Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፍርድ ቤት በእነ አቶ ስብሃት ነጋና አቶ ዓባይ ወልዱ መዝገብ በመርማሪዎችና ጠበቆች...

ፍርድ ቤት በእነ አቶ ስብሃት ነጋና አቶ ዓባይ ወልዱ መዝገብ በመርማሪዎችና ጠበቆች ላይ ትዕዛዝ ሰጠ

ቀን:

አቶ ስብሃት በታሰሩበት የግል ሐኪማቸው እንዲያክማቸው ተፈቅዷል

በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት እነ አቶ ስብሃት ነጋ (ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች) እና እነ አቶ ዓባይ ወልዱ (ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች) የምርመራ መዝገብ ላይ ክርክር እያደረጉ በሚገኙት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድንና በተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ላይ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የሰጠው የካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ተጠርጣሪዎቹ ችሎት በቀረቡበት ወቅት ሲሆን፣ ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱም ተከራካሪዎች አንዱ ሌላውን፣ ‹‹ክርክሩ ከምርመራ መዝገቡ የወጣ በመሆኑ ትክክል አይደለምና ፍርድ ቤቱ ዕርምት ሊሰጥበት ይገባል›› ሲል፣ ሌላው ደግሞ ‹‹ክርክሩ ከምርመራ መዝገቡ የወጣ ከሆነ ማስቆም ያለበት ፍርድ ቤት እንጂ ተከራካሪው ያለ ሥልጣኑ መናገሩ ማሸማቀቅና ማስፈራራት ነው›› በማለት ባሰሙት ቅሬታ አቤቱታ ምክንያት ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ቅሬታው የተፈጠረው መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው 14 የምርመራ ጊዜ በመቀሌ የሚገኘው የምርመራ ቡድን የላከለትን የ200 ሰዎች የምስክርነት ቃል ለይቶ ከዋናው የምርመራ መዝገብ ጋር ማያያዙን፣ ቡድኑ የላከለትን ሁለት ማዳበሪያ የተለያዩ ማስረጃዎችን የመለየት ሥራ ሠርቶ ከምርመራ መዝገቡ ጋር ማያያዙን፣ በትግርኛና በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ 500 ገጽ የሰነድ ማስረጃዎችን በአማርኛ አስተርጉሞ ከምርመራ መዝገቡ ጋር ማያያዙንና ተጨማሪ የ85 ሰዎች የምስክርነት ቃል መቀበሉን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በመቀሌ ከተማ የሚገኙና ወሳኝ የሆነ የሰነድ ማስረጃዎችን አሰባስቦ ማስመጣት፣ ተጠርጣሪዎቹ ሲጠቀሙበት የነበረ የጦር መሣሪያን ተከታትሎ መያዝ፣ ተጨማሪ የምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ያልተተረጎሙ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን ማስተርጎምና በመቀሌ የሚገኘው የምርመራ ቡድን የምርመራ ሥራውን አጠናቆ መመለስ ስለሚቀረው፣ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 59(2) ድንጋጌ መሠረት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው የምርመራ ሪፖርት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሁሉም ተጠርጣሪዎች ጠበቆች መጀመርያ ያነሱት ነጥብ፣ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ምርመራ ሪፖርት በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ስለመሥራቱ ማረጋገጫ እንደሌለ በመግለጽ ነው፡፡

