ዌንስተን ቸርችል (The Winston S Churchill ) የተባለችው የአሜሪካ የጦር መርከብ በሱዳን ወደብ ተገኝታለች። የጦር መርከቧ ፀረ ሚሳኤል አስወንጫፊ (Guided missile destroyer) ስትሆን ለአየር እና የባህር ውጊያዎች በዋናነት ጥቅም ላይ እንደምትውል እና የምድር ለምድር ውጊያዎችን ለማድርግም የታጠቀች መሆኗን የአሜሪካ የባህር ኃይል መረጃ ያመለክታል።
የጦር መርከቧ ወደ ሱዳን ወደብ በጉዞ ላይ በነበረችበት ወቅት በቀይ ባህር አካባቢ የባህር ደህንነት ቅኝት ያደረገች እንደሆነ እና እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 11 እና 12 ቀኖች ደግሞ ሁለት ዜግነት የሌላቸው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ የጫኑ መርከቦችን በሶማሊያ ባህር ላይ በቁጥጥር ስር ማዋሏ ተገልጿል።
ዋንስተን ቸርችል በሚል ስያሜ የምትጠራው ግዙፏ የአሜሪካ የባህር ኃይል መርከብ ወደ ሱዳን ወደብ ከመድረሷ ከአራት ከቀናት በፊት ካርሰን ሲቲ ( Carson City) የተባለችው ሌላዋ የአሜሪካ ባህር ኃይል የሎጀስቲክስ (የጦር መሳሪያዎች ፣ ተዋጊ ጀልባዎች እና ሌሎች ስንቆች ) አጓጓዥ መርከብ በዚሁ የሱዳን ወደብ መገኘቷንም የአሜሪካ የባህር ኃይል መረጃ ያመለክታል።
የጦር መርከቧ በሱዳን ወደብ የመገኘቷ ዋና ዓላማ በአሜሪካ እና በሱዳን የባህር ኃይሎች መካከል አዲስ ወታደራዊ ትብብር ለመፍጠር እና አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላትን ብሔራዊ የደህንነት ፍላጎት ለማጠናከር ፤ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና መረጋጋትን ለመፍጠር እና ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር እንቅስቃሴን ለማረጋገጥ እንደሆነ በአሜሪካ የባህር ኃይል የአፍሪካ የባህር ቀጠና ዳይሬክተር የሆኑት ሬር አድሚራል ማይክል ቤዝ ተናግረዋል።