Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹‹እኛም የዋጋ ግሽበቱ ተባባሪዎች ነን››

ከሰሞኑ የገበያ ዋጋ በእጅጉ ካስገረሙኝ ውስጥ የምግብ ቅቤ፣ ዕንቁላልና ካሮት ይገኙበታል፡፡ የዕንቁላል ዋጋ ጭማሪ አስገራሚ የሚሆንብኝ እንቁላልን እንኳን በበቂ ሁኔታ አምርቶ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም እንዴት እናጣለን ከሚል ጭምር ነው፡፡ ሥራ ጠፋ በሚባልበት አገር እንዲህ ያለውን ሥራ ንቆ ዋጋው ተወደደ እያልን ስንናገር አንዳንዴ ለኑሮ ውድነቱ እኛው ራሳችንም ተባባሪዎች ነን እንድል አስገድዶኛል፡፡ በዚህ ሳምንት አዘውትሬ ዕንቁላል ከምገዛበት መደብር ስሄድ ከሳምንት በፊት አምስት ብር ከሃምሳና ስድስት ብር የገዛሁትን አንድ ‹‹የሐበሻ ዕንቁላል›› በለመድኩት ዋጋ መግዛት አለመቻሌ አንዱ ምክንያትም ይኼው በቀላሉ ገዝተን ልንጠቀምባቸው የሚችሉ ምርቶችን አምርቶ ለገበያ አለማቅረባችን ነው፡፡ በዕለቱ የተጠየቅሁት ዋጋም 7 ብር ከ50 ሳንቲም ነበር፡፡

 የዋጋ ጭማሪን ዕድገት በደንብ ካጤንነው አስደንጋጭ የሚባል ሆኗል፡፡ በዕንቁላል ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በአብዛኛው የሚኖረው በዓውደ ዓመት ዋዜማ ሲሆን፣ እሱም ቢሆን ከበዓሉ በኋላ ወደ ነበረበት ይመለሳል፡፡

አሁን ላይ ግን በአንድ ዕንቁላል ላይ የተደረገው ጭማሪ ከ1.50 እስከ 2.00 ብር ነው፡፡ ነገሩን በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቀመር ካሠላነው የአንድ ዕንቁላል ዋጋ ሰሞናዊ ጭማሪ ከ30 በመቶ በላይ ነው፡፡ ስለዚህ ዕንቁላል ታሪካዊ የዋጋ ጭማሪ እንድታደርግ ተወስኖባታል ማለት ነው፡፡ ሌላው ምሳሌዬ ካሮት ነው፡፡ ከሰሞኑ ወደ ገበያ ወጥታ በፀሐዩም በገበያውም ዋጋ ግላ ያገኘኋት ወዳጄ፣ አንድ ኪሎ ካሮት 50 ብር መግባቱን ነገረችኝ፡፡ ካሮት 50 ብር? አንዳንዴ በሰሞኑ ገበያ የተማረረ ሁሉ እያጋነነ ይሆናል ብዬ ነገሩን ለማረጋገጥ ወደ አንድ ገበያ ሥፍራ ሄጄ የተባለውን አረጋገጥኩ፡፡ እንደየሥፍራው ከ35 ብር እስከ 40 ብር የሚሸጥበት ሁኔታ መኖሩንም መረጃ አግኝቻለሁ፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንድ ኪሎ ካሮት 20 ብር መሸጡን አውቅ ነበርና በካሮት ላይ የተደረገው ጭማሪ ከዕጥፍም በላይ ወደ ላይ ያሻቀበ መሆኑን አረጋገጠልኝ፡፡

