በበቀለ ሹሜ
- መነሻ
ከጥቅምት 24 አንስቶ በታየውና በተገላለጠው ልምድ መሠረት የወረራ ትርጓሜ ውጫዊና ውስጣዊ ተብሎ መስተካከል የሚሻ አይመስለኝም፡፡ የዚያ ዓይነት እንግዳ ልምድ ፊትም የታየ ወደፊትም የሚደገም ስለመሆኑ ያጠራጥራል፡፡ አናሳ ነጭ ዘረኛ ገዥዎች ደቡብ አፍሪካንና ሮዴዢያን በተቆጣጠሩበት ዘመን ጥቁሮች ወታደርና ሰላይ እየሆኑ አገልግለዋል፣ የእንጀራ ገመድ ይዟቸው፡፡ ለረዥም ጊዜ ቅኝ በተያዙም ሆነ ለአጭር ጊዜ በቅኝ ኃይል ነፃነታቸውን ተገፈው በዱር በገደል የአርበኝነት ትግል ውስጥ በነበሩ አገሮችም ዘንድ፣ ለቅኝ ገዥዎች ባንዳነት መግባት እንግዳ ነገር አልነበረም፡፡ ፋሺስት ጣሊያን አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ በቆየበት ጊዜ ባንዳ ሹሞችና ወታደሮች ነበሩ፡፡ በባንዳነት ሽፋን የሚስጥር አርበኝነት ሥራ መሥራት፣ አዘንግቶና ስንቅ ዘርፎ ከባንዳነት ወደ አርበኝነት መግባት፣ በጦርነት እሳት ውስጥ አፈሙዝን ወደ ጠላት ማዞር ሁሉ በእኛም አገር ሆነ በሌሎች አገሮች ውስጥ ታይቷል፡፡
የውስጥ ወረራው ከከሸፈ በኋላ ወራሪዎቹ መቀሌን ለቀው ተሰዳጅ በሆኑበት ጊዜ የበቀሉበትን ሕዝብ የባንክ ገንዘብ፣ መድኃኒትና የመሳሰሉ ስንቆችን ከመዝረፍ በላይ በአሥር ሺሕ የሚቆጠር እስረኛ ከተማ ላይ በትነው ሕዝብ በወሮበላ ቁም ስቅሉን እንዲያይ ማድረጋቸውም ሌላ የዱርዬ ፖለቲካቸው መገለጫ ነበር፡፡ እነሱ የሕዝብ ጥሪትን የጦርነት መደገሻ አድርገው፣ ዕጦት በተባባሰበት ሕዝብ ላይ እንደገና ወሮበላ ረጭተው ለፈጠሩት ሥርዓተ አልባነት በጊዜያዊነት የተቋቋመን አስተዳደር ተወቃሽ ለማድረግ መልፋት ከዱርዬነትም ዱርዬነት ነው፡፡ የጎረቤት አገሮችን በገዛ አገር ላይ ወረራ እንዲያካሂዱና ለእርስ በርስ ፍጅት አብሲት የሚሆኑ ጭፍጨፋዎችን እንዲያጎበጉቡ አማካሪና ድልድይ ሆኖ ማገልገል ደግሞ ሌላ እንግዳ የሆነ ባንዳነት ነው፡፡ እናትን ገበያ አውጥቶ ከማስማማት የከፋ የክህደት ተግባር ነው፡፡ ይህ ድርጊታቸው ቢሳካ ምን ጥቅም ታገኘላችሁ ተብለው ቢጠየቁ ምን መልስ እንደሚኖራቸው አላውቅም፡፡ ከእርስ በርስ ፍጅትና መበታተን ውስጥ ትግራይን እንደነበረች እናገኛትና ሥልጣን ላይ እንወጣለን ብለው እያሰቡ ከሆነ እዕምሯቸው ተስፋ በሌላው አኳኋን ተናውጧል ማለት ነው፡፡ ልባቸውንና ምላሳቸውን ከተግባራቸው ጭምር የሚመራው የበቀል እሳት ነው፡፡ ኢትዮጵያም ትግራይም እንዳይሆኑ ሆነው ሲቃጠሉ በማየት እሰይ አንጀቴ ቅቤ ጠጣ የሚሉ ካልሆኑ በቀር የሚያገኙት ትርፍ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ግብግብ የገጠመው ከዚህ ዓይነት ጉግ ማንጉግ በቀል ጋር ነው፡፡
እንዲህ ያለ የመቶ በመቶ በቀልን እሰይታው ያደረገ ጉግ ማንጉግነት ከምን መጣብን? ጉግ ማንጉግ ዘመን ደርሶ ከተፈጥሮ ማኅፀናችን እንዲህ ያለ ጉድ ተፈጠረ? ጉዳችንን ከብሔረሰብና ከጎጥ ጋር ሊያገናኝ የሚሻ ፖለቲከኛ መልቲ ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ዕውር በቀል፣ አረመኔያዊ ጭካኔና አቀጣጥ የጠነነበት ወረራና ጭፍጫፋ (በኦሮሚያ በቤንሻንጉል ጉምዝና በሌሎችም ሥፍራዎች የታየው ሁሉ) ከፖለቲካ ማኅፀናችን የተወለደ ነው፡፡ ስህተትና ጥፋቱን ማየት አይወድም፡፡ ፖለቲካችን ከስህተትና ከጥፋት ተፀፅቶ መታረምም ለእኛ ፖለቲካ ውርደትና ሽንፈት ነው፡፡ በእኛ ፖለቲካ ጀግንነት የያዙትን የፀብ መንገድ ሳይለቁ፣ ለሰላም ሳይበለጡ ደርቆ፣ በእልህ ላይ እልህን በጥላቻ ላይ ጥላቻን ማናር ነው፡፡ የዚህ መጨረሻውም የማገናዘብ አቅምን እንዳለ ለጥላቻና ለበቀል እሳት ማስረከብ ነው፡፡ በዘግናኝ በቀል የመርካት ጉግ ማንጉግነት ላይ ያደረሰን ሕመምተኛው ፖለቲካችን ነው፡፡ የኦሮሞ ፅንፈኝነት ሕዝብን ከመዘንቸሩ በፊት የተወሰኑ ወጣቶችን ነበር የቀረጠፈው፣ ክራንቻ እንዲሆኑት፡፡ የሕወሓት ጉግ ማንጉጎችም የኢትዮጵያን መከላከያ (በተለይ ሰሜን ዕዙን) ከመግመጣቸው በፊት የትግራይን ወጣቶች ነበር የገመጡት፡፡ እንደ አገማመጣቸው ጥልቀት ናላቸውን እስከ ማጣት ጉዳት የደረሰባቸው፣ ያላንዳች ጥያቄ ለጭካኔያቸው መሣሪያ ሆነዋል፡፡ ከእነ ናላቸው የነበሩት፣ በተለያየ ሥፍራና ጊዜ ከተሰጣቸው ጭራቃዊ ተግባር መመለስ ችለዋል፡፡ ጉግ ማንጉጎቹ ከተሸነፉ በኋላ ዛሬም ናላቸውን ያላገኙ ጉዳተኛ ወጣቶች በየጉራንጉሩና በስደት ሥፍራ አሉ፡፡ ጉግ ማንጉጋዊ ክራንቻ ይህንን ያህል ነው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የዘነቸረው፡፡
ዛሬ የጎረቤት ወረራና ሰላም በጥባጭነት አቀናባሪ እስከ መሆን ድረስ በበቀል የሰከሩ የሕወሓት ጉዶች የተያያዙት የአገር ክህደት ሥራ፣ ከቅጥረኛነት ደመወዝና ‹‹የቤቴ መቃጠል ለትኋኑ በጀው›› ከሚል እሰይታ በቀር ትርፍ አያስገኝላቸው እንጂ፣ ኢትዮጵያን ሊጎዳ እንደሚችል ያውቃሉ፡፡ ኢትዮጵያን ወጣጥሯት የነበረው የጭካኔ አማሽነት ቀለል ቢልምና የፀጥታ መሻሻል ቢታይም፣ አሸምቆ ጥቃት አድራሽነትና መጠማመዱ ገና አልደረቀም፡፡ ፖለቲከኞቹ ውስጥ ያለው መጠማመድ የረመጥ ዓይነት ኑሮ እየኖረ ነው፡፡ የሱዳን ከኢትዮጵያ ወዳጅነት ማፈንገጥና ድንበር አልፎ ብዙ ንብረት አውድሞ መሬት መያዝ፣ ሌላ ጦርነት የሚጋብዝና በህዳሴ ግድብ ላይ የተጀመረውን ድርድር ጥሬ የሚያደርግ ነው፡፡ ወደ ጦርነት ቢገባ፣ ከሱዳን ጋር ሠልፍ የምትገባው ግብፅ ብቻ አይደለችም፡፡ ጦርነቱ ከወዲህም ከወዲያ ብዙ እጅ የገባበት ውስብስብ የጎራዎች ጦርነት ወደ መሆን ሊያድግ ይችላል፡፡ በሌላ ጎን የሕወሓት ጉዶች የሚለፉት የጎረቤት ጠላት በኢትዮጵያ ላይ በማሰማራትና በማሰባሰብ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ የምዕራቡንም ዓለም ከኢትዮጵያ ለማቆራረጥ የሐሳዊ መረጃ ሞገድ በራሱ በምዕራቡ ሚዳያ በኩል ማካሄድ ተያይዘዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ በኢኮኖሚ መንገድ የመፍጠር አቅመ ደካማ ለሆነቸው ኢትዮጵያ ምዕራባዊ ዕርዳታ (በተለይ የአውሮፓና የአሜሪካ) ቢሸመቀቅባት፣ ብዙ እንደምትጎዳና በዕቃዎች እጥረትና ልክ ባጣ ግሽበት ልትመታ እንደምትችል ያውቃሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው የከፋ ውጤት እንዲያመጡ አሥልተው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡
መካከለኛው ምሥራቅ ድረስ ጎራ ሊሠራ የሚችል ባለብዙ ሥለት ጥቃት እየተሸረበብን ሳለ፣ የለውጥ ፖለቲከኞች ነቅነቅ የማንል ከሆነ ወይም ዕዳውን ለመንግሥት ትተን ስለምርጫ የምናሰላስል ከሆነ የጉድ ነው! በሕወሓት፣ በኦነግ ሸኔና ምልምሎቻቸው አማካይነት በአገር ላይ የወረደው ግፍና ሰቆቃ በዙሪያችን ተከምሮ ሳለ፣ አሁንም ተስማሚ ሁኔታዎችን ጠብቆ ጉግ ማንጉግ ሊወልድ የሚችል የጥላቻና የበቀል ሽል በፖለቲካ ማኅፀናችን ውስጥ እያለ እስካሁን ለሆነው ሁሉ የጋራ የጥፋት ተጠያቂነት ያለብን መሆኑን አውቀንና በሆነው ነውር ሁሉ አፍረን፣ በፖለቲካችን ውስጥ ያንቀላፋውን የመጠማመድ ረመጥ አምክነን፣ በአገርና በሕዝብ ላይ የመጣ የጥቃት ትብትብ በጋራ ለመመከትና ሕዝብን በዚህ ለመካስ የሚባንን ነፍስ ከሌለን በግንቦቱ ምርጫ ለመሳተፍ ሽር ጉድ የምንለው ምን ልንፈይድ ነው? ሕመም የሚወደው ፖለቲካችን የወለዳቸውና የፖለቲካ ቀብራቸውን ያስፈጸሙ የእኛው ጉዶች የሚያስተናብሩትን ወረራ የማክሸፍና ሕዝብን የመካስ ተግባር የሚጠይቀን ዋጋ፣ ማዶ ለማዶ የቆመ የፖለቲካ አተያያችንን ማነካካት ብቻ ነው፡፡
ቀደም ባለ ጽሑፌ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ (አገራዊ ፓርቲ ነን የሚሉ) ኢትዮጵያን የብዝኃነት ኅብር አድርገው ቢያስተውሉና ብዝኃነቷ የግለሰቦች መቀረጪያ እንዲሆን ቢሹ፣ የራስ አስተዳደር ግንባታ ላይ ያተኮሩም የራስ አስተዳደራቸው ጉልህ ጉልምስናና ጥንካሬ በትልቅ አገር ግንባታ ውስጥ መሆኑን ተማምነው በራስ አስተዳደሮቻቸው ውስጥ ያሉ ማንነቶችን የኢትዮጵያዊ ማንነት አካል አድርጎ ማሸራረብን ሁነኛ ጉዳያቸው ቢያደርጉት፣ ሁለቱም ወገኖች አንድ ላይ ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል የአተያይ ዕርቅ ፈጠሩ ማለት ነው፡፡ ይህንን ዕርቅ በመፍጠራቸው ብዙ ማንነቶችን ያዋደዱና ብዙ ቋንቋዎችን የሚናገሩ አዲስ ትውልዶችን ያዋልዳሉ፡፡
ኅብረ ብሔራዊነት ሁሉም ዘንድ እንዲለማ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪነትና ባለብዙ ባህልነት የማኅበረሰቦች ጥቅል መታወቂያ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ አዲስ ተወላጆች ግለሰባዊ ገጽታም የሚሆንበት ጥርጊያ ከተከፈተ፣ በዚህ ጥርጊያ አማካይነት የብሔረሰብ መብቶች፣ የሰብዓዊ መብቶችና የዜግነት መብቶች የሚግባቡበት ምቹ ሁኔታ መልማት ይችላል፡፡ የልዩ ልዩ ብሔረሰቦች አባላት ብዙ ቋንቋዎችንና ባህሎችን የሚጋራ ማንነት ወደ ማበጀት ሲያመሩ የኢትዮጵያዊነት ማንነትም የዚህ ዓይነት ኅብራዊነት (ብሌንድ) መሆኑ ነውና፣ ገና ከወዲሁ ‹‹ኢትዮጵያዬ›› የሚሉና ‹‹ብሔሬ›› የሚሉ የጥላቻና የፍጥጫ ጥጎች የመኖር ምክንያት ያጣሉ፡፡ በሌላ አነጋገር የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ የአገረ መንግሥትና የራስ አስተዳደሮች ግንባታ፣ ከዴሞክራሲ ተቋማትና ባህል ግንባታ ጋር የተግባባ አገራዊ መሠረት ይቀዳጃልና የመሳካቱ ነገር የበለጠ አስተማማኝ ይሆናል፡፡ የለውጥ ፖለቲከኞችም የአተያይ ሰላማቸውንና ኅብረታቸውን ይዘው አገራቸው ላይ የተቃጣውን ወረራ ንፋስ በማይገባው አርበኝነት ለመመከት ይቀላቸዋል፡፡ አተያይን ከማስታረቅ ለግሞ፣ ለእነዚህ ሁሉ መልካም ዕድሎች ልማት ተቀናቃኝ መሆን፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ሌላ በደል መፈጸም ብቻ ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ራስን በራስ ማሰናበትም ይመስለኛል፡፡
2. የአርበኝነት ኅብረት የሚሰጥን ጉልበትና ተግባራት
2.1 ኢትዮጵያነት የብዝኃነት ሽርብነቱ ይሟላ! በባህል፣ በቅርስ፣ በሙዚቃ፣ በውዝዋዜ፣ በሙዚቃ መሣሪያ፣ በሥነ ቃል፣ ወዘተ ያሉን ሀብቶች ሁሉ ከአካባቢ ወደ አካባቢ እያቆራረጡ በመላ አገራችን ይታወቁ! ሁላችንም እንጋራቸው! ግለሰብነታችንም በብዝኃነታችን ያጊጥ! ብዝኃነታችን ግለሰባዊ ገጽታችንም ይሁን! በአፍ መፍቻ ቋንቋችን መጠቀምና መማር መብታችን እንደሆነ ሁሉ ቢያንስ ለሕይወታችን ቅርብ የሆኑ የፌዴራልንና የአካባቢያችንን የሥራ ቋንቋዎች ማወቅና መጠቀም መብታችንና ኃላፊነታችን ነው! እንዲህ ያለ አተያይ የመያዝ ነገር የፓርቲ ፖለቲካዊ ትርፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ የኅብረተሰብችንን ሰላምና መግባባት፣ ኢትዮጵያነትንና ኢትዮጵያዊነትን በዓለት ላይ የመገንባት ጉዳይ እንጂ፡፡ እንዲህ ያለ ኅብራዊና ሰፊ አመለከካት ውስጥ የመግባት ነገር የፓርቲዎችን ስብሰባ መቀመጥና መከራከርን ወይም ቅድመ ሁኔታዎች መደርደርን አይጠይቅም፡፡ በዚህ አተያይ የተመራ የተግባር እንቅስቃሴ ብዝኃነታችንን ከየጓዳችን እያወጣ ኢትዮጵያችንንና ግለሰባዊ ሰብዕናችንን ማበልፀጉን፣ ኅብረተሰባችንን አሸራርቦ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሰላማችንን ፅኑ መሠረት ማስያዙን የተረዱና ለእዚህ ዕውን መሆን መሥራት የሚሹ ወገኖች መጠራራታቸውና መሰባሰባቸው፣ ተሰባስበውም ዕይታቸውን ማጎልበታቸውና በሕዝባችን ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው፡፡
