Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ውጤታማ ለመሆን የተቋማትን አሠራር ማሻሻል ያስፈልጋል ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርቡ መተግበር የጀመረው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመተግበር በኢትዮጵያ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ተቋማትን አሠራር ማሻሻል እንደሚገባ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ በንግድ ስምምነቱ ዙሪያ በተሰናዳ የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት፣ ስምምነቱ ውጤት እንዲኖረው ከሁለት እጅ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ኢመደበኛ በመሆኑ ወደ መደበኛ ማምጣት ሌላው ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መገንባት፣ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን መቃኘት፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል፣ የተረጋጋ ዋጋ እንዲኖር ማድረግና ለኢንቨስተሮች በቂ ዋስትና መስጠት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡  

የንግድ ስምምነቱን ውጤታማ ለማድረግ የጥሬ ዕቃዎች ጥራትና እጥረት፣ የማምረቻ ዋጋ ማሻቀብ፣ የንግድ ማሳለጫ አገልግሎት ውጤታማ አለመሆን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና፣ የኃይል መቆራረጥ፣ የተጣጣመ የንግድ ፖሊሲ አለመኖር ሌላኛዎቹ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነት የሚፈታተኑ ናቸውና እነዚህ ጉዳዮች ቸል መባል እንደሌለባቸው አመልክተዋል፡፡

‹‹የአገሪቱ የምርት አቅርቦት ማነቆ በራሱ ሊፈታ ይገባል ብለን እናምናለን›› ያሉት ወ/ሮ መሰንበት፣ በአገሪቱ ንግድን ለማከናወን ያለው ሁኔታ መሻሻል መቻል እንደሚኖርበትም ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ስምምነት ሲታይ በአጠቃላይ የግሉ ዘርፍ አቅሙ ሊጠናከር እንደሚገባና መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት በዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በአጀንዳ 2063 ላይ ልዩ ቦታ ተሰጥቶት የተዋሃደች፣ የበለፀገች ሰላማዊ አፍሪካን የመፍጠር ዓላማ ያላው የፓን አፍሪካ ውጥንና ራዕይን የገነባ እንደሆነ እንደሚገነዘቡ የጠቀሱት ወ/ሮ መሰንበት፣ ይህም የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት የሚያስፋፋ፣ በሰዎች ነፃ እንቅስቃሴ የሚታገዝ፣ የዕቃዎችና አገልግሎቶች ግብይትን የሚፈጥር መሆኑን፣ ሆኖም በኢትዮጵያ ደረጃ ውጤት እንዲመጣ አሁንም ብዙ መሠራት ይገባል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን በማስመልከት በዕለቱ በዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር)፣የቀረበ ጽሑፍ የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የታሪፍ ቅነሳ ስምምነት፣ በንግድ ሥርዓት ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ይፈትሻል፡፡

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ የንግድ መፈጠርን ዕውን በማድረግ ረገድ የተወሰነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የንግድ ምልከታዎቹ የሚያሳዩ ሲሆን፣ የንግድ ስብጥርን በመፍጠር ረገድ ጠንካራ ዕድሎች መኖራቸውን ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ይገልጻሉ፡፡  

ስምምነቱ አፍሪካ ከአኅጉሪቱ ውጪ የምታደርገውን የወጪ ንግድ አሁን ከሚገኝበት 72.7 ቢሊዮን ዶላር አማካይ ዓመታዊ መጠን፣ በ19 በመቶ በማሳደግ የ13.7 የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ እንደሚኖረው የሚጠቁም ስለመሆኑ በጉዳዩ ዙሪያ የተጠኑ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ አስረድተዋል፡፡  

