Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየዓድዋ ድል 125ኛ ዓመት

የዓድዋ ድል 125ኛ ዓመት

ቀን:

ዩኔስኮ የዓድዋ ጦርነት ኮንፈረንስን በድረ ገጽ ዓርብ ያካሂዳል

ኢትዮጵያ በወራሪው የጣሊያን ሠራዊት ላይ በ1888 ዓ.ም. የካቲት ወር 23ኛ ቀን ላይ በዓድዋ ከተማና ተራሮች ላይ ድል የተቀዳጀችበት 125ኛ ዓመት በየክልሉ መዲናዎችና በተለያዩ አገሮች በሚገኙ አገራዊ ኤምባሲዎች በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

በተለይ አገራዊው በዓል በጠቅላይ አዝማቹ በተሰየመው የአዲስ አበባው ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ፣ በተለያዩ ዘመኑን በሚያስታውሱ ትርዒቶች ከመከበሩም ባለፈ እንደ ሁሌው በንጉሠ ነገሥቱ ሐውልት ሥር ጉንጉን አበባ ተቀምጧል፡፡

ከበዓሉ ሁለት ቀናት በፊት 125ኛውን በዓል የሚዘክር የባህል ኮንሰርት፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አማካይነት በወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል።

በኮንሰርቱ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ጀግንነት የተመሰከረበት፣ ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነትና እኩልነት ዋጋ የተከፈለበት፣ የአገር ፍቅር በተግባር የተገለጠበት ዘመን አይሽሬ የድል በዓል ነው።

የካቲት 21 ቀን 2013 .. በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የብሔራዊ ቴአትር የሙዚቃ ዳይሬክተር አቶ ወሰንየለህ መብረቁ ባደረጉት ንግግር፣  ታላቁን የድል በዓል በየዓመቱ በኮንሰርት እንደሚዘከር አስታውቀዋል።

የዓድዋ ድል 125ኛ ዓመት

በተያያዘም በምሕፃሩ ዩኔስኮ የሚባለው ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም፣ በአፍሪካ ጠቅላላ ታሪክ ሥር ስለዓድዋ ጦርነት ‹‹የዓድዋ ጦርነትለአፍሪካ አህጉር ነፃነት ትግል ወሳኝ ምዕራፍበሚል ርዕስ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. (ማርች 5 ቀን 2021) ኮንፈረንስ እንደሚካሂድ በፈረንሣይ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሔኖክ ተፈራ ሻውል በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

በድረ ገጽ የሚደረገውን ኮንፈረንስ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር  ሒሩት ካሳው የሚከፍቱት ሲሆን፣ የዩኔስኮ የማኅበራዊና ሰብዓዊ ሳይንስ ረዳት ዋና ዳይሬክተር ጋብሪላ ራሞስ፣ የዩኔስኮ ቅድሚያ ለአፍሪካ መርሐ ግብርና የውጭ ግንኙነት ረዳት ዋና ዳይሬክተር ፊርመን ማቶኮ፣ እና በዩኔስኮ የናሚቢያ ቋሚ መልዕክተኛና በዩኔስኮ የአፍሪካ ቡድን ሊቀመንበር አምባሳደር አልበርትስ አዎቻሙብ ንግግር ያደርጋሉ።

ዓድዋና የሴቶች ተሳትፎ በጥቂቱ ሲቀዳ

ስለ ዓድዋ ጦርነት ውሎ የዘገቡ ልዩ ልዩ ድርሳናት እንደሚሳዩት፣ በዓድዋው ዘመቻ የሴቶች ተሳትፎ በወሳኝነት ይታወቃል፡፡ እቴጌ ጣይቱ ከአፄ ምኒልክ ጦር ጋር የራሳቸውን ፈረሰኛ ጦርና እግረኛ ሠራዊት እየመሩ ከመዝመታቸውም በተጨማሪ ለቁስለኞች የሚያስፈልገውን ዝግጅት፣ ለስንቅ የሚያስፈልገውን ምግብም አሰናድተዋል፡፡ በቤተ መንግሥት ያካበቱት ዕውቀት በጦር ሜዳም አገልግሏቸው ኖሮ፣ እንዳ ኢየሱስ ላይ ጣሊያን የመሸገበትን ለማስለቀቅ በኃይል ሳይሆን በብልሃት ብለው በነደፉት እቅድ መሠረት የእቴጌ ጣይቱ ጦር ጠላትን ማርኳል፡፡

ከእቴጌ ጣይቱ አንስቶ እስከ ታች ድረስ የነበሩት አገልግሎታቸው ለድሉ ስኬት ያስጠቅሳቸዋል፡፡ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም በነበሩበት ዓውደ ግንባር የታዘቡትን በግለ ታሪካቸው እንዲህ ጽፈውታል፡፡