ሁለት ጥጎችን ባገናኘ (ባስታረቀ) እና ሕዝቦች ይሁነኝ ባሉት አተያይ ላይ የሚቋቋም የአርበኝነት ኅብረት ጠንካራ ነው፡፡ ይህንን ዓይነት ጠንካራ ኅብረት ኢትዮጵያችን ዛሬ በጣም ትፈልጋለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ አያሌ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሉ ለኢትዮጵያና ለህዳሴዋ የሚቆረቆሩ ሁሉ አንድ ላይ መቆም መቻላቸው በራሱ አንድ ትልቅ የፖለቲካ ጉልበት ነው፡፡ በተባበረ ኃይላቸውና እንቅስቃሴያቸው የውስጥ ሰላማቸው ላይ ፈጣን ለውጥ ካመጡ ደግሞ በጉልበት ላይ ሌላ ጉልበት ይጨምራሉ፡፡ ይህ የትብብርና ሰላምን የማረጋገጥ ጉልበት ብቻውን (አልፎ አልፎ ድጋፍ ሳይሻ) የሕወሓት-ኦነግ ሸኔ ፅንፈኛ ርዝራዦች ከውጪ የሚያካሂዱትን ሐሳዊ ፕሮፓጋንዳ ሰሚ የለሽ ትቢያ ያደርገዋል፡፡ በፖለቲካ ረገድ ራሳቸውን በራሳቸው የገደሉትን ሕወሓቶች ከሞት ለማስነሳት የተወሰኑ ምዕራባውያን አጋዦቻቸው ሲረጩት የቆዩት ውዥንብር ሁሉ የቆሻሻ ገንዳ ሲሳይ ይሆናል፡፡ አውሮፓና አሜሪካ ኢትዮጵያን ለማክበር ለማዳመጥና ለማገዝ የበለጠ ይፈቅዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ እንዲህ ደፍሮ ለመናገር የሚያበቃ ስትራቴጂካዊ ዋጋ አላት፡፡ ከአፍሪካ ቀንድ ጎረቤቶቿ ጋር ሰላምና ልማትን አሳልጣ ማደጓ በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ ጂኦፖለቲካዊ ተሻሚነት የምታስፈራቸው አገሮች ቢኖሩም፣ ከምሥራቃዊው የአኅጉሩ ክፍልና ከንግድ ቀጣናው ሰላምና ደኅንነት አኳያ ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት አገሮች ተቀዳሚዋ ነች፡፡ አቀማመጧ፣ ትልቅነቷና ከየጎረቤቶቿ ጋር ለጋራ ዕድገት መጣጣሯ የአፍሪካ ቀንድ ፈርጥ አድርጓታል፡፡ ለሃይማኖት አሸባሪነት መዘባነኛ ባለመሆንና በፀረ ሽብር ትግል አጋርነት መታወቋ፣ በሰላም አስከባሪነትና እያሸማገሉ የአካባቢ መረጋጋትን በማገዝ ረገድ መልካም ስም ማበጀቷ ሁሉ የአስፈላጊነቷ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ላይ አነሱም በዚያ የተዋጣ የዴሞክራሲ ምርጫ አክላበት፣ የአርበኝነት ኅብረቷን በኢኮኖሚና በዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ስታሠራው ደግሞ ያንኑ ያህል የፈርጥነቷ ዋጋ ይጨምራል፡፡ እናም የኢትዮጵያን ሰላማዊና ተስፋ ያላት አገር መሆን ምዕራባውያኑ የሚሹትና የሚያግዙት ኢትዮጵያ ጥቅማቸው መሆኗን ስለሚያውቁም ነው፡፡
ምንም ቢሆን ጥለው አይጥሉኝም በማለት ግን ኢትዮጵያ ልትዘባነን አትችልም፡፡ አንደኛ እንደ ኢትዮጵያ ለምዕራባውያን አስፈላጊ ከሆነችው ግብፅ ጋር በአሁኑ ደረጃ ጥቅሟ በ‹መሻኮት› ላይ ነው፡፡ የግብፅ አካሄድ በሽኩቻ መንገድ ውስጥ እስከ ቀጠለ ድረስም የጥቅማቸውን ተደጋጋፊነት ለዓለም ማሳመን ከባድ ሥራን ይጠይቃል፡፡ ሁለተኛ ኢትዮጵያ ያላት የውጪ ምንዛሪ አቅም በእጅጉ ከውጭ ድጋፍ መቅረትና አለመቅረት ጋር የተሳሰረ በሆነበት በአሁኑ ደረጃ፣ ትንፋሽ ሰብሰብ ለማድረግም ሆነ ለልማት ማኮብኮቢያነት የምዕራብ አውሮፓና የአሜሪካ ድጎማ ስለማስፈለጉ መናገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆንብኛል፡፡ እነዚህን ሁለት ሰበዞች በቅጡ አስተውሎ በብልኃት በመጠበብ ፈንታ፣ ‹‹እኛ ነፃነታችንን ጠብቀን የቆየን…›› ወዘተ የሚል ቀረርቶና ኃያላን አገሮች ተፅዕኖ ሊያደርጉ ቢችሉም በሉዓላዊ ጥቅማችን ላይ ዋናዎቹ ወሳኞች እኛ ነን የሚል አስተሳሰብ፣ በሦስት በኩል መያዝ ያለብንን ትክክለኛ ዕይታና ስሜት ያደናግራል፡፡ አንደኛ ኢትዮጵያውያንም ሆንን ነፃነት ተቀዳጀን ባይ አፍሪካውያን ዓድዋ ያንቦገቦገችውን የነፃነት ማሾ ለመንከባከብ ከመቸገር በባሰ ደረጃ፣ በኢኮኖሚ ግስጋሴና በብልህ ትግግዝ እጥረት ጭል ጭል ስናደርገውና ጥቀርሻ ስናጠጣው ኖረናል፡፡ እናም መነሻችን መሆን ያለበት መመፃደቅ ሳይሆን፣ በለማብን (በተንሰራፋብን) የፋይናንስ የኢኮኖሚ ሽምድምድነት (ጥገኝነት) ያደበዘዝነውን ዓድዋ ዙሪያ ገባውን የማፍካት እልህ ነው፡፡ ሁለተኛ ኃያላኑ ጦር ሳያዘምቱ እንደ ኢትዮጵያ ያለችን ደሃ አገር በድምፅ አልባ የውጭ ምንዛሪ መጠጣና በማዕቀብ ቀስፈው ለማድፈቅፈቅ፣ ወይም በሌላ ሦስተኛ ሎሌ አገር/አገሮች በኩል ለማመስ እንደማይከብዳቸው በተደጋጋሚ አሳይተውናል፡፡ ሦስተኛ የኢትዮጵያ የህልውና ጥቅም በኢትዮጵያ ካርታ ውስጥ የታጠረ አይደለም፡፡ ጎረቤቶቿ ውስጥ ይገባል፡፡ የጎረቤቶቿም ጥቅም ኢትዮጵያ ውስጥ ይገባል፡፡ በሌላ ገጽ ደግሞ የኢትዮጵያና የጎረቤቶቿ ሉዓላዊ ጥቅም ቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ ድረስ የተዘረጋ ነው፡፡ ይህን ጥቅም ኢትዮጵያም ጎረቤቶቿም በየብቻቸው ሊያሳኩትም ሊያስጠብቁትም አይችሉም፡፡ ይህንን ያልተረዳና ያላገናዘበ ዲፕሎማሲ ከመደናበር ብዙም አይርቅም፡፡
2.2 እየፈካና እየፈጠጠ የመጣው የኢትዮጵያና የጎረቤቶቿ ይህ ክፍለ አኅጉራዊ የህልውና ጥቅም በአገሮቹ የተናጠል ሩጫ የማይሟላና የማይከበር መሆኑ ከታወቀ ሰነባብቷል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያና የቀንዱ አገሮች ቀጣናዊ ጥቅማቸውን ማስከበር በማያስችል የአገር ውስጥና የአገር ለአገር ንቁሪያ ተጣበው ሲትረከረኩ እንዲቆዩ፣ የሚሠራባቸው ደባ ቀጣናቸውን የመቆጣጠር ቡድናዊ ሥሪት ያለበት መሆኑ፣ የቀንዱን አገሮች ድኩምነት ክፉኛ አጋልጧል፡፡ ሱዳን በመሬት አለኝ ሰበብ በልማት አጋሯ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ መክፈቷ በዚሁ ቀጣናዊ ወጥመድ የመጠመዷ ድኩምነት ምስክር ነው፡፡ ለቀጣናዊ ጥቅም ከመቆምና የከበባ ወጥመድን ከመታገል አኳያ፣ የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ምን ያህል ከአፍንጫ ያልራቀ ድህነት ውስጥ ተዘፍቆ አንደቆየ አሁንም አዙሪቱን እንዳልጨረሰ ክፉኛ ተጋልጧል፡፡ ከመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም መንገሥ ጋር እያደጉ የመጡት የመነጠል ትግሎች የዚሁ መገለጫዎች ነበሩ፡፡ የ1983 ዓ.ም. የሻዕቢያና የሕወሓት ‹‹ድል›› ያንን ተከትሎም ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅኝ ገዥዎች ወጥመድ ውስጥ እንደሆኑ ሁለት ‹‹ነፃ›› አገር ነን ማለታቸው ፖለቲካችን ማንንም ከጅብ የማያስጥል ከመሆንም በላይ፣ ቀጣናዊ የህልውና ጥቅሙን ያልተረዳ እንደነበር ራሱ በራሱ ላይ የመሰከረበት ልምድ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የደረሰው፣ ዕጣ ፈንታን ከየብሔር ብሔረሰብ ጋር ያያያዘ የዕይታ መሰባበር (ለኢትዮጵያ መሥራትና ለብሔር መሥራት የሚሻኮቱ ነገሮች መሆን) የባሰ ውድቀት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንኳን