የኢትዮጵያ መንግሥት ከፕራይቬታይዜሽን ጋር ተያይዞ ‹‹ለኢትዮ ቴሌኮም በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እያደረገለት ነው›› ተብሎ የወጣው መረጃ የተሳሰተ ዕይታ ነው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር የሆኑት ኦስማኔ ዲዮን፣ መንግሥት ለኢትዮ ቴሌኮም የሚያደርገውን ልዩ ድጋፍ እንዲያቆምና አዲስ ወደ ገበያው ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁት የቴሌኮም ድርጅቶች ጋር እኩል ተወዳዳሪ መሆን እንዳለባቸው መግለጻቸውን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ኢዮብ (ዶ/ር) እንዳስረዱት፣ የዓለም ባንክን ጨምሮ የተለያዩ የቴሌኮም ድርጅቶች፣ ‹‹ለኢትዮ ቴሌኮም ልየ ድጋፍ ተደረገ›› በሚል እየገለጹ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ገለልተኛና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሪፎርም ሥራና ሰፊ ውድድር እያካሄደ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ለምን የግል የቴሌኮም ማማ (Tower) ዓልሚዎችን ከለከላችሁ በሚል የሚነሳው ቅሬታ ምክንያታዊ አይደለም፣ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብት ያወጣንበት የቴሌኮም መሠረተ ልማት እንዲባክን መፍቀድ የለብንም፤›› ብለዋል ኢዮብ (ዶ/ር)፡፡
በመሆኑም የተገነባውን የኢትዮ ቴሌኮም መሠረተ ልማት እንዲጠቀሙ ነግረናቸዋል፡፡ አዲሶቹ ካምፓኒዎች ወደ ተግባር ሲገቡበት ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ይረዳሉ ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ያለውን የመሠረተ ልማት አዲስ ለሚገቡት ኩባንያዎች በመከራየት፣ ከ1.6 እስከ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ እንዳለው ተቋሙ ቀደም ብሎ አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡
‹‹ከዚህ በተለየ መንግሥት ሜዳውን ክፍት ከማድረግና ከማስተካከል ባለፈ፣ አንዱን የመጥቀም ሥራ አልሠራም፣ አይሠራምም›› በማለት ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ዓለም አቀፍና ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ የመገንባት ዕቅድ እንዳለውና ሥራውም በጥንቃቄ እየተመራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የጨረታ ሒደቶቹ የተወዳዳሪዎችን ነፃነት ለመጠበቅ በሚል ምንም ዓይነት ጥያቄ ቢኖራቸው ከፖሊሲ አውጪዎች በተለይም ብሔራዊ ባንክ፣ ገንዘብ ሚኒስቴርና የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ጋር በቀጥታ እየተገናኙ እንዲወያዩ ሲደረግ እንደቆየ አክለው ተናግረዋል፡፡
በዚህም በዚህ ሳምንት የተሻሻለውን የጨረታ ሰነድ እንደሚወስዱና የጨረታ ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የጨረታ ሒደቱ ግልጽ በሆነ መልኩ እየተከናወነ ሲሆን፣ ውድድርና ፉክክር የታየበት እንደሆነ ኢዮብ (ዶ/ር) አክለው ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የሚፈልገውን የጨረታ ዋጋ ካገኘ እንደሚቀጥልና ነገር ግን በተሰጠው መልኩ ካላገኘ እንደገና እንደሚታይ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
በውድድር ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁት ሁለቱ የቴሌኮም ካምፓኒዎች ከመጋቢት 22 በኋላ ይታወቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