡ ሰፋ አድርገው ቢያዩት ደግሞ ዓለም በብጥብጥ እየታመሰች ነው፡፡ እንዴት ያለ ነገር ነውአሁን እዚህ ላይአይ የተነሱበትን አለማወቅ?› አትሉም። ምክንያቱስ ካላችሁ ለተከበረው የሰው ልጅ ሌላ ሌላው ቀርቶ፣ ፍትሕና ነፃነት ተፈጥሮውን የሚመጥኑ ስለሆኑ ነው መልሴ። ዳሩ ቆይ ጠብቀኝ የሚሉት ዛቻ በዝቶ ተቸገርን። እነዚያ ጥጉን ይዘው እነዚህን መቦጨቅ፣ እነዚህም እነዚያን በሐሜት መዘንጠል፡፡ ይኼ መገዳደር ተራራውን ሜዳ፣ ሜዳውን ሸለቆ ያደርገዋል ብሎ ማሰብ ገደለን። በአንድ ጽንፍ እያየን እንዳላየን ሆነን የምናልፈው ከንቃት ጉድለት ለሚመጣው የአስተሳሰብና የአመለካከት ወለምታ፣ ጥቂቶች በሌላ ጽንፍ በቻሉት አቅም ከራሳቸው ነጥቀው ለሌሎች የሚቀምሙት መድኃኒት አልሠራ ብሏል። ምን ሠርቶ አትሉም!

ይህ እንግዲህ በአጭሩዲማንድ ኤንድ ሰፕላይአልተመጣጠነም ማለት ነው (እንግሊዝኛዬ እንዴት ነው? ምንም ደላላ ብሆን ፀሐይ የሞቃቸውን ቃላት እንኳን እኔ አዋፍት እያወቋቸው መጥተዋል)፡፡ ‹‹ለዚህ እኮ ነው ከዳር ቆሞ ማሽሟጠጥና ጠጋ ብሎ ለጥቅም ማጨብጨብ የበዛው…›› የሚሉኝ በዚያ ማራኪ አንደበታቸው አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው። አፈር ልብላላቸውና፡፡ መቼም ትልቅ ሰው ትልቅ ነው። ግን የሚያሳዝናችሁ ትልቅ ሰው ለመሆን ከሚመኘው ይልቅ፣ በአቋራጭ ባለሀብት ሆኖ ግዙፍ ሕንፃ ለመገንባት የሚጓጓው እየበዛ የኩረጃ ትምህርት ቤቶች ተጨናንቀዋል። ወረቀት ይዞ በአቋራጭ ለመክበር፡፡ ታዲያ በዚህ ዓይነት በረከታችን እንደ ዳቦ በአጭር ጊዜ ተጋግሮ ቢበስል ስንካፈል እንዴት ሊሆን ነው? ኧረ ከአሁኑ በደንብ እንጠያየቅ ተው ግዴለም፡፡ አንዱ በቀደም ዕለት፣ ‹‹አንበርብር ድህነት ውስጥ ተዘፍቆ የጀግንነት ገድል ማነብነብ ማን ጠቀመ?›› ሲለኝ አፌን መረረው፡፡ እርግጥ ነው እኔ የማምነው ድህነት የሚወገደው ዘርፎ በመክበር ሳይሆን፣ ላብን አንጠፍጥፎ ወይም ዕውቀትን እስከ መጨረሻው በመጠቀም ስኬታማነት በመጎናፀፍ ነው፡፡ ያኔ ከትናንቱ ጀግኖች እኩል የሚያስከብር ገድል ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንዲያ ነው!

ዘመናችን ብዙ ፀጋዎች የጎደሉት እየመሰለኝ ስራመድ ችግሩ ዘመን ላይ ሳይሆን እኛ ላይ ይመስለኝ ጀምሯል፡፡ ፀብ ያለሽ በዳቦ የሞላው የዘመኑ ትዕግሥት የለሽ ሰው የማይሆነው ነገር የለም። ወጣት ባልና ሚስት ተጣልተው ኖሮ የገዛ መኖሪያቸውን ሸጠው ሊካፈሉ (ሲገኝ መከራ ሲታጣ መከራ) ደልል ተባልኩ። በፍቅር ጊዜ በትዕግሥትና በጥናት የተሠራውን ባለሦስት ፎቅ መኖሪያ አጣድፌ እንዳሻሽጠው መልዕክት ደረሰኝና ቀልቤን ሳትኩ። በኋላ ለቤቱ ገዥ አግኝቼ ይዤያቸው ቤቱን ለማሳየት ወደ ሥፍራው አቀናሁ። ደንበኛዬ ቤቱን ተዘዋውረው ዓይተው ከጨረሱ በኋላ፣ ‹‹ለመሆኑ ምን ሆኖ ነው ይኼን የመሰለ ቤት በዚህ ዋጋ የሚሸጠው?›› ብለው ስለሻጩ ጠየቁኝ። የሰማሁትን እኔምአሉእያልኩ አጫወትኳቸው። እሳቸውም፣ ‹‹እንደ ራሱ የሚወዳት ሚስት የነበረችው ገበሬ ታሪክ ትዝ አለኝ..›› ብለው ጨዋታ ያዙኝ። ልማዴ ነውና ከሥራ ጎን ለጎን በተረት የታሸ ወሬ ለመለቃቀምእህብዬ መስማቴን ቀጠልኩ። ደግሞ ለመስማት!