ቀጣናዊ ጥቅምን ለማራመድ አቅም ሊኖረው ይቅርና አገራዊ ጥቅምን እንኳን ለማስከበር የሚያስፈልገውን የዕይታ ሥምረት ያጣ (ጎጣጎጥ ውስጥ በመርመጠመጥ የተብሰከሰከ) ሆኖ አረፈው፡፡ ለብሔር/ለጎጥ ማሰብ ለኢትዮጵያ ከማሰብ በልጦ ደመቀ፡፡ የብሔር መገንጠልን ባሻ ጊዜ መከጀል ‹‹በመብት መጠቀም/መብትን ሙሉ ማድረግ›› ሆኖ ተቦተለከለት፡፡ በዚሁ ቅዠታምነቱ የእኛ ፖለቲካ የቅዠቶችና የዕብደቶች ስብስብ መሆኑን ራሱ በራሱ አሳየ፡፡ የውጭ ተንኮል ሳያሻው እንደ አገር ጠንክሮ መቆም እንኳ ሊስተውና መፈረካከስን ‹‹ድልና ጌጡ›› ሊያደርግ እንደሚችል በእነ ኦነግ ሸኔና በሕወሓቶች ወፈፌነት አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ የአርበኝት ኅብረት አንዱ ሁነኛ ተግባር የኦነግ ሸኔና የሕወሓት ፅንፈኝነትን ርዝራዦችን ከማክሰም በላይ፣ ለእነሱ ወፈፌነት ማኅፀን የሆነውን አተያይ አርሞና ቀጣናዊ ጥቅምን ለማስከበር በሚያስችል አተያይ አገርን አጠንክሮ የማፍካት ጉዳይ ነው፡፡ የኦነግ ሸኔንና የሕወሓትን ፅንፈኛ ዕብደት የማጠናቀቁ ሥራም፣ በአተያይ የደረሰብንን መሰባበር የመጠገን ትልቅ ተግባራችን አካል ሆኖ ሲመጣም ከባድ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያነትንና ብሔረሰብነትን ያግባባና አገራዊ ቀጣናዊ ጥቅምን ሊያራምድ የሚያስችል የአተያይ ተሃድሶን ማልማት በራሱ ፅንፈኛነትን ወላጅና አሳዳጊ ያጣ ያደርገዋል፡፡
ፅንፈኝነትን ወላጅና አሳዳጊ በማሳጣት ዓውድ ውስጥ በአገርም በትግራይም ደረጃ የሕዝብ አመኔታ ተስፋና ንቁ ተሳትፎ የተቆሰቆሰበት (በዘመነ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ታይቶ የማይታወቅ) በነፃነት ስሜት የተሞላ የመልካም አስተዳደርና የኑሮ መሻሻል ኮለል ማለት ከጀመረ፣ የመብቶች መከበር ከየትኛውም ፓርቲ ገዥነት ጋር ሳይጣበቅ እንደ ሥርዓት መገንባቱ እርግጥ እየሆነ ከመጣ፣ ጥፋተኞችን የመፋረድ እንቅስቃሴ ከፖለቲካና ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነፃ ከሆነ፣ በፅንፈኞች የተወናበዱ ለውጥ ፈላጊዎችን ለውጡ በተሃድሶ መሳብን ካወቀበት፣ የሕወሓትና የመሰሎቻቸውን የጦርና የዘረፋ አበጋዞችን ግፍ በመዘክዘክ እንቅስቃሴ ውስጥ አባሎቻቸውና ሆድ ይፍጀው ብሎ የቆየ ሕዝብ ራሱ ዋና ተዋናይ ወደ መሆን ይሸጋገራሉ፡፡ ይህ ሆነ ማለት በፈረንጅ አገርና በጎረቤት አገር ያሉ አስወራሪና የፅንፈኛ ቡድኑ ርዝራዝች ትጥቅ ትግል መጀመር ይቅርና ምላስም ይቸግራቸዋል፡፡ ይህን አገራዊ የድል አቅጣጫ በአርበኝነት ኅብረት ተቆናጠን ከግንቦቱ ምርጫም በኋላ ካስቀጠልንና አውሬዎቹ የፈጸሙትን ለኢትዮጵያም ለአፍሪካ ቀንድም ቀበኛ የሆነ ክምር ግፍና ውንብድና በአግባቡ ሰንዶ ለዓለም ማጋለጥ ከተሳካልን ደግሞ የክስመታቸውን ሐውልት አቆምን ማለት ነው፡፡ አሁንም ልድገመው፣ የተባበረ የአርበኝነት ተጋድሏችን አንዱ ሁነኛ ትኩረት፣ የተረጂነትንና የአደግድጎ ኑሮን በሚቀይር የልማት ሙላት ውስጥ ሆነን በኢትዮጵያ ውስጥ ውሎ ያደረውን የፖለቲካ መሀንነትና አስጠቂነት ባህርይ መለወጥ ነው፡፡ በሕወሓትና በኦነግ ሸኔ ርዝራዦችና መሰሎቻቸው ላይ የሚካሄደውም ትግል የዚያ አገራዊ ተልዕኮ አካል እንጂ ሁለመና አይደለም፡፡ እነሱ የፖለቲካ መቃብራቸው ውስጥ ሆነው ካዝረጠረጡን ከእነሱ ይበልጥ እኛ ሞተናል ማለት ነው፡፡
2.3 የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድርና የሱዳንና የኢትዮጵያን የድንበር ጣጣ፣ ኢትዮጵያ ያለ ፖለቲካ ኪሳራ ዕልባት ላይ ለማድረስ ‹‹ትልቁ አቋሟ›› ሁነኛ ጉልበት ይሆናታል፡፡ ‹‹ትልቁ አቋሟ›› ምንድነው?