‹‹ሁለት ማዳበሪያ የሰነድ ማስረጃ መቀበሉን ለፍርድ ቤቱ መንገር ምን ማለት ነው?›› በማለት የጠየቁት ጠበቆቹ፣ በምርመራ ስለማግኘቱ የሚያሳይ ምንም ነገር አለማቅረቡን ገልጸዋል፡፡ ተደጋጋሚ የሆኑ የምርመራ ግኝቶችን ከመናገር ባለፈ አዲስ የምርመራ ግኝት ስለማግኘቱ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው ማስረጃ እንደሌለም ጠበቆቹ አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ አብዛኞቹ በጡረታ የሚኖሩ ከመሆናቸው አንፃር፣ ቡድኑ የሚሠራውን የምርመራ ሒደት ሊያደናቅፉ የሚችሉ አለመሆናቸውንም አክለዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ተከታትሎ የሚይዘው የጦር መሣሪያ እንዳለ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን በሚመለከትም፣ ‹‹በማን እጅ የነበረን የጦር መሣሪያ? ወይስ በሙሉ በክልሉ የሚገኘውን የጦር መሣሪያ ነው? የጦር መሣሪያ ሰብስቦ እስከሚጨርስ አስሮ ሊያቆያቸው ነው?›› የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ጥያቄው ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ምርመራው በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ፍርድ ቤቱ ሊቆጣጠረው የማይችልበት ደረጃ ሊደርስ ስለሚችል፣ መርማሪ ቡድኑ መጀመርያ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ሊያከብር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ችሎት በሰጠው ትዕዛዝ፣ የእንዳንዱ ተጠርጣሪ የወንጀል ተሳትፎ ተለይቶ እንዲቀርብ ያለ ቢሆንም፣ አሁንም (በዕለቱ) ያቀረበው የምርመራ ሪፖርት በጥቅልና አንድ ላይ በመሆኑ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሊከበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪዎቹ እንዳይጎዱ ማድረግ እንደሚገባና አቶ ዓባይ ወልዱ በዕድሜና በሕመም እየተጎሳቆሉ መሆኑን ጠቁመው፣ መታሰር እንዳልነበረባቸውም ተናግረዋል፡፡ በጥቅልና በጅምላ የሚቀርብ የምርመራ ሪፖርት ሆን ተብሎ ተጠርጣሪዎቹን በእስር ለማቆየት እንደሆነ ገልጸው፣ የእያንዳንዱ ተጠርጣሪ የወንጀል ተሳትፎ ለተይቶ ከቀረበ፣ ፍርድ ቤቱም ሆነ ተጠርጣሪዎቹ ምርመራ ሒደቱ የት እንደደረሰ ለማወቅ እንደሚያስችላቸውና ጠበቆችም የሚከራከሩበትን ጉዳይ ለይተው ተገቢ የሆነ ክርክር ማቅረብና ማገዝ ያለባቸውን የሕግ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያግዛቸው አስረድተዋል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉም የሚያዘው እንዲህ መሆኑን በመጠቆም፣ መርማሪ ቡድኑ እያደረገው ያለው የምርመራ ሒደት ግን ሕጉን እየተከተለ እንዳልሆነ አክለዋል፡፡

በደንበኞቻቸው ላይ ምርመራ ከተጀመረ ከሦስት ወራት በላይ እንደሆነና ከሥነ ሥርዓት ሕጉ ውጪ መሆኑን ሲያስረዱ፣ ፍርድ ቤቱ በመሀል ገብቶ፣ ‹‹ምርመራው የተጀመረው ከጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ አይደለም እንዴ?›› የሚል ጥያቄ አንስቷል፡፡ ጠበቆቹ ምርመራ የተጀመረው ጦርነቱ በተጀመረ ማግሥት መሆኑንና ሰዎች ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ማሰብ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዋስትና መብት ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ በጠባቡ መተርጎም እንደሌለበት ጠቁመው፣ መብት መሆኑ ቀርቶ በልዩ ሁኔታ (Exceptions) በጠባቡ ትርጉም እየተሰጠበት መሆኑንም አክለዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የሚያስተረጉመውን የሰነድ ማስረጃ እየጠበቀ እንደሆነና ሌሎች ምርመራዎች እንደቀሩት ለፍርድ ቤቱ እያስረዳ ቢሆንም፣ የትግራይ ክልል የሽግግር መንግሥት ደግሞ በተጠርጣሪዎች ላይ በሚቀጥለው ሳምንት ክስ እንደሚመሠረትባቸው እንደገለጸ ጠቁመው፣ ‹‹ይህ አካሄድ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ምን ዓይነት አመኔታ ሊኖር ያስችላል?›› በማለትም ጠበቆቹ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ አንድና ሁለት ገጽ በደንብ የተዘጋጀች የምርመራ ሪፖርት ለፍርድ ቤቱ እያቀረበ፣ በዚያ ላይ ብቻ ክርክር ማድረጉ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረው፣ የምርመራ መዝገቡን ለፍርድ ቤቱ በማቅረብና ኦዲት እየተደረገ ቢሠራ፣ የተሠራውንና ያልተሠራውን በመለየት የምርመራ ሒደቱን መከታተል እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከተለያየ ቦታ ተይዘው እያለ በጥቅልና አንድ ላይ አድርጎ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ፣ የሚመለከተውንና የማይመለከተውን ለመለየት እንደማይቻልና ተገቢም እንዳልሆነም አክለዋል፡፡

