የምርጫ ወቅትን ተከትሎ የመንግሥትም ሆነ ሌሎች አካለት ትኩረት በምርጫው ዙሪያ እንደመሆኑ መጠን የዋጋ ንረቱ አሁን ካለበት ግሽበት በላይ እንዳይባባስ መንግሥት የአጭር ጊዜ መፍትሔዎችን ሊያጤን እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
አገሪቱ በዚህ ወቅት ከሕግ ማስከበርና ያንንም ተከትሎ ለደረሰው የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት፣ እንዲሁም ቀጣናዊ የፖለቲካ ውጥረቶችን በማስተናገድ እንደምትገኝ፣ በቅርቡም አገራዊ ምርጫ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እያደረገች ከመሆኗ አንፃር፣ መንግሥት እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ለመከላከል የአጭር ጊዜ መፍትሄ ማስቀመጥ እንዳለበት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ባለሙያና ተንታኙ አቶ ዋሲሁን በላይ ገልጸዋል፡፡
የምርጫ ወቅት ሲደርስ የመንግሥት ትኩረት አብሮ ወደ ቅስቀሳና ተዛማጅ ጉዳዮች እንደሚሆን የሚገልጹት ተንታኙ፣ ሆኖም አገሪቱ ላይ የዋጋ ንረቱን እንዲቀጥል ሊያደርጉ የሚችሉ የተለያዩ ዕርምጃዎች በመንግሥት እተወሰዱ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህም በዋጋ ንረቱ ላይ የራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡
በምርጫ ወቅት ነጋዴውም በአገሪቱ ውስጥ የሚከናወኑ ጉዳዮችን በአንክሮ ለመመልከት በማለት ኢንቨስት ከማድረግ የመቆጠብ ሁኔታ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ባደጉ አገሮች ጭምር የሚስተዋል ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀው፣ በተለይ በእንደነዚህ ዓይነት ወቅቶች መንግሥት የዋጋ ንረቱን የሚያባበሱ ዕርምጃዎችን ከመውሰድ መቆጠብ ይገባዋል ብለዋል፡፡
ለዋጋ ንረት መባባስ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ሁሌም እየተነሳ ያለ ጉዳይ መሆኑን የሚገልጹት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ መንግሥት ለነዳጅና ከሰላም ማስከበር ጋር የሚያያዙ ሌሎች ግብዓቶችን ለመግዛት በሚል በሚይዘው የዶላር ክምችት ሳቢያ ዜጎች የውጪ ምንዛሪን በቀላሉ ማግኘት ስለማይችሉ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ስለሚቀንሱ በዚያው ልክ የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት እንደሚያጋጥም አስረድተዋል፡፡
መንግሥት በተወሰነ መልኩ የዋጋውን ንረት ለመከላከል ከወራት በፊት ከውጭ በሚገቡ የተወሰኑ ምርቶች ላይ ይጥል የነበረውን ታክስ በማንሳቱ ምክንያት በጊዜያዊነት የተወሰኑ ምርቶች ዋጋ ተረጋግቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዋሲሁን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድጎማና የተደረገው የታክስ ማሻሻያ ይነሳል በሚል የአንዳንድ ምርቶች ዋጋ ከወዲሁ ጭማሪ እየታየበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አንድ ቁስ ላይ የሚደረግ የዋጋ ማሻሻያ ብዙ ቁስ ላይ የመሄድ ዕድሉ ሰፊ ነው ያሉት ባለሙያው፣ ለምሳሌ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት ነዳጅን ሲደጉም እንደቆየ አስታውቀው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ 25.4 ቢሊዮን ብር ለነዳጅ ድጎማ እንዳወጣና ከድጎማው 25 ከመቶ በመነሳቱና ዋጋው በዓለም ዓቀፉ ገበያ በመወሰኑ በአንድ ወር ውስጥ የተለያዩ ክለሳዎች እንዲደረጉ ሆኗል፡፡ ይህም ለወቅታዊው የዋጋ ንረት አንዱ ምክንያት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም በንግድ ባንክ የተደረገው የወለድ ማሻሻያ መሠረታዊ ቁሳቁስን ለማስመጣት ጥሩ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ ሌሎች የወለድ ጭማሪ የተደረገባቸው ነገሮች እንደ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ቁጠባ ወለድ ማሻሻያዎች የራሳቸው የሆነ ጫናን ሲፈጥሩ ይስተዋላል ያሉት ባለሙያው፣ በአጠቃላይ በመንግሥትና መንግሥታዊ ተቋማት እየተወሰዱ ያሉት እንደነዚህ ዓይነት ዕርምጃዎችና ለውጦች በአንድ ጊዜ መጣላቸው በድፍን ኢትዮጵያ የግብይት መበላሸት ሒደት ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ይፈጥራል ሲሉ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ምርጫው እስከሚደረግበት ጊዜ የሚሆን የአጭር ጊዜ መፍትሄ ሊደረግ እንደሚገባ የሚገልጹት አቶ ዋሲሁን፣ አቅርቦት ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግና መሠረታዊ የሚባሉትን ቁሳቁሶች ወደ አገር ውስጥ የሚመጡበትን ብድርና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ዕድሎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ገበያዎችን የመቆጣጠር ሥራ በደንብ ሊሠራ ይገባል ያሉት የኢኮኖሚ ተንታኙ፣ በዚህ ወቅት ምርትን መሸሸግ የተለመደ ጉዳይ እየሆነ በመምጣቱ የገበያ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