በኢትዮጵያም ሆነ በተጎራባቾቿ ውስጥ በግፈኛና ከፋፋይ አገዛዝ የደረሰ የመከራ ክምር፣ ድንበር ወደ ማስፋት በመዞርና የበዳይ ተበደልኩ ባይ በመሆን እንደማይፀዳ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ተምራለች፡፡ ከዚያ ዓይነት ራስን በራስ የማታለል ጨዋታ ወጥታ ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ ቁርጠኛ መሆን ተቀዳሚ የጉልበት ምንጭ ነው፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ በውስጥ ውዝግብ ተዳክማለችና በተበዳይነት እየተንጫጫን ግዛት ብናሰፋ፣ የኢትዮጵያን የውስጥ ቀውስ በማባባስ የድርድር ድል አትርፈን ሕዝብን መደለል እንችላለን ወይም መቁረጫ በማይኖረው ጦርነት ወደ ተለመደው ወታደራዊ አገዛዝ ማቆራረጥ እንችላለን ለሚል አሮጌ ሥሌት ማስፊያ ምጣድ ያለ መሆን ጠንካራ ሥነ ልቦናና ኅብረት (መንግሥት፣ ሕዝብ፣ ፖለቲከኞችና ምሁራን አንድ ላይ የገጠሙበት) ይዞ መገኘት ነው፡፡ በሌላ ጎን የጎረቤቶቿን መንግሥታትና ሕዝቦች በአሮጌ ሸርና ግጭት መጫወቻ አለማድረግን ፅኑና መታወቂያ አቋሟ ማድረግ ሌላ የትልቅነት ገጽ ነው፡፡ ይህንን መንታ ኃላፊነት ያወቀ አቋም መያዝ የፅድቅ ፍለጋ ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በክፍለ አኅጉራዊና በአኅጉራዊ ጥቅሟና ኃላፊነቷ ውስጥ አገራዊ ጥቅሟን ብታስተውል ቅንጦት አይሆንባትም፡፡ የኢትዮጵያና የጎረቤቶቿ የጥቅምና የህልውና ዕጣ እርስ በርስ የተያያዘና አብሮ መጎለባበት ያለበት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ህልውናና ሰላም የማትረፍ ጉዳይ ጎረቤቶቿም እንዳይቃወሱ ከማገዝ ጋር የተዛመደ መሆኑን ኢትዮጵያ አጥብቃ ማመን ያሻታል፡፡ እናም ብላ ብላ ምርጫ ካላጣች በቀር፣ ከግጭትና ከጦርነት መንገድ ርቃ የግጭት መንገድ በቀጣናዋም በአኅጉሯም ውስጥ ከሥራ ወጪ እንዲሆን መታገል የማትታማበት ተግባር መሆን አለበት፡፡
ወደዚህ አቋም መድረስን ትክክል የሚያደርግ ከበቂ በላይ የሆነ ልምድ አለ፡፡ ግጭትና ጦርነት ብዙ አቅምን እንደሚያነክት በውስጥም ሆነ ጎረቤት ከጎረቤት ባላት ግንኙነት ኢትዮጵያ በተግባር አይታዋለች፡፡ የጎረቤቶቿ ቀውስ ወደ ራሷም እየፈሰሰ አጎሳቁሏታል፡፡ በራሷ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰት የውስጥ ቀውስም፣ ከጎረቤቶቿ መሀል የጋራ ሰላምንና ህልውናን ያልተረዳ የአጋጣሚ ሌባ እንደሚፈጥር ትናንትናም ዛሬም አይታዋለች፡፡ እናም እንዲህ ያለው አጋጣሚ ወለድ መልቲነት ዕድል እያገኘ ቀጣናውን እንዳይበጠብጥ ከጎቤቶቿ ጋር ያላት አጋርነት ይበልጥ የኢኮኖሚ ልማት ሥጋ እንዲኖረው መሥራት፣ በጎረቤት ቀውስ ልነግድ ባይ መንግሥታዊ መልቲነት በቀጣናው ውስጥ ሲነሳም፣ በምትችለው ሰላማዊ መንገድ ሁሉ ከጥፋት እንዲርቅ መጣጣር ትልቅ ኃላፊነቷም ጥቅሟም ነው፡፡ በዚሁ የምሥራቅ አፍሪካን ሰላምና ልማት ጥቅሜ ባለ አቋም ውስጥ፣ የድንበር ጉዳዮችና የተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም መግባባት እየተደረሰባቸው ወደ ጋራ የልማት ሠፈርነት እንዲቀየሩ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን፣ ከወዲሁ ጎረቤቶቿ ማወቃቸውም መቀራረብንና መተማመንን ይጠቅማል፡፡