የምርመራ መዝገቡን ፍርድ ቤቱ አስቀርቦ እየተመለከተ ምርመራው ቢቀጥል፣ ለምርመራው የሚወጣውን አላስፈላጊ ወጪ (Judicial Economy) ማስቀረት ይቻል እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የፖለቲካ አመራሮችና ፖለቲከኞች መሆናቸው እየታወቀ፣ በሚያምኑበት ነገር ላይ ሲገልጹ የነበረውን ድምፅ (Audio) እና ምሥል (Video) እያሰባሰቡ በማስረጃነት ማቅረብ ተገቢ እንዳልሆነ ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ጦርነት መቆሙን ተናግሮ ሳለ፣ መርማሪ ቡድኑ ግን የምስክሮችን ቃል ለመቀበል አካባቢው የጦርነት ቀጣና ስለሆነ እንዳልቻለና ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው 14 ቀናት መጠየቁ ተገቢ ስላልሆነ፣ ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ ደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በድጋሚ ባቀረበው የመከራከሪያ ሐሳብ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ ለፍርድ ቤቱ የሚቀርበው ወይም የሚነሱት ጉዳዮች ከሕግ ጋር የተገናኙ ብቻ ናቸው፡፡ ነገር ግን የተጠርጣሪዎች ጠበቆች እያነሱና እየተከራከሩ ያሉት ከምርመራ መዝገቡ ውጪ የፖለቲካ አመለካከታቸውን ነው፡፡ ከምርመራ መዝገቡ ጋር አይገናኝም፡፡ ክርክራቸው ከጊዜ ቀጠሮ ክርክር ጋር ብቻ የተገናኘ መሆን አለበት፡፡ መንግሥት፣ ‹‹ጦርነት ቆሟል፣ ከሳምንት በኋላ ክስ እመሠርታለሁ›› የሚለው የተለያዩ መዝገቦች ኖረውት ካልሆነ በስተቀር፣ እሱ (መርማሪ ቡድኑ) ከያዘው ምርመራ መዝገብ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ጠበቆች እያነሱት ያለው መከራከሪያ ሐሳብ ከምርመራ መዝገቡ ውጪ በመሆኑ እርምት ሊወስዱበት እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

