በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ የገበያ ማዕከላት ላይ ባለፉት ስድስት ወራት በደረሱ 199 የእሳት አደጋዎች፣ ከ157.8 ሚሊዮን ብር ብላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮና ከንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረገው ውይይት፣ 85 በመቶ የሚሆኑት አደጋዎች የደረሱት ከጥንቃቄ ጉድለት መሆኑን ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
በ2013 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ በገበያ ማዕከላት በደረሱ አደጋዎች፣ 25 የንግድ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውንም አመልክቷል፡፡
‹‹የአዲስ አበባ የንግድ ተቋማት የአደጋ ደኅንነትና ተጋላጭነት ሁኔታ›› በሚል የመወያያ ዳሰሳ ያቀረቡት የኮሚሽኑ የቴክኒክ አማካሪ አቶ ጥላሁን ቶላ፣ የኢንዱስትሪ ብክለትን ኬሚካሎችና ጨረራ አመንጪ ቁሳቁሶችን ባልተገባ ሥፍራ ማስቆሙን ለአደጋዎቹ መንስዔ ናቸው ብለዋል፡፡
አቶ ጥላሁን በፀሐይ ወቅት ተቀጣጣይ ቁሶችን በአንድ ሥፍራ ማከማቸት ለእሳት አደጋ ተጋላጭነት ሌላው ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመድረኩ የተገኙ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች በበኩላቸው በገበያ ሥፍራዎች የሚዘረጉ መሠረተ ልማቶች ለእሳት አደጋ እንደሚያጋልጡ፣ ውስብስብ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች ለአደጋው መንስዔ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በየገበያ ሥፍራው ውስጥ ምግብ፣ ሻይ ቡናና ሌሎች ትኩስ ነገሮችን ለመሸጥ ከሰል፣ ጋዝና የኤሌክትሪክ ምድጃዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውም ሌላው አሳሳቢ የእሳት አደጋው መንስዔ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታውን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር የተጀመረውን ቅንጅት በማጠናከር መፍትሔ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ ተናግረዋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብም የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ቀድሞ እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል፡፡