ቀጣናዊው የጋራ ልማት ትቅቅፍ ከወዲሁ መፍካት መጀመሩ በራሱ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር ላለብን ጉዳይም መልካም ጥቅም ይሰጣል፡፡ ከሱዳን ጋር ኢትዮጵያ ያላትን የድንብር ጉዳይም ሆነ በህዳሴ ግድብ ላይ የተጀመረውን ድርድር የምትረዳውና ዕልባት እንዲያገኝ የምትጥረው በቀጣናዊ የመለማማት የጋራ ጥቅም ውስጥ እያሰበች መሆኑን ይመሰክርላታል፡፡ ደባና ወታደርዊ ጥቃት ሰንዛሪንም የተሰነዘረበትንም ይጎዳል፡፡ የኢትዮጵያ ሰላም ማጣት ለግብፅና ለሱዳን ሲሳይ እንደማይሆናቸው ሁሉ የሱዳንና የግብፅ የውኃ መቸገር ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማትን አያንቆረቁርላትም፡፡ ደባና የልማት እጥረትን ተገን አድርጎ እንቦጭ አረም አስዋን ግድብ ድረስ ተሻግሮ የልማት ፀር ሊሆን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ የተደጋገፈ ልማት ቅውስውሱ ቢወጣ የበረሃነት መስፋፋትና በሥርዓት አልባ አጠቃቀም የዓባይ መጋቢ ወንዞች ደርቀው ዓባይ ለማንም የማይፈይድ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ያላት የፍትሐዊ ድርድር ማዕዘንም የብቻ ጥቅሟን ብቻ ያስተዋለ ሳይሆን፣ የሱዳንንም የግብፅንም ሕዝብ መጠቀም ዘላቂ ጥቅሜ ብሎ የሚያስብ ነው፡፡ ሱዳን ጦር አዝምታ የገፋችውን ድንበር በወታደራዊ መንገድ ለማስተካከል የማትፈልገውም፣ ወታደራዊ መንገድ ቀጣናውንም ሆነ ሁለቱን አገሮች እንደማይበጅ ስለምታምን ነው፡፡ ጦርነት የሱዳንንም የኢትዮጵያንም የኢኮኖሚ ችግሮች ያብሳል እንጂ አያቃልልም፡፡ የሁለቱንም አገሮች ወደ ዴሞክራሲ የመሻገር ጉዞ ያደናቅፋል እንጂ አያፋጥንም፡፡ የድንበሩ ውዝግብ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ኢትየጵያ እየለመነች ጦርነትን ሙጥኝ ማለት የሁለቱንም አገሮች የጋራ ጥቅምና የቀጣናውን ሰላም የሚበጠብጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን መሳይ አቋሟን የጎረቤቶቿ መንግሥታትና ሕዝቦች፣ የሱዳንና የግብፅ ሕዝቦች፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የዓለም ታላላቅ አገሮች ሁሉ በቅጡ እንዲያውቁላት ማድረግ ከቻለች ለራሷም ለቀጣናውም የሚኖረው አንድምታ ትልቅ ነው፡፡
2.4 ‹‹ኅብረት ለኢትዮጵያ›› (ዩኒቲ ፎር ኢትዮጵያ) በሚል መጠሪያ የሚታወቀውና በቅርብ የተፈጠረው እንቅስቃሴ ዓላማውን አስፍቶ ወይም እሱን ያካተተና ባለብዙ ግብረ ኃይል ስብስብ ተፈጥሮ፣ ከላይ የተነሱት ተልዕኮዎች መሞሸር እንዳለባቸውም ይሰማኛል፡፡ የቀጣናው ሰላምና ትግግዝ የኢትዮጵያ ጥቅም ብቻ እንዳለመሆኑም፣ ከቀይ ባህር እስከ ህንድ ውቅያኖስ አፍሪካዊ ደጅ ድረስ ያስተሳሰረ የፖለቲካ ልሂቃን የሰላም እንቅስቃሴ ማደራጀትም ወቅታዊ ነው፡፡ የሰሜን አፍሪካ ጥቅም ከምሥራቅ አፍሪካ፣ ከመላው አፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ ጥቅም ጋር ያለውን ተደጋጋፊነት እየመረመሩ ማፍካት፣ ከዚያም አኳያ በጠባብ ጥቅም የሚሸረቡ ሴራዎችና ግጭቶችን ጠንቀኝነት ማጋለጥ፣ የትኞቹም ውዝግቦች በሽምግልናና በድርድር እንዲፈቱ መሥራት፣ ስደተኛ አራቢና የፖለቲካ አለመረጋጋት አመንጪ ችግሮች እንዲቃለሉ ትልሞችና ምክሮች እያፈለቁ ተሰሚነት እንዲያገኙ መጣር፣ በቀጥተኛና በእጅ አዙር ውጊያዎች መጠቃቃት እንዲመክንና የልማት ትግግዝ (የወንጀለኛ መሸሸጊያ/ተገን አለመሆንንና የአካባቢ ሰላምን በጋራ መንከባከብን ጨምሮ) የቀጣናው መታወቂያ እንዲሆን ዒላማ አድርጎ መሥራት የእንቅስቃሴው ዋና ጉዳዮች ይመስሉኛል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