ሴት አገልጋይ የተባለችው (የቤት ውልድ ነች ወለተ አማኔል የእንኮዬ ወለተ ማርያም ልጅ ከኛው ጋር ያደገች ነች) ከዘመቻው ላይ በጣም አገለገለች፤ ከቶ እሷ ባትኖር እንዴት እሆን ኖሯል፡፡ እያልኩ ዘወትር ሳስበው ያስደንቀኛል፡፡ እቃ ተሸክማ ስትሄድ ትውላለች፡፡ ከሰፈርን በኋላ ውሃ ቀድታ፣ እንጨት ለቅማ፣ ቂጣ ጋግራ፣ ወጥ ሰርታ ታበላናለች፡፡ ወዲያው እንደዚሁ ለማታ ታሰናዳለች፡፡ እንደዚህ የወለተ አማኔልን አገልግሎት እያሰብኩ ስደነቅ ደግሞ፣ በየሰፈሩ እንደዚህ እንደርሷ ስንት ሴቶች እንደሚያገለግሉ ይታሰበኛል፡፡

የሴቶቹን አገልግሎት ስገምት፣ ደግሞ የበቅሎቹ አገልግሎት ይታወሰኛል፡፡ በመጨረሻው ድምሩን ስገምተው፣ የዓድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮችና በበቅሎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል፡፡ ሁሉንም አያይዤ በደምሳሳነት ስመለከተው፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ነፃነቱን ጠብቀው እዚህ አሁን አለንበት ኑሮ ላይ ያደረሱት፣ እነዚህ የዘመቻ ኃይሎች መሆናቸውን አልስተውም፡፡

ማዕደ ጥበብ

የዓድዋ ድልን አስመልክቶ በተለያዩ የጥበብ ሰዎች የተሠሩ ኪነጥበብ ተኮር ሥራዎች በፊልም፣ በተውኔት፣ በሥነ ሥዕል፣ በሥነ ግጥም፣ በቅኔ ወዘተ. የቀረቡት በርካታ ናቸው፡፡
ከሩብ ዘመን በፊት ታዋቂው የፊልም ዳይሬክተር  ኃይሌ ገሪማ (ኘሮፌሰር) ‹‹ዓድዋ›› በሚል መጠሪያ የደረሰው ፊልም በበርካታ ታሪካዊ ፎቶግራፎች የታጀበ ነበር፡፡ በተውኔት ዘርፍ ጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን «ዓድዋ» ከተሰኘውና 1964 .. ከደረሰው ግጥም ሌላ አሜሪካ ውስጥ ለእይታ የበቃው «ምኒልክ» ተውኔት ዓድዋን ያጎላበት ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ 100 ዓመት ታዋቂው የቴአትር ዳይሬክተር አባተ መኩሪያ በአጋጣሚው የዓድዋውን ዘመቻ ክተት የሚያሳይ ትርኢት ‹‹ክተት ወደ ዓድዋ ዘመቻ›› በሚል ርዕስ ያሳየው ዘመን ተሸጋሪ ሥራ ይጠቀሳል፡፡ የደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት ካለፉ በኋላ የታተመው «ዓድዋ» ተውኔታቸውም ይጠቀሳል፡፡ የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ‹‹ትናገር ዓድዋ፣ ትናገር ትመስክር…››፣ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ‹‹ጥቁር ሰው›› ዓድዋ ተኮር ቅንቀናውም የቅርብ ዘመን ሥራ ነው፡፡ ሌሎችም እንዲሁ፡፡

ሥነ ሥዕልን በተመለከተ ድሉን የሚያሳዩ በተለያዩ ሠዓልያን የተሣሉ ባህላዊና ዘመናዊ ሥዕሎች የመኖራቸውን ያህል ጣሊያናውያንም የምኒልክን ታላቅነትና ድል አድራጊነት፣ የክሪስፒን ተሸናፊነትና ውድቀት የሚያሳይ የካርቱን ሥዕል አሰራጭተዋል፡፡ ሥዕሉ « ፐቲት ጆርናል» የታተመ ሲሆን፣ ምኒልክ ክርስፒን ሲጎሽሙትና ሲጥሉት ያሳያል፡፡

የዓድዋ ጦርነት ድልን በሥዕል በመግለጽ በኩል የቤተ ክርስቲያን ሠዓሊዎች ዓይነተኛ ሚና እንደነበራቸው ይገለጻል፡፡ በቅርቡ ዜና ዕረፍታቸው የተሰማው አቶ ግርማ ፍሥሐ፣ “Ethiopian Paintings on