አቶ በቀለ ገርባ ዋና ዓቃቤ ሕጉን በሕግ እጠይቃለሁ አሉ
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት 3፡30 ሰዓት አካባቢ ከተገደለው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ጋር በተያያዘ፣ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ክስ የተመሠረተባቸው እነ አቶ በቀለ ገርባ በረሃብ አድማ ምክንያት በመታመማቸውና የእምነት ክህደት ቃል መስጠት እንደማይችሉ በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፍርድ ቤት በመናራቸው ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕገ መንግሥት ጥሰትና ሽብርተኝነት ወንጀሎች ችሎት፣ የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ ሃምዛ አዳነና አቶ ሸምሰዲን ጠሃን ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች (በሌሉበት ክሳቸው ከሚታየው ውጪ ያሉት) ቀርበው ነበር፡፡
አቶ በቀለና አቶ ሃምዛ ግራና ቀኝ ተደግፈው ስለቀረቡና ችሎት ውስጥ ከገቡም በኋላ ችለው መቀመጥ ባለመቻላቸው አብረዋቸው ከተከሰሱ ግለሰቦች ላይ ተደግፈው ለመቀመጥ ተደርገዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንደተሰየመ ችሎቱን ከመጀመሩ በፊት ስለጤንነታቸውና ሕክምና ስለማግኘትና አለማግኘታቸው ጠይቋል፡፡
ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የተከሳሾቹ ጠበቆች ሲሆኑ፣ ጥር 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ተከሳሾች ሕክምና እንዲሰጡ ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሰው፣ በወቅቱ ታመው የነበሩት አቶ በቀለ ብቻ የነበሩ ቢሆንም፣ አሁን ግን አቶ ጃዋርና አቶ ሃምዛም መታመማቸውን ተናግረው፣ ሕክምናውን በሚመለከት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንደከለከላቸው አቶ በቀለ እንደነገሯቸው አስረድተዋል፡፡ ክልከላውም የደረሳቸው ወደ ሕክምና ቦታ እየሄዱ ባለበት ወቅት መንገድ ላይ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታልፎ ደንበኞቻቸው ከዚያና ከዚህ በተላከ ደብዳቤ ሕክምና ሳያገኙ የከፋ ጉዳት ቢርስባቸው ፀፀቱን እንደማይችሉትም ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡
ደንበኞቻቸው ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም. የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ በረሃብ አድማ ላይ ስለነበሩና ስለደከሙ ባለመቻላቸው ለየካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. መቀጠራቸውን በማስታወስ፣ ዛሬ ደግሞ (የካቲት 22 ቀን 23013 ዓ.ም.) አቶ ጃዋር፣ አቶ ሃምዛና አቶ በቀለ የረሃብ አድማውን ከጀመሩ 33 ቀናት እንደሆናቸው አስረድተው፣ ቀሪዎቹ ተከሳሾች የረሃብ አድማውን ካቆሙ ገና 11 ቀናቸው በመሆኑ፣ በማገገም ላይ መሆናቸውንና በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነው የእምነት ክህደት ቃል መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ የሚናገረው እንዳለው ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ሲፈቀድለት እንዳስረዳው፣ እስካሁን ድረስ የረሃብ አድማ ሲያደርጉ፣ ‹‹ምንድነው የገጠማችሁ? ችግሩ ምንድነው?›› ብሎ የጠየቃቸው አካል የለም፡፡ ይህም አሳፋሪ መሆኑን አክሏል፡፡ ከፍተኛ አመራሮቻቸው በሕይወትና ሞት መካከል ሆነው፣ የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጡ መጠየቅ አግባብ አለመሆኑንም ተናግሯል፡፡
ተከሳሾቹ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ዓቃቤ ሕግ አስተያየት እንዲሰጥ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፣ ተከሳሾቹ እምነት ክህደት ቃላቸውን ካልሰጡ ክደው እንደተከራከሩ ይቆጠራል፡፡ ነገረ ግን አሁን ‹‹አሞናል›› እያሉ የዕምነት ክህደት ቃል እንዲሰጡ ማድረግ ተገቢም ስለማይሆን ተለዋጭ ቀጠሮ ቢሰጥ ተቃውሞ እንደሌለው ገለጸ፡፡
ሌላው ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ለምን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳላከበረ ኃላፊዎች ታስረው በመቅረብ እንዲያስረዱ በመሆኑ፣ የቀረቡት ኃላፊዎች እንዲያስረዱ ጠየቀ፡፡
አቶ በቀለ ላንድ ማርክ ሆስፒታል እንዲታከሙ የሰጠውን ትዕዛዝ በመተው እንዴት ወደ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሊወሰዱ እንደቻሉ ተጠይቀው፣ የማረሚያ ቤቱ ሁለት ኃላፊዎች እንዳስረዱት፣ ትዕዛዙ የደረሳቸው የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡ አቶ በቀለን ወደ ግል ሐኪማቸው ይዘው ሲሄዱ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ እንዳለና ወደ ጦር ኃይሎች እንዲወስዷቸው መመርያ በቴሌግራም ከበላይ አካል እንደደረሳቸውና እነሱም በተሰጣቸው መመርያ መሠረት ወደ ጦር ኃይሎች እንደወሰዷቸው አስረዱ፡፡ መመርያውን ማን እንደሰጣቸው እንዲያስረዱ ፍርድ ቤቱ ላነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የላከው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንደሚመስላቸው ግምታቸውን ተናገሩ፡፡ በማን ስልክ እንደተላከ ፍርድ ቤቱ ሲጠይቃቸው በአንደኛው ኃላፊ ስልክ እንደተላከ ሲገልጹ፣ ፍርድ ቤቱ ስልኩን ተቀብሎ እውነት ስለመሆኑ አረጋገጠ፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቆች ፍርድ ቤቱ እውነት ስለመሆኑ ያረጋገጠው ደብዳቤ በችሎት እንዲነበብላቸው ወይም ከመዝገብ ጋር እንዲያያዝላቸው ጠየቁ፡፡ ፍርድ ቤቱም የመጨረሻውን አማራጭ ወስዶ ከመዝገብ ጋር እንደሚያያዝ ተናገረ፡፡
ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ጥያቄውን ቀጥሎ ማረሚያ ቤቱ መስማት ወይም መፈጸም ያለበት ‹‹የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ወይስ የበላይ አካልን ትዕዛዝ ነው?›› የሚለውን ምላሽ እንዲሰጡ ኃላፊዎቹን ጠየቀ፡፡
ኃላፊዎቹ በሰጡት ምላሽ፣ ማረሚያ ቤቱ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሆኑን ገልጸው፣ የተፈጸመው ነገር ስህተት እንደሆነ እንደሚያውቁ (የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አለመፈጸማቸውን) ተናግረው፣ ግን የበላይ አካል ትዕዛዝ ሲሰጣቸው፣ ለተከሳሹ አቶ በቀለ አሳይተው ይዘዋቸው እንደሄዱ አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ቀጥሎ፣ ‹‹ታምኑበታላችሁ?›› ብሎ ሲጠይቃቸው፣ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ከበላይ አካል ስለሆነና ማረሚያ ቤቱም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በመሆኑ፣ እንዲሁም ወታደር የበላይ አዛዡን ትዕዛዝ ስለሚያከብር፣ የተባሉትን መፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡ የመመርያ ጥሰት ችግር ቢገጥም፣ ‹‹ተጠያቂ ያደርገናል፤›› በሚል በቴሌግራም የተላከውን ትዕዛዝ ለታራሚው በማሳየት፣ ወደተባሉበት ሐኪም ቤት መውሰዳቸውን ተናገሩ፡፡ በወቅቱ የፀጥታ ችግር ስለመኖሩና አለመኖሩ ፍርድ ቤቱ ላነሳው ጥያቄ፣ ኃላፊዎቹ የደኅንነት ሥጋት ይሁን ወይም አይሁን አለማረጋገጣቸውን ገልጸው፣ መልዕክቱ የደረሳቸው ግን ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ ከሆኑት አቶ ጀማል ኡምሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ ኃላፊው ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የደረሳቸው መልዕክት እንዳለ ተናግረው፣ ያንን ትዕዛዝ እንዲፈጽሙ እንዳዘዟቸውና እንደፈጸሙ አስረድተዋል፡፡
አቶ በቀለ መናገር የሚፈልጉት ነገር እንዳለ ጠበቆቻቸው ለፍርድ ቤቱ ሲያመለክቱ፣ ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ ዕድል እንደሚሰጣቸው ገልጾ፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት ያለባቸው ሕክምና ካገኙና አቅማቸው ሲበረታ መሆን እንዳለበት ፍርድ ቤቱ መገንዘቡን ተናግሮ፣ ለመጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ከሰጠ በኋላ አቶ በቀለ እንዲናገሩ ፈቅዷል፡፡
አቶ በቀለ ለፍርድ ቤቱ ክብር እንዳላቸውና እየደከማቸውም ችሎት የሚገኙት ለዳኞቹ ክብር ስላላቸው መሆኑን ገልጸው፣ ከማረሚያ ቤት ኃላፊዎችና አጃቢዎች፣ ለሕክምና ወደ ላንድ ማርክ እንደወሰዷቸው አረጋግጠው፣ ሆስፒታል ሊደርሱ ትንሽ ሲቀሯቸው፣ መንገድ ተዘግቶ ወደ ጦር ኃይሎች እንዲወስዷቸው ትዕዛዝ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ‹‹አልታከምም›› ብለው ከአራት ሰዓታት ቆይታ በኋላ ወደ ማረሚያ ቤት እንደመለሷቸውም አክለዋል፡፡ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ፀሐይ እንዲያገኙ እያደረጉና በአግባቡ እንደያዟቸው ጠቁመው፣ ነገር ግን እነሱ እንዳይታከሙና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳይከበር የሚያደርግና እነሱን ማጥፋት የሚፈልግ አንድ ማፊያ ቡድን እንዳለ ተናግረዋል፡፡
በየወሩ ይከታተሉት የነበረው የዓይን ሕክምና ሳይቀር እንዲቋረጥ መደረጉንና እስከሚቀጥለው ቀጠሮ በሕይወት ላይገኙ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ገልጸው፣ በሕይወት የሚኖሩ ከሆነ ግን በጤናቸው ላይ ጉዳት ያደረሰባቸው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንደሆነ ጠቁመው፣ ዋና ዓቃቤ ሕጉን ጌዴዮን ጢሞቴዎስን (ዶ/ር) ከሰው ካሳ እንደሚያስከፍሏቸው ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ አቶ በቀለን ከሰማቸው በኋላ፣ ለምን የዓይን ሕክምና እንደተከለከሉ የማረሚያ ቤቱን ተወካዮች ጠይቋል፡፡ አቶ በቀለ የሚታከሙት ዋጋ የዓይን ሐኪም ቤት የሚታከሙ መሆኑን ኃላፊዎቹ ጠቁመው፣ ሐኪማቸው መኖር አለመኖራቸውን ሲያረጋግጡ እንደለቀቁ ስለተነገራቸው በዚያ ምክንያት ሊታከሙ አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን እንዲታከሙ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ አቶ በቀለ ላንድ ማርክ እንዲታከሙ የሰጠውን ትዕዛዝ ማን እንደጣሰና የጥፋቱ ኃላፊነት በማን ላይ እንደሚወድቅ መርምሮ፣ መጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ውሳኔ እንደሚሰጥም ተናግሯል፡፡