Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአማራ ክልል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ክስ መሠረተ ቢስ ነው አለ

የአማራ ክልል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ክስ መሠረተ ቢስ ነው አለ

ቀን:

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰሞኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጡትን መግለጫ መሠረተ ቢስ ሲል አስታወቀ፡፡  

የአማራ ብሔራዊ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፣ የአማራ ክልል በሕውሓት የተቃጣበትን የህልውና አደጋ በኃይል መቀልበሱ ሊያስመሠግነው ሲገባ፣ በትግራይ ክልል ልዩ ኃይል አሰማርቷል ማለት ኢፍትሐዊ ብቻ ሳይሆን ግልጽ አድሏዊነትና ኢምክንያታዊ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትግራይ ክልል በተለያዩ አካላት የተከሰተው ሞት፣ መፈናቀል፣ ፆታዊ ጥቃቶችና ሌሎች ከፍተኛ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች  የአሜሪካ መንግሥትን እንዳሳሰበው በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡ የኤርትራ ሠራዊትና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ከትግራይ ክልል በፍጥነት የመውጣታቸው ጉዳይ የመጀመርያው መፍትሔ መሆን አለበት ሲሉም አስታውቀዋል፡፡  

የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ግን፣ ‹‹ዓለም እንዲያውቅልን የምንፈልገው ነገር ቢኖር የአማራ ክልል ትግራይ ክልል ውስጥ ያስገባውና ያስቀመጠው የልዩ ኃይል ሠራዊት የለም፤›› ብለዋል፡፡ ከሰሞኑ በአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን የተላለፈው ውንጀላም በማስረጃ ያልተደገፈ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ውጤት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳምንቱ መጀመርያ እንደስታወቀው፣ መንግሥት ክልሉን በማረጋጋት ለሴቶችና ለሕፃናት ቅድሚያ በመስጠት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን በተመለከተ በተሻለ መንገድ እየሠራ ነው፡፡ ‹‹በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብሊንከን የወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የገባና አግባብነት የሌለው ነው፤›› ሲል አስታውቋል፡፡

በተለይ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ጠቅሶ በአሜሪካ መንግሥት የተገለጸው መግለጫ አሳዛኝ እንደሆነ ያስታወቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር ይህ ዓይነቱን ጉዳይ ለኢትዮጵያ መንግሥት ሊተው እንደሚገባ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልልን በማስመልከት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ከወልቃይትና ከራያ ጋር ተያይዞም ከሆነ ‹‹አካባቢዎቹ በየትኛውም የታሪክ ወቅት የትግራይ ክልል ሆነው አያውቁም፤›› ያሉት አቶ ግዛቸው፣ ‹‹ከዚህ በኋላም የሚሆነው ከዚህ የተለየ አይሆንም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከላይ የተገለጹት አካባቢዎች ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ከሥልጣን የተወገደው የሕወሓት ኃይል ላለፉት 30 ዓመታት ሕዝቡን በማስገደድ የሥቃይ ዘመን እንዲያሳልፍ ሲያደርግ ቆይቷል ያሉት አቶ ግዛቸው፣ ‹‹ይሁን እንጂ ለነፃነት፣ ለፍትሕ፣ እንዲሁም ለማንነት በተደረገ ትግል ሕውሓት አክትሞለት ሕዝቡ ነፃነቱን አውጇል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...