የንግድ ሥርዓት ምልከታ ውጤቱ እንደሚያሳየው ደግሞ፣ ይህ ታሳቢ ውጤት በጥንቃቄ ሊፈጸም የሚያስፈልገው መሆኑን ነው፡፡

ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችና የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ ስኬታማነት ለታዳጊ ኢንዱስትሪዎች አኅጉራዊ ጥበቃና አኅጉራዊ ተራማጅነትን መሠረት ያደረገ የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ በመፍጠር ሊጣመሩ የሚገባቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለወጪ ንግድ በማቅረብ ረገድ ስምምነቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ በአኅጉሩ የሚስተዋሉት ደካማ የተወዳዳሪነት አቅምና ውስን የንግድ ተመጋጋቢነት ሊገድቡት የሚችሉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አኅጉሪቱን በስፋት በዳሰሳው ምልክታ መሠረት፣ በወጪ ንግድ ላይ የሚደረግ የአሥር በመቶ የዋጋ ቅናሽ የአኅጉሪቱን የወጪ ንግድ መጠን በ21.67 በመቶ ማሳደግ እንደሚችልም የፕሮፌሰር ዓማየሁ ጽሑፍ ያመለክታል፡፡

ይህ አኃዝ የአኅጉራዊውን ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ተከትሎ የሚደረግ የታሪፍ ቅነሳ ንግድን በመፍጠር ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት ከተመሠረተ በኋላ የተመሠረተው ይህ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና፣ የዓለማችን አንደኛው ግዙፍ ቀጣና ነው ሊባል እንደሚችል የገለጹት ወ/ሮ መሰንበት ደግሞ፣ አሁን ያለው 1.2 ቢሊዮን የአፍሪካ ሕዝብ ቁጥር በ2050 ወደ 2.5 ቢሊዮን እንደሚያድግ ስለሚጠበቅ ግዙፍ ዕድሎችና ገበያን ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ወገኖች በተለይም የግሉ ዘርፍ ስለ አኅጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ ያላቸው ዕውቀት ሰፊ ሊባል የሚችል ያለመሆኑን፣ በስምምነቱና በአተገባበሩ ዙሪያ ሁሉም የኢኮኖሚ አጋር አካላትና ተዋንያን ሊሳተፉበትና ሊገነዘቡት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

እንደ ንግድ ምክር ቤታቸው እምነት ከነፃ ንግድ ቀጣናው የሚገኙ ዕድሎች እንዳሉ የሚረዱ መሆኑን በመግለጽም፣ ለኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች አስተማማኝና ሰፊ የገበያ ዕድሎችን ይፈጥራል ብለው እንደሚያስቡ ጠቁመዋል፡፡ 

አማራጭ ምርቶች በተሻለ ዋጋ እንዲገኙ ያደርጋል የሚል እምነት ያላቸው ወ/ሮ መሰንበት፣ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንደሚጨምርና ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረትም ቢሆን የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባር ላይ በማዋል እ.ኤ.አ. በ2022/23 ላይ በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚደረገውን የንግድ ልውውጥ አሁን ካለው በ60 በመቶ ከፍ ያደርጋል ሲል ግምቱን ያስቀመጠ ቢሆንም፣ ይህ ሁሉ የሚከናወነው አልጋ በአልጋ በሆነ ከባቢ እንዳልሆነ ይታመናል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ክልላዊ የንግድ ትስስር በተለይ የታሪፍ መቀነስን የሚያስከትል፣ የፖሊሲ ውህደትና የሕጎች መጣጣምን የሚጠይቅ መሆኑ ሥራ የሚጠይቅ ሲሆን፣ በኢንዱስትሪዎች ላይ የውድድር ጫና ማስከተሉ ሌላው በተግዳሮትነት የሚነሳ ጉዳይ መሆኑን ያስረዱት ወ/ሮ መሰንበት፣ በእነዚህ ዙሪያ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ተገቢነት አለው ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ50 የአፍሪካ አገሮች በላይ ስምምነቱ ይጠቅመናል ብለው ቢፈርሙም፣ የአፍሪካ አገሮች በእኩል የዕድገት ደረጃ ላይ አለመሆናቸው፣ ተወዳዳሪነቱ ዋነኛ ተግዳሮት ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ አቅም ሊጠናከርና መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ስምምነቱ በመንግሥታት መካከል ቢሆንም፣ የድርድሩ ውጤት የሚያርፈውና ተግባራዊ የሚያደርገው የንግዱ ማኅበረሰብ ስለሆነ፣ የግሉ ዘርፍ በስምምነቱ አተገባበር ላይ አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች