የዛሬ 125 ዓመት የአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶችን አንገት ያስደፋ፣ የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦችን አንገት ደግሞ በኩራት ቀና ያደረገ ታሪክ የተሠራው በጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ወደር የሌለው ተጋድሎ ነበር፡፡ ታላቁ የዓድዋ ድል የአይበገሬነት ፅናትንና የእናት አገር ጥልቅ ፍቅርን ተምሳሌታዊነት ያረጋገጠ የመስዕዋትነት ውጤት ነው፡፡ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ መሪነት ከአራቱም ማዕዘናት እንደ ንብ በመትመም የጣሊያንን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች የታጠቀ የሠለጠነ ሠራዊት አከርካሪውን የሰበረው ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ምንም እንኳ እዚህ ግባ የሚባል ትጥቅ ባይኖረውም ለእናት አገሩ በነበረው ወደር የሌለው ፍቅር አንፀባራቂ ታሪክ ሠርቷል፡፡ ከምንም ነገር በላይ ኢትዮጵያዊነት የሚባለውን ታላቅ የአንድነቱ ማሰሪያ ገመድ በመታጠቅ፣ ውድ ሕይወቱን ሰውቶ ቅኝ ገዥውን ኃይል አንበርክኳል፡፡ ይኼ ህያው ታሪክ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ በመናኘት ኢትዮጵያችንን የነፃነት አብሪ ኮከብ አድርጓታል፡፡ ጀግኖቹ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ከመኖሪያ ቀዬአቸው እስከ አገር አቀፍ ድረስ በወቅቱ በነበረው ሥርዓት ይንገላቱ የነበሩ ቢሆንም እንኳ፣ ከአገር ህልውና በላይ ያስቀደሙት አንዳችም ነገር ባለመኖሩ ለአገራቸው በአንድነት ተሠልፈው አንፀባራቂ ታሪክ ሠርተው አልፈዋል፡፡ ከውስጥ ሽኩቻና ፍልሚያ በላይ ለሆነች ታላቅ አገር በፍቅር መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ታላቁን የዓድዋ ድል ስንዘክር ይህንን ህያውና ጥልቅ የአገር ፍቅር ስሜት መቼም ቢሆን አንረሳውም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የታላቁ ሕዝባችን መገለጫ ስለሆነ፡፡
በታላቁ የዓድዋ ድል በዓል መታሰቢያ ዋዜማ ላይ ሆነን ይህን የኢትዮጵያዊነት ግርማ በተለያዩ መገለጫዎቹ ማውሳት ይገባናል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ክብር ያገኘችው በዓድዋ ድል ምክንያት ነው፡፡ የቀድሞውን ሊግ ኦፍ ኔሽንስም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን፣ እንዲሁም ታዋቂ ዓለም አቀፍ ተቋማትን መሥራች መሆን የቻለችው በዓድዋ ድል ምክንያት ባገኘችው ክብር ነው፡፡ አፍሪካውያንም ሆኑ ሌሎች የአርነት ግንባሮች ኢትዮጵያን አርዓያ አድርገው ሰንደቅ ዓላማዋን የተዋሱት በዓድዋ ድል ምክንያት ነው፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መጀመርና ዕውን መሆን ምክንያት የሆነው የዓድዋ ድል ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ የሆነው የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችው በዓድዋ ድል ምክንያት ነው፡፡ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ጥልቅ ኢትዮጵያዊነት የፈጠረው ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር፣ ኢትዮጵያዊነትን ምን ያህል ትልቅ ዋጋ የተከፈለበት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ጀግናው፣ ጨዋው፣ አስተዋዩና አይበገሬው ሕዝባችን ኢትዮጵያዊነት ሲገነባ የኖረው ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ የአገር ፍቅር ስሜት ነው ኢትዮጵያ አገራችንን ቅኝ ያልተገዛች የነፃነት ተምሳሌት ያደረጋት፡፡ ይህ ተረት ሳይሆን በደም የደመቀ ታሪክ ነው፡፡
የጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን በዓለም ያስተጋባ የጀግንነት ታሪክ ሲዘከር፣ የእዚህ ዘመን ትውልድ ልምድና ትምህርት መቅሰም አለበት፡፡ በተለይ ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፣ በተለያዩ መስኮች የተሠማሩ ዜጎች፣ ወዘተ ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ስላላቸው ዕይታ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ አገር ከምንም ነገር በላይ በመሆኗና ለዚህም ሲባል ውድ ልጆቿ የሕይወትና የአካል መስዕዋትነት ሲከፍሉ መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአስተዋይነትና የጨዋነት ፀጋ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምስክር ነው፡፡ አሁን ባልበሰለ የፖለቲካ አተያይ ምክንያት የሚፈጠሩ ውዝግቦችና ውዥንብሮች አገሪቱን መልህቅ እንደሌላት መርከብ ሲንጧት የምናየው፣ ስክነትና ለአገር ማሰብ በመጥፋቱ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት ታላቁ ምሥል እየጠፋ በመንደርተኝነት መቧደንና መጠፋፋት ውስጥ የተገባው፣ ለሰከነና ጨዋነት ለተላበሰ የፖለቲካ ግንኙነት ዕውቅና በመነፈጉ ነው፡፡ ከአገር በላይ ግላዊና ቡድናዊ ጥቅም እየበለጠ ኢትዮጵያዊነት እንዲደበዝዝ በመደረጉ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በዓለም አደባባይ ያላኮራና አንፀባራቂ ታሪክ ያላሠራ ይመስል፣ በዚህ ዘመን ብሔር ተኮር ግጭት መቀስቀሱ ያሳፍራል፡፡ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው፣ ተፋቅረውና ተዋልደው በኖሩባት ታሪካዊ አገር ውስጥ ጠባብነት አገር እስኪያፈርስ ድረስ መቀንቀኑ ያሳምማል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን በወሳኝ ታሪካዊ የሽግግር ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡ ይኼንን ታላቅና ታሪካዊ ወቅት በብልኃትና በኃላፊነት መንገድ በመምራት አንፀባራቂ ውጤት ለማስመዝገብ፣ ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊነት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ታሪካዊ የሽግግር ወቅት በመላ ኢትዮጵያዊያን ሁለገብ ተሳትፎ ወደፊት መራመድ አለበት፡፡ ለዚህ ሽግግር የተቃና ዕርምጃ ደግሞ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የእምነት፣ የፖለቲካ አቋምና የመሳሰሉት ልዩነቶች ጠበው ለብሔራዊ ጉዳዮች የጋራ ራዕይ ሊኖር የግድ ይላል፡፡ በስግብግብነትና ከመጠን ባለፈ ራስ ወዳድነት ይህንን መልካም አጋጣሚ ማበላሸትና ማጨናገፍ አይገባም፡፡ ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ የሚደረግ ሽግግር ለኢትዮጵያ ራዕይ በሌላቸው እንዳይጨናገፍ በአንድነት መቆም ተገቢ ነው፡፡ ይህ የሽግግር ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ሲገጥመው ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሲያጋጥም፣ እንደ ጲላጦስ እጅን እየታጠቡ ጣትን ወደ ሌሎች ከመቀሰር ችግርን የጋራ አድርጎ መፍትሔ መፈለግ የዜግነት ግዴታን መወጣት ይገባል፡፡ ሽግግሩ በምርጫው አማካይነት በስኬት ተጠናቆ በነፃነትና በእኩልነት መኖር የሚቻለው እንደ አየር ፀባይ በሚለዋወጥ ወላዋይ አቋም ሳይሆን፣ ስህተት ሲፈጸም በመወቃቀስና የማስተካከያ ሐሳብ በማቅረብ ጭምር ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ጽንፍ እያስያዙ ለጭቅጭቅና ለግጭት የሚዳርጉ ችግሮችን ከመኮልኮል ወይም እንደ ነገረኛ ሰው ስህተት ብቻ ከማነፍነፍ ይልቅ፣ የመፍትሔ አካል ሆኖ ለውጤታማነት መታገል ያስከብራል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የምትፈልገው እንደ ዓድዋ ጀግኖች ከፊት ረድፍ ተሠልፈው የሚታገሉላትን እንጂ፣ ወሬ ላይ ተጥደው የአሉባልታ መርዝ እየረጩ የሚያመሳቅሏትን አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትገነባ የሚመኝ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ የግልና የቡድን ጥቅም ከአገር በላይ እንዳይሆን መታገል አለበት፡፡ በዚህ ዘመን አገር እያመሱ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ዋና ችግራቸው ከአገር በላይ እንሁን ማለታቸው ነው፡፡ የአገር ክብርና ታሪክ ምንም የማይመስላቸው፣ ሌላው ቀርቶ የዓለም ጥቁሮች መመኪያ የሆነውን ታላቁን የዓድዋ ድል ጭምር ያንቋሽሻሉ፡፡ ለአገር ክብርና ታሪክ ደንታ ቢስ የሆኑ ግለሰቦችና ስብስቦች፣ የአገርን ራዕይ ከማጨናገፍ ወደኋላ አይሉም፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት መጫወቻ ካደረጋት አምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ያስችላታል የተባለውን ምርጫ ለማካሄድ ስትዘጋጅ፣ በየቦታው ግጭት በማስነሳት የንፁኃን ሕይወት መቅጠፍ፣ የአገር አንጡራ ሀብት ማውደም፣ ዜጎችን ከቀዬአቸው ማፈናቀልና በአጠቃላይ አገርን ተስፋ ቢስ ማድረግ መወገዝ አለበት፡፡ ለአገር ደንታ የሌላቸው ስግብግቦችና የአቋራጭ ሥልጣን ፈላጊዎች፣ ሕዝቡን እርስ በርስ እያጋጩ አገር እንዲያተራምሱ መፍቀድ አይገባም፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በሕግ አደብ ገዝተው በመፎካከር አገርን ወደ ታላቅነት መመለስ ታሪካዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በአንድነት መቆም ይኖርበታል፡፡ የዓድዋ ጀግኖች በመስዋዕትነታቸው ያስተማሩት ይኼንን ታላቅ ኃላፊነት ጭምር ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት የሚጎለብተው ከሥልጣን በላይ አገር እንደምትቀድም ማስተማመኛ ሲገኝ ነው፡፡ በአፍ ከሚነገረው በላይ ለሕዝብ ሲታሰብ ነው፡፡ በሰከነ መንፈስ ለመነጋገርና ለመደራደር መቀራረብ መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ ሕዝብን በአግባቡ በማዳመጥ ምላሽ ለመስጠት ተነሳሽነት ሲኖር ነው፡፡ ከኋላ ቀርና አሮጌ አስተሳሰቦች በመላቀቅ የዘመኑን ትውልድ ፍላጎቶች የሚወክሉ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ሲቻል ነው፡፡ ታላቁን የዓድዋ ድል ተምሳሌታዊነት በማረጋገጥ ድሉን ከምንም ነገር በላይ በመዘከር ነው፡፡ ይኼ ታሪካዊና አንፀባራቂ ድል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ቁርጠኝነት በመፍጠር ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ለኢትዮጵያዊነት ትልቁ ምሥል ከፍተኛ አክብሮት በመስጠት ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመሻገር የሚያስችሉ አስተማማኝ የጋራ መፍትሔዎች መገኘት የሚችሉት፣ በዚህ መንፈስ ማሰብና መግባባት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሲፈልጉ የሚለብሱት፣ ሳይፈልጉ የሚያወልቁት ሸማ ሳይሆን ትውልዶች መስዕዋትነት የከፈሉለት ህያው አገራዊ መገለጫ ነው፡፡ ይህንን ታላቅ እሴት ማስቀጠል የሚቻለው ደግሞ በጥልቅ የአገር ፍቅር ስሜት ነው፡፡ በታላቁ የዓድዋ ድልም ሆነ በተለያዩ ዓውደ ግንባሮች ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ሲገብሩና አጥንታቸውን ሲከሰክሱ የኖሩት፣ ለውዲቷ አገራቸው በነበራቸው ወደር የሌለው ፍቅር ነው፡፡ ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የአገር ክብር ማንሰራራት ያለበት በዚህ ምክንያት ነው!