የቅቤ ዋጋንም በመሳሳይ ተመለከትኩ፡፡ ከአንድ ወር በፊት ተወደደ ተብሎ ከ280 እስከ 300 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ለጋ ቅቤ በዚህ ሳምንት 380 ብር ደርሷል፡፡ የአንድ መቶ ብር ጭማሪ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉት የዋጋ ጭማሪዎች ግን ጤናማ አለመሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ በሌሎች ምርቶች እየታየ ያለውን ጭማሪ እንተውና በእነዚህ ምርቶች ላይ የታየው ጭማሪ ያላግባብ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለምን በሚል የሚያስቆጭ ስለሆነ ነው፡፡ ደጋግመን እንደምንለውም በአንድ አጋጣሚ ዋጋ የመቆለል የቆየ ልምድ አሁን ላይ ብሶ መታየቱን ነው፡፡ ግርድፍ በሆነ ሥሌት በቅርቡ የተጨመረው የነዳጅ ዋጋ በመቶ ሲሠላ 20 በመቶ አካባቢ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡

ይህ የነዳጅ ጭማሪ ማለት በዝርዝር ሲታይ በገበያ ውስጥ ሊኖር የሚችለው የዋጋ ለውጥ በመቶኛ እንደተሠላው አይደለም፡፡ ቢበዛ ከሰባት በመቶ ያነሰ ጭማሪ ሊያስከትል ቢችል ነው፡፡ ይሁንና በርካታ ምርቶች ላይ የምናየው የዋጋ ጭማሪ እጅግ ተጋንኖ በመቶና በሁለት በመቶ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ምርቶች የነዳጅ ጭማሪው ሊያስከትልባቸው የሚችለው ተፅዕኖ አነስተኛ መሆኑ እየታወቀ፣ ነዳጅ ጭማሪ ሰበብ ተደርጎ ዋጋቸው እንዲሰቀል ሆኗል፡፡ ይህ በግልጽ የሚታይ ሲሆን ለምን እንዲህ አደረጋችሁ ብሎ የሚጠይቅ መጥፋቱም ሸማቹን እያማረረ ነው፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን የነዳጅ ጭማሪ ከታሰበበት ጊዜ ጀምሮ ምርቶቹን በመሸሸግ፣ እጥረት በመፍጠር ዋጋን ለመስቀል የሚደረጉ ጥረቶችን እያየን ቆይተን፣ በተጨባጭም ተተግብሯል፡፡ ለዚህ የምግብ ዘይት ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ሌትር ዘይት ተሸሽጎ ተገኘ በተባለ ማግሥት፣ እንዲሁም ይኼው ዘይት በሸማቾች በኩል ተከፋፈለ በሚባልበት ወቅት፣ አሁንም በገበያው ውስጥ የምግብ ዘይት እጥረት እየታየ መሆኑ የግብይት ሥርዓቱን ብልሽት በሚገባ ያሳያል፡፡

ከሰሞኑ በብዙ መደብሮች መደርደሪያዎች ላይ የምግብ ዘይት አይታይም፡፡ በአንዴ ከመደብሩ ሼልፎች ላይ የጠፋበት ምክንያት ሸማች እጅ ደርሰው ሳይሆን፣ ዋጋ ይጨምራል በሚል ሰበብ እኔም የድርሻዬን ያሉ ቸርቻሪዎች ሸሸገውት ስለመሆኑ ይታመናል፡፡ ስለዚህ በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሰበብ ገበያው የበለጠ እየተበላሸ ነው፡፡ በተለይ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ብዙም የማይመለከታቸው እዚሁ የሚመረቱ ምርቶች ዋጋ ማሻቀብ ጉዳይ ግን አደገኛ የሚባል ነው፡፡ የዋጋ ዕድገቱን ለመከላከል ይኼ ነው የሚባል ሥራ ባለመኖሩም ችግሩን አብሶታል ማለት ይቻላል፡፡