‹‹ገበሬው ሚስቱ ድንገት ሳትታመም ሞተችና አረፈች። እሱ ደግሞ መኖር አስጠላው። አንድ ቀን መንገድ ሲሄድኧረ ምን አባቱ! ባይኬድ ምን ሊኮን?’ ይልና ድንጋይ ላይ አረፍ እንዳለ ዋለ። አመሻሽ ላይ የሚያውቀው የመንደሩ ሰው በዚያ መንገድ ወደ ቀዬው ሲያዘግም አገኘው።ምነው ወዳጄ ደክሞህ ነው?’ አለው።የለም! ከእግዜር ተጣልቼ ነውአለው። ወዳጁ ተገርሞእና ከእግዜር ብትጣላ ተቀምጠህ ምን ትፈይዳለህ?’ ብሎ ጠየቀው።ተጉዤስ ምን አደርጋለሁ? መጨረሻዬ የምወዳት ሚስቴ የሌለችበት ቤት መግባት አይደለም ወይ?’ ሲለው ወዳጁ መልሶተቀምጠህስ ምን ትሠራለህ? እግዜር ጨክኖ ቢጨክን ለጅብ አይድርህ?’ ብሎ አሸንፎት እያፅናናው አብረው አዘገሙ ይባላል። የዘመኑ ሰው ትዕግሥት እያጣ የነገን የተሻለ መሆን ማየት ተስኖት ለሌላ ትልቅ ጥፋት ሲፈጥን ይህን ያህል ነው…›› ብለውኝ ቤቱን እንደሚገዙት መወሰናቸውን አሳወቁኝ። የማትሰሙት የለም እኮ ጆሮ ከሰጣችሁ፡፡ ይኼንን ጉዳይ በአገር ተርጉሙት ብላችሁ እኮ እናንተ እኔን ፖለቲከኛ ከማድረግ አትመለሱም፡፡ አይደለም እንዴ!

ያን የመሰለ ቤት መቻቻል በመጥፋቱ ፈርሶ ሲሸጥ በእውነት ያገኘሁትኮሚሽን’ ‘ምን አገባኝ?’ ቢያስብልም አንጀቴ ተላወሰ። የራሴን ጎጆ ብቻ ሳይሆን የአገሬን ነገር ዘወር ብሎ መቃኘት ግድ ሆነብኝ። ፍርኃት ተጋብቶኝ ሥጋት ሲገባኝ ማንጠግቦሽን ጠጋ ብዬ ይኼ ነው፣ ይኼ ነው ሳልል አጋጣሚውን እንደ ቀልድ ነገርኳት። ‹‹ይኼውልህ እንዲህ ነው ይህችን የመሰለችም አገር ቀስ በቀስ የምትፈርሰው…›› ብትለኝ ድንጋጤዬ እንደ ማዞር አድርጎ ስላንገዳገደኝ ደሜን ለማስለካት አቅራቢያዬ የሚገኝክሊኒክጎራ አልኩ። ‹‹ደም ለማስለካት ነበር…›› ብዬ ተራ ያስያዝኳት ነርስ እስክትጠራኝ የጠበቅኩትን ያህል ጊዜ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ይወጣልኝ ነበር ብል ማጋነን አልነበረም። ማጋነን ብርቅ አይደል!

ወዲያ ጥግ ተቀምጦ የሚንቆራጠጥ ታማሚ ትዕግሥቱ አልቆ፣ ‹‹እናንተ ሰው ናችሁ? የገነት መግቢያ በር አሳላፊ ብትሆኑ ምን ልታደርጉን ነበር?›› ይላል። ‹‹ወንድሜ ቀበሌ ወይም ክፍለ ከተማ አይደለም ያለኸው፡፡ አርፈህ ዶክተሩ እስኪጠራህ መጠበቅ ብቻ ነው…›› ይላል በኮምፒዩተር ካርታ የሚጫወት ወጣት የሕክምና ባለሙያ ተብዬ። ‹‹እሺ እኔስ? እኔን እኮ ዶክተር ማየት አይጠበቅበትም…›› አልኩት ሹመት ሰጥቶ በሚለምናቸው ሕዝብ ላይ ደረታቸው የሚያብጥ አገልጋዮቻችንን ባስለመድንበት የልምምጥ ዘዴ። ‹‹ተከተለኝ አንተ…›› አለኝ አፍታ ሳይቆይ። ‹‹አይ አንች አገር!›› ብዬ ብዙ ልብሰለሰል ስል ለደም ግፊት ስፈራ ስኳር ደርቤበት እንዳላርፍ ለራሴ ስላሰብኩ ዝም አልኩ። ሆ…ሆ… ደግሞ ለስኳርቼክ አፕቢቀጥሩኝ የህዳሴው ግድብ ግንባታ አልቆ ለምረቃ አይበቃም? ደም ግፊቴኖርማልእንደሆነ ስሰማ ግን እንዳሻችሁ ብዬ እየተበሳጨሁ ወጥቼ ሄድኩ። አይ የአገልጋይና የተገልጋይ ነገር እያልኩ ነዋ፡፡ ሌላማ ምን ብዬ እበሳጫለሁ? ያውም በምርጫ ዋዜማ!