በተሰጠው ጊዜ ያከናወናቸውን የምርመራ ዓይነቶችና ሒደቶች አስረድቶና በጽሑፍ ጭምር ገልጾ እያለ፣ ዳተኝነት ይታይበታልና አልሠራም ሊባል እንደማይገባም አክሏል፡፡ ከገለጻቸው የምርመራ ሥራዎች በተጨማሪ ቀሪ የሚሠራቸው ምርመራዎች እንዳሉ በመግለጽ፣ ጉዳዩ ውስብስብና በርካታ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ እንደሆነም አስረድቷል፡፡ መሣሪያ መሰብሰብን በሚመለከት ጠበቆች ያነሱትን መከራከሪያ ሐሳብ በሚመለከትም፣ የተጠርጣሪዎቹ አጃቢዎች በርካታ የጦር መሣሪያ ስለነበራቸው እነዚያ መሣሪያዎች ተሰብስበው ወንጀል እንደተሠራባቸው ወይም እንዳልተሠራባቸው መመርመር ስላለባቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የጦር መሣሪያው ከወንጀል ድርጊቱ ጋር ግንኙነት የለውም ሊባል እንደማይችልም አክሏል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች መርማሪ ቡድኑ ባነሳቸው መከራከሪያ ሐሳቦች ላይ በሰጡት ምላሽ እንዳስረዱት፣ ተጨማሪ ምስክሮች እንደሚቀሩትና ቃል ለመቀበል አካባቢው የጦርነት ቀጣና በመሆኑ ሥጋት አለ ያለው መርማሪ ቡድኑ ነው፡፡ ምስክሮችን ማግኘትና ቃል መቀበል እንደማይችልም የገለጸው ራሱ ምርመራ ቡድኑ ሆኖ ሳለ፣ ጠበቆቹ ከምርመራ መዝገብ ውጪ እንደሆኑ አድርጎ መግለጹ ተገቢ አለመሆኑንና ሥልጣኑም እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ጠበቆችን ለማሸማቀቅና ለማስፈራራት የሚደረግ ሐሳብ መሆኑን ጠቁመው፣ ተከራካሪ ወገን ከክርክር ጭብጡ ውጪ ሲሆን የማስቆምና የመከልከል ሥልጣን የፍርድ ቤቱ እንጂ የምርመራ ቡድን እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ እነሱ (ጠበቆቹ) አውጥተው አውርደው፣ አስበውና አምነውበት የሚከራከሩበት ሒደት ከምርመራ መዝገቡ ውጪ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ሊያስቆማቸው እየተገባ፣ መርማሪ ቡድኑ ማሸማቀቂያ ሊያደርገው እንደማይገባ አስታውቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ወክሎ የሚቀርበው ተቋሙን እንጂ፣ አመራሮች የነገሩትንና በወረቀት ላይ ብቻ ባለው ላይ መነጋገር አለባችሁ ሊላቸው እንደማይችል ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ አለበለዚያ የእነሱ (የጠበቆቹ) ተጠርጣሪዎችን ወክለው መቆም አስፈላጊ እንደማይሆን ጠቁመው፣ ፍርድ ቤቱ የሕግ ግምት (Judicial Notice) ሊወስድበት እንደሚገባም ስላመኑበት እንደሚናገሩም አክለዋል፡፡ እነሱ (ጠበቆች) ከማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብም ሆነ ግንኙነት ወይም አቋም እንደሌላቸው ተናግረው፣ መንግሥት የገለጸውን ከመናገር ወደኋላ እንደማይሉና መርማሪ ቡድኑ መገናኛ ብዙኃን በሚመቻቸው መንገድ እንደፈለገ አቅርቦ፣ ለዚያ መልስ ሲሰጥ ለማስፈራራትና ለመሸማቀቅ መሞከሩ ተገቢ ስላልሆነ፣ ፍርድ ቤቱ እርምት እንዲወስድ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑና ጠበቆች ጠንከር ብለው በተከራከሩበት፣ ‹‹ከምርመራ መዝገብ ውጪ የፖለቲካ ክርክር እየቀረበ ነው በሚለውና ለማስፈራራትና ለማሸማቅ እየተደረገ ነው፤›› በሚለው መከራከሪያ ሐሳብ ላይ፣ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ሁለቱም ተከራከሪዎች ፖለቲካዊ ለዛ ያለው ክርክር እንዳያቀርቡ አሳስቧል፡፡

የአቶ ስብሃት ነጋን የሕክምና ጉዳይ በሚመለከትም ጠበቆቹ ባቀረቡት ክርክር፣ ተጠርጣሪው በፖሊስ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል ተምርምረው የተወሰነ ሕክምና ቢደረግላቸውም ቀሪ ምርመራ እንደሚቀራቸው እንደተነገራቸው ገልጸው፣ ቀደም ብሎ ያክማቸውና የምርመራ ታሪካቸውን (Medical History) የሚያውቀው ሐኪም በአዲስ ሕይወት ሆስፒታል ስለሆነ በአጃቢ ወጥተው እንዲታከሙ ጠይቀዋል፡፡ የጤና ጉዳይ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ፣ ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የተፈቀደ መብት በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡   

ሌሎች ደንበኞቻቸውም በጡረታ የሚተዳደሩና ቤተሰቦቸውን የሚያስተዳድሩ በመሆናቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው ውክልና እንዲሰጡ እንዲፈቀድላቸውም ጠይቀዋል፡፡ አቶ ገብረ መድኅን ተወልደ የተባሉ ተጠርጣሪ ከተጠረጠሩበት ጉዳይ ጋር ምንም ግንኙነት ስለሌላቸው የጊዜ ቀጠሮ መስጠት ሳያስፈልግ መዝገቡ ታይቶ ከእስር እንዲፈቱ ጠበቃቸው ጠይቀዋል፡፡

በወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምና በወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር ላይ መርማሪ ቡድኑ ተመሳሳይ ምርመራ ሪፖርት አቅርቦ የሚቀሩትን የምርመራ ሒደቶች ለማጠናቀቅ 14 ቀናት ጠይቆባቸዋል፡፡

ጠበቆቹ ለሌሎች ደንበኞቻቸው ያነሱት የመከራከሪያ ነጥቦች ለእነ ወ/ሮ ኬሪያም እንዲመዘግብላቸው ጠይቀው ተጨማሪ መከራከሪያ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ምርመራውን ማራዘምና በሕግ አግባብ አለማጠናቀቅና የምርመራ ሐደቱን በጅምላ ማቅረብ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልተፈጸመና በፍርድ ቤት እንደተፈጸመ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁሞ፣ ምርመራው ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ሕግጋትን ባከበረ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግሯል፡፡ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ ያለውን የወንጀል ተሳትፎ ለመለየት እየሠራ እንደሆነና ምርመራውን አጠናቆ ለዓቃቤ ሕግ ሲያስተላልፍ፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ የእያንዳንዱን ተጠርጣሪ ተሳትፎ ለይቶ እንደሚያቀርብ አስረድቷል፡፡ ውክልናን በሚመለከት ሀብት የመለየትና የማጣራት ሥራ እየተሠራ በመሆኑ መከራከር እንደማይችል ገልጾ፣ አቶ ዓባይ ዕድሜያቸው ትልቅ ስለሆነ መታሰር አልነበረባቸውም ለሚለው የጠበቆች ክርክር፣ ክርክሩ የሕግ መሠረት የሌለውና ተገቢ አለመሆኑን መርማሪ ቡድኑ አስረድተዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ፣ መርማሪ ቡድኑ የሰበሰባቸውን ማስረጃዎች ተጠርጣሪዎቹ ባላቸው የወንጀል ተሳትፎ ለይቶ ከምርመራ መዝገቡ ጋር አያይዞ ማቅረብ እንዳለበት ገልጿል፡፡ መርማሪዎችና ጠበቆች ፖለቲካ ይዘት ያላቸው ክርክሮች እንዳያቀርቡም አሳስቧል፡፡ ያልተተረጎሙ ሰነዶችን አስተርጉሞ ከምርመራ መዝገቡ ጋር እንዲያያዝና የጡረታ አበልና ሌሎች ማኅበራዊ ነገሮችን በሚመለከት፣ ተጠርጣሪዎች በአጃቢ ሆነው ውክልና እንዲሰጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ንብረታቸው ለተወሰደባቸው ተጠርጣሪ እንዲመለስላቸው አስታውቋል፡፡

የአቶ ስብሃትን ሕክምና በሚመለከት ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ሕክምናው መሰጠት ያለበት ተጠርጣሪው ባሉበት ማረሚያ ቤት ግቢ ውስጥ ነው ወይስ በሌላ ቦታ?›› የሚለውን ጭብጥ ይዞ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 21 (2) ድንጋጌ መንፈስን ሲመረምር፣ ታካሚው ባለበት በማረሚያ ቤት እንደሚሆን ቢያሳይም፣ በልዩ ሁኔታ ታካሚውን በሚጠቅም መንገድ ከማረሚያ ቤት ውጪ እንዳይታከም እንደማይከለክልም አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የአቶ ስብሃት የግል ሐኪም የሕክምና መሣሪያውን ይዞ በማረሚያ ቤት ግቢ እንዲያክማቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ነገር ግን ሕክምናው መሣሪያ የሚያስፈልገውና በሐኪም ቤት መሰጠት አለበት ካለ፣ ሐኪሙ ፍርድ ቤት ቀርቦና አስረድቶ እንዲታከሙ ማድረግ እንደሚችል በመግለጽ፣ ከተጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ 13 ቀናት በመፍቀድ ለመጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡             

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...