የምርጫ አስፈጻሚ አባላት ተሰይመዋል
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዓርብ የካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ፣ ከዚህ ቀደም ለዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ተልኮ ይሁንታ ያገኘውን መተዳደሪያ ደንብ ተቀብሎ አፀደቀ፡፡ ጉባዔው በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ተዘጋጅቶ የቀረበለትን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የምርጫ ማስፈጸሚያ መመርያ ላይ ከተወያየ በኋላ ሦስት የምርጫ አስፈጻሚ አባላትን ሰይሟል፡፡
በአይኦሲ ማሻሻያ ተደርጎበትና ተቀባይነት አግኝቶ የመጣው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መተዳደሪያ ደንብ፣ በአራት ክፍልና በ43 አንቀጾች የተደራጀ ነው፡፡ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዓምና በጉባዔው አፀድቆ ለአይኦሲ ልኮት በነበረው መተዳደርያ ደንብ ውስጥ ከስያሜ ጋር ተያይዞ፣ ቀደም ሲል ‹‹ኢመርጀንሲ ኮሚቴ›› ይባል የነበረው በማኔጅመንት ኮሚቴ እንዲተካ፣ እንዲሁም በደንቡ አንቀጽ 12 መሠረት የአባላት መብቶችን አስመልክቶ አከራካሪ ሆኖ የቆየው፣ በክልልና በከተማ አስተዳደር የኦሊምፒክ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ‹‹መኖር አለበት፣ የለበትም›› የሚለው መኖር እንዳለበት በአይኦሲ ይሁንታ አግኝቷል፡፡ የዕድሜ ጣሪያ፣ ዕጩ የሚቀርብበት መሥፈርትና ሌሎችም በመመርያው ውስጥ ከተካተቱት ይጠቀሳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መተዳደሪያ ደንብ፣ በየአራት ዓመት አንድ ጊዜ ፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ማድረግ እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ ባካሄደው 45ኛ ጉባዔው፣ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው አመራር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በ2020 መካሄድ የነበረበት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ስያሜውን እንደያዘ በ2021 እንዲካሄድ መደረጉን ተከትሎ፣ በአመራር የተጀመሩ እቅዶችና ዝግጅቶች በተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት መከናወን ስላለባቸው እስከ ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ማግሥት እንዲቆይ ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡
ሌላው በዕለቱ ጉባዔው ትኩረት ሰጥቶ የተነጋገረበት ጉዳይ፣ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተዘጋጅቶ የቀረበው የምርጫ ማስፈጸሚያ መመርያ ይጠቀሳል፡፡ በመተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ 6 መሠረት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መመርያዎችን ማውጣትና በተግባር ላይ የማዋል ሥልጣን የተሰጠው በመሆኑ ይህን መመርያ መውጣቱ ተነግሯል፡፡
የቀረበው የምርጫ ማስፈጸሚያ መመርያ በ12 አንቀጽ ተደራጅቶ የቀረበ ሲሆን፣ በተለይም እንዲህ ዓይነቱ መመርያ ከምርጫ በፊት ቀደም ብሎ መቅረብ መቻሉ ጠንካራ ብሔራዊ ተቋም ለመመሥረት የጎላ ፋይዳ እንዳለው በጉባዔው አባላት ታምኖበታል፡፡
ይህ የምርጫ ማስፈጸሚያ መመርያ ቀደም ባሉት ዓመታት ከምርጫ ጋር ተያይዞ ሲቀርቡ ለነበሩ አላስፈላጊ ውዝግቦችና ሀሜቶች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ መተዳደሪያ ደንብ ላይ በጥቅሉ የተቀመጡትን የምርጫ ማስፈጸሚያ ደንብና ድንጋጌዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል በሚችሉበት መልኩ ለማዘጋጀትና የምርጫ አፈጻጸሙን ግልጽ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና በጉባዔው ተዓማኒነት ያለው ለማድረግ እንደሆነ ጭምር ከመድረኩ ተነግሯል፡፡
የዕጩ አቀራረብ የምዝገባ ሥርዓትና የተገቢነት ጉዳይ በመመርያው ተካቷል፡፡ ከተካተቱት መካከል ለሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባልነት፣ አልያም ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚፈልግ ሰው በትምህርት ዝግጅቱ ቢያንስ የመጀመርያ ዲግሪና ኢንተርናሽናል ቋንቋ መቻል እንደሚኖርበት፣ ይህ መሥፈርት ኦሊምፒያን የሆኑ አትሌቶችን እንደማይመለከት፣ በሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ውስጥ ሁለት ኦሊምፒያኖች አንድ ወንድና አንድ እንስት እንደሚካተቱበት ያሳያል፡፡
የክልልና የከተማ አስተዳደር ተወካዮች ምርጫን በተመለከተ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 12. 1.3 መሠረት ሁለት ተወካዮች በጉባዔ ተመርጠው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል መሆን እንደሚችሉ፣ አንድ ክልል ወይም ከተማ አስተዳደር ከአንድ ዕጩ በላይ ማቅረብ አይችልም የሚሉትና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡
ጉባዔው በመጨረሻም ጥበቡ ቸኮል (ዶ/ር)፣ አቶ አዱኛ ይግዛውና ወ/ሮ አዜብ ወልደ ሥላሴ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አድርጎ መርጧል፡፡