በሉ እስኪ እንሰነባበት ደግሞ። ባሻዬ አዘውትረው ‹‹ሁሉም በአገር ያምራል!›› ይላሉ። ሁሉም ሲሉ ታዲያ ሁሉም ነው። ብስጭትንም ጨምሮ። የባሻዬን ልጅ የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ሳገኘው ብስጭቴ ደስታ ወልዷል። ‹‹ምነው ዛሬ ተፍነከነክ?›› ብሎ ሲጠይቀኝ መልሴ ‹‹ስለተበሳጨሁ!›› የሚል ነበር። ግር ብሎታል። ‹‹ሰው ተበሳጭቶ እንዴት በእኩል ሰዓት ይደሰታል?›› አለኝ መልሶ። ‹‹በአገር ነዋ! የተበሳጨሁት በአገሬ ላይ ሆኜ ነዋ! ይኼኔ ሰው አገር ቢሆን ኖሮ ገመድ አልገዛም ነበር?›› አልኩት። አንድ ሁለት እያልን ጨዋታችንን አደራነው። ውሎዬን ሰማ፣ ውሎውን አዳመጥኩ። የሁለታችንም ገጠመኝ በአጉል ነገር ተረግዞ ብስጭት ሲወልድ የዋለ ነበር። እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙኃኑ ጠጪ ማለት ይቻላል በእሮሮ ተቃኝቶ ነው የመጣው። አንዳንዱ እንደ ሰደድ እሳት የሚግለበለበው ኑሮ ናላውን አዙሮታል፡፡ ሌላውን ደግሞ የአገሩ ጉዳይ ያሳስበዋል፡፡ ግዴለሾች ደግሞ ዳሌና ባት ላይ ተተክለው ቀርተዋል፡፡ ዓለም እንዲህ ናት!

የግሮሰሪዋ ወግ ግን ቀጥሏል፡፡ አንዳንዴ እኮ ግሮሰሪዋ አገር ትመስለኛለች፡፡ አንዱ የትም ሲንዘላዘል ስላባከነው ሃምሳ ሺሕ ብር ይቆጫል። ሌላው አበድሮ ስለቀለጠበት ብድር ያማርራል። ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ኧረ የውኃ ያለህ? በውኃ ጥም አቃጥለውን ሊገድሉን ነው፣ የት አባታችን እንድረስ?›› ይላል። ‹‹ናፈቀኝ ክርክር! ናፈቀኝ በተለያዩ ሐሳቦች ተፋጭቶ መከራከር!›› የሚለው ደጋግሞ ጂኑን ይጋታል። የባሻዬ ልጅ ዘወር ብሎ ወደ እኔ ሲያፈጥ፣ ‹‹እስኪ ማንን ታያለህ ስለሌላ አገር የሚጮህ?›› አልኩት።ማንንምለማለት ራሱን ነቅንቆ ሲያበቃ፣ ‹‹ሁሉም በአገር ያምራል አቦ! ብስጭትም ቢሆን!›› አለኝ። ይኼን ሲለኝ የሰማ አንድ ሞቅ ያለው፣ ‹‹ታዲያስ! አባት የሞተ እንደሆን. . . እናት የሞተች እንደሆን. . . በአገር ይለቀሳል. . .  አገር የሞተ እንደሆን. . . .›› ብሎ ሳይጨርሰው ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ወዴት ይደረሳል?›› ብሎ ጮኸ። ‹‹አገር አያሳጣ ነው የሚባለው። አለበለዚያማ ወዴት ይደረሳል?›› ሲል አንዱ ሌላው ከአፉ ተቀብሎት፣ ‹‹ነበር! ምን ያደርጋል ታዲያ፣ አንዱ ለአገሩ ሲማስን ሌላው ካላፈርስኩ ይላል፡፡ የሚያፈርስ ያፍርሰውና ጃርት ሁሉ!›› እያለ ሲብከነከን አንዱ ደግሞ፣ ‹‹አይዞህ! አገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል ቢባልም፣ ስንት አንበሶች አሉ መሰለህ! ‹እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው› ሲባል አልሰማህም እንዴ! እኛ ግን አናንቀላፋም!›› ካለ በኋላ፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ‹‹ትልቅ አገር ንዶ መንደሮች መገንባት፣ ቅንድብ እየላጩ ኩል እንደ መቀባት ስለሆነ አናንቀላፋም…›› እያለ ሲቀኝ ግሮሰሪያችን በድንገተኛ ጭብጨባ ተሞላች፡፡ መልካም ሰንበት!     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት