‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካና ለዓለም የሚተርፍ ሐሳብ እንዳለን ዓድዋ ትልቁ ምስክራችን ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)
ከ125 ዓመታት በፊት በዓድዋ ተራሮች አውሮፓዊ ቅኝ ገዥ በነበረው የጣሊያን ሠራዊት ላይ የተገኘው አንፀባራቂ ድል፣ ዘንድሮ በመላ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል፡፡ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ መሪነት በ1888 ዓ.ም. በተካሄደው ፍልሚያ የተገኘው ታላቅ ድል፣ የኢትዮጵያዊያንን የአይበገሬነት ከፍታ ከመጨመሩም በላይ ኢትዮጵያንም የአፍሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝቦች አብሪ ኮከብ ማድረጉን በማውሳት፣ ማክሰኞ የካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በተለያዩ ከተሞች አደባባይ በመውጣት የዓድዋ ጀግኖችን ዘክረዋል፡፡
በበዓሉ ዋዜማ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካና ለዓለም የሚተርፍ ሐሳብ እንዳላቸው ዓድዋ ትልቁ ምስክር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ዓድዋ ከፍታ ላይ ከሰቀላቸው የኢትዮጵያ ዕሴቶች አንዱ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ነው፡፡ ከምዕራብና ከምሥራቅ፣ ከሰሜንና ከደቡብ የዘመቱ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በመልክና በሙያ ኅብር የሆኑ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያን ከቅኝ ግዛት የማዳን የአንድነት ዓላማ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ያስገኙት ድል ነው፡፡ በዓድዋ ዘመቻ ከ10 ዓመት ሕፃን እስከ 90 ዓመት አዛውንት ተካፍለዋል። ማየት የቻሉት ብቻ ሳይሆኑ ዓይነ ሥውራንም ዘምተዋል፤›› ብለዋል፡፡
ይህ ሁሉ ኅብረ ብሔራዊ ሠራዊት የተለያየ ቋንቋ እየተናገረ፣ የተለያየ እምነት እያመነ፣ የተለያየ ዓይነት ምግብ እየተመገበ፣ የተለያየ ዓይነት ልብስ ለብሶ፣ የተለያየ ዓይነት ባህል ይዞ፣ በምን እየተግባባ ዘመተ የሚለውን መጠየቅ ተገቢ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የተግባባው በኢትዮጵያዊነቱ ነበር። ኢትዮጵያዊ ኅብረ ብሔራዊነታችን መግባቢያ ቋንቋ ነውና፡፡ አንድነታችን የሚሠራበት ሰበዝ፣ ጥንካሬያችንን የሚገነባው ቅመም፣ ውበታችን የሚኳልበት ቀለም የሚቀዳው ከሌላ ሳይሆን ከኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነታችን ነውና፤›› በማለት ድሉን አወድሰዋል፡፡
የዓድዋ ዘመቻ ኢትዮጵያውያንን ከጥንቱ በተሻለ ያስተሳሰረ ዘመቻ እንደነበረ፣ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን፣ ከሁሉም ብሔሮች፣ ከሁሉም እምነቶች፣ ከሁሉም ዓይነቶች ለአንድ ዓላማ፣ በአንድ ቦታ በዚህ መልኩ መገናኘታቸው ያጠራጥራል ብለው፣ ‹‹ይብዛም ይነስም ዛሬ ያለችውን ኢትዮጵያ የሚወከሉ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ከፍሎች ወረኢሉ ላይ ተገናኝተዋል። ዓድዋ ዘምተዋል። ለዚህም ነው ብዙ ምሁራን ዓድዋ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መሠረት ነው የሚሉት፡፡ እኛ ሁላችን የዓድዋ ልጆች ነን የምንለውም ለዚህ ነው፤›› ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
‹‹በውጊያው ጊዜ ከቅድመ አያቶቻችን መካከል አንዳቸው ጎድለው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ዓድዋም፣ የዓድዋ ልጅነትም ከእነ አካቴው ባልኖሩ ነበር። የአገርን ጥሪ እኩል ሰምተው በጋራ ባይዘምቱና ዓድዋ ላይ የድል ሰንደቅ ባይተከሉ ኖሮ፣ ዛሬ የምናከብረው የድል ቀን መሆኑ ቀርቶ እንደ ሌሎች አፍሪካውያን የነፃነት ቀን በሆነ ነበር። በድል ቀንና በነፃነት ቀን መካከል የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለ። ዓድዋ ከእኛ የድል ሰንደቅነት አልፎ ተርፎ ለብዙ የነፃነት ቀናት እንደ ምንጭ ሆኖ ያገለገለ፣ ለፀረ ቅኝ አገዛዝ እንቅስቃሴዎች ፋና የለኮሰ፣ በሁለት ዘሮች በጥቁሮችና በነጮች መካከል የተገነባውን የበታችነትና የበላይነት ግንብ የፈረካከሰ፣ ባለ ብዙ መልክ ትዕምርት ነው፡፡›› ሲሉ የድሉን መሠረት አስታውሰዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች አኩርፈው የሸፈቱ ሳይቀሩ ዕርቅና ሰላም እያወረዱ ከዓድዋው ዘማች ጋር መቀላቀላቸውን፣ ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የአመራር ጥበብ የታየበት ድል መሆኑን፣ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በአራት መንገድ ሠራዊቱን ማደራጀታቸውን፣ የኋላ ኋላ ዕውን የሆነው ድል በአንድ ጀንበር የመጣ እንዳልነበረ፣ ብርቱ የአገር ልጆች በተለያዩ መንገዶች መሣሪያ በማሰባሰብ፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ ጥቂት ጊዜ መግዛት የሚያስችል የዲፕሎማሲና በመረጃዎች የመራቀቅ ሥራዎችን በማከናወንና ሠራዊቱን አደራጅተው በመዝመት ያንን ድል ማሳካታቸውን አመላክተዋል።
በየምዕራፉ የነበረውን ፈተና በልኩ እየተጋፈጡ፣ ጥቃቅን ችግሮችን እየታገሱ፣ በፀና ዲሲፕሊን እየተመሩ፣ ብልጫ ሊገኝበት የሚቻልበትን መንገድ እየተጠቀሙ፣ የጠላት ጓዳ ጎድጓዳ ውስጥ ገብቶ ጠቃሚ መረጃዎችን እየመነተፉ በመታገል የተገኘ ድል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ይህ የመሪዎችን የአመራር ብልኃትና የሠራዊቱን መርህ ጠባቂነት ያሳየ ነበር። የአመራር ብልኃት፣ የመሣሪያ አጠቃቀም፣ የሠራዊት ብቃትና የመልክዓ ምድር አያያዝ ተባብረው ያስገኙት ድል ነው፡፡ በአጠቃላይ የዓድዋ ድል የማይቻል የሚመስለው የተቻለበት፣ የማይቀየረው የተቀየረበት ታሪካዊ ድል ነው፤›› ሲሉ አሞካሽተዋል፡፡
ያልዘመነ ጦር የታጠቀ አፍሪካዊ ኃይል ልዩ ልዩ የዘመኑ የጦር መሣሪያዎችን እስከ አፍንጫው የታጠቀ አውሮፓዊ ኃይል ድባቅ መትቶ የጣለበት ውብ አጋጣሚ እንደነበር፣ የማይቀየር የሚመስለው የነጮች የበላይነት ታሪከ በጥቋቁር አናብስት የተሸነፈበት፣ ኢትዮጵያም በዓለም አደባባይ ጥቁር ፈርጥ ሆና ብቅ ያለችበት ድንቅ ጊዜ መሆኑን አክለዋል፡፡
‹‹ዓድዋ ድል ብቻ አይደለም። ዓድዋ የኢትዮጵያ መለያ ‹ብራንድ› ነው። የኢትዮጵያውያን ከፍታ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል የሚያሳይ ፍልስፍና ነው። ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከመተንተን ይልቅ ዓድዋን ማሳየት በሚገባ ለመረዳት ያስችላል። መሪና ተመሪ ተናቦና ተገናዝቦ ከሠራ ውጤቱ እንዴት ዓለምን እንደሚቀይር ዓድዋ የዘለዓለም ማሳያ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካና ለዓለም የሚተርፍ ሐሳብ እንዳለን ዓድዋ ትልቁ ምስክራችን ነው፡፡ ለወደፊትም ዓድዋን የመሰሉና እንደ ዓደዋ የገዘፉ ምስክሮች እንደሚበዙልን አልጠራጠርም፤›› ብለዋል።
‹‹ጉዟችን ኢትዮጵያን ወደ ቀጣዩ ከፍታ ማሻገር ነው። የዓድዋን ሪከርድ መስበር ነው። እንደምንችል አረጋግጠናል፣ እንደምንችል ማሳየት ግን ይቀረናል። ሰንኮፎቻችን ሁሉ ቀስ በቀስ እየተነቀሉና መንሳፈፊያ ክንፎቻችን እየተዘረጉ ሲመጡ ያለ ጥርጥር ዘመናችን ብሩህ ይሆናል፣ ጉዞውን ጀምረናል። ወደ ዓድዋ መድረሻው መንገድ ፈታኝ ነበር፡፡ የዓድዋ ድል ግን ጣፋጭ ነው። ወደ ብልፅግና መድረሻ መንገዳችን ፈታኝ ይሆን ይሆናል። ብልፅግናችን ግን እንደ ዓድዋ ሁሉ አይቀሬ ድል ነው። ኢትዮጵያ ከዓድዋ በታች አትወርድም። ከዓድዋ በላይ ወዳለው ከፍታ ደግሞ አንድ ሆነን እኛ እናወጣታለን፤›› በማለት መልዕክታቸውን አሳርገዋል።