እንደ ካሮትና ዕንቁላሉ ሁሉ በቅርብ ርቀት ወደ ከተማ የሚገቡ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ለውጥ በተለየ እንድንመለከት የሚያደርገን በምርቶቹ ላይ የሚታየው ዋጋ ለውጥ የቱንም ያህል ቢያድግ ፈፅሞ አሁን እየተሸጠባቸው ባለ ዋጋ ሸማቾቹ መግዛት የማይገባቸው በመሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን ትንሹንም ትልቁንም ምርትና ሸቀጣ ሸቀጥ እጥረት አለ እየተባለ የሚደረገው የዋጋ ዕድገት ስግብግብ የምንላቸው ነጋዴዎች ላይ ብቻ ጣት የምንቀስርበት ያለመሆኑን ነው፡፡ ለማምረት ብዙም የውጭ ምንዛሪ የማይፈልጉ ምርቶችን በቀላሉ አምርቶ ለገበያና ለራስም መጠቀም ሲቻል፣ በምርት እጥረት ሰበብ ዋጋቸው አልቀመስ ሲል ማየት ውድቀትን ያሳያል፡፡

ቅቤንም ካየን በቀንድ ከብት ሀብቷ አንደኛ ነች በምትባል አገር የወተትም፣ የቅቤም የአቅርቦት እጥረት ሲነሳና ዋጋው እንዳሻው ሲወጣ መመልከት ችግሩ የእኛም ነው ብለን እንድንወስድ ያደርገናል፡፡ ሁሌም ጠባቂ የመሆን ልማድ በእጅጉ የተዛመደን በመሆኑ የምንቸገር መሆናችንንም መቀበል አለብን፡፡ ሸማቾች ሁሉንም ነገር በመሸመት የምንዘልቅ ከሆነ አሁንም የበለጠ የዋጋ ንረት እየገጠመን ሊቀጥል ይችላል፡፡

አንዳንዴ የከተማ ግብርና እየተባለ ሲለፈፍ ትርጉሙ ከፍ ያለ ስለመሆኑ የምንገነዘበው እንዲህ ባለ ወቅት ነው፡፡ በራስ ግቢ ያለን ቦታ ወይም በአካባቢ ያለምንም ሥራ የተቀመጠን ቦታ በመጠቀም ዛሬ በአንድ ኪሎ 50 ብር የተጠየቀበትን ካሮትና መሰል የጓሮ አትክልቶችን በማልማት የመጠቀም ልምዱ ቢዳብር፣ የከተማ ግብርና የሚለውን ሐሳብ በትክክል መተግበር ቢቻል የጭልፊት ነጋዴዎችና ደላሎች ሲሳይ ባልሆንን ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡

ዋናው ነገር ግን ካሮት 50 ብር ገባ፣ ሽንኩርት ይህንን ያህል ደረሰ፣ ዕንቁላልና ቅቤ ዋጋቸው አልቀመስ አለ የሚለው ምሬታችን የዛሬ ብቻ ሳይሆን፣ የቆየና የሰነበተ ከመሆኑ አንፃር ድጋሚ ችግሩ እንዳይፈጠር ምን አደረግን? የሚለው ነው፡፡

ኢትዮጵያን የሚያህል በቀላሉ ሊለማ የሚችልና ፆም ያደረ መሬት ባላት አገር፣ ሽንኩርት በውጭ ምንዛሪ እያስመጣን ስንጠቀም መስማት የበለጠ የሚያስተዛዝበን ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ስለዚህ እኛው በቀላሉ የምናመርተውን ምርት አለማምረት በራሱ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ሽንኩርት አጠረ ሲባል ዶላር እንጠልጥሎ ወደ ሱዳን መሮጥ መጀመራችን የቆጨው በመጥፋቱ፣ ይኼው ሽንኩርት ተወደደ ምርት ጠፋ ሲባል ይሰማል፡፡ ነገም ካሮትና ዕንቁላል እጥረት ስለበረታ ተብሎ ከውጭ ሊወጣ ነው?

ግብርና ወዲህም ሥራ ፈጠራ ወዲህም ኢኮኖሚ ነው ብሎ በገበያ ውስጥ እጥረት የተፈጠረባቸው ምርቶች ላይ መረባረብና ቀጣይነት ያለው ሥራ መተግበር ያስፈልጋል፡፡ አሁን በስንዴና በዘይት ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ ጥሩ ምስክር ሊሆን ይችላልና በራሳችን ስንፍና እየከፈልን ያለውንም ዋጋ ማሰብ መልካም ነው፡፡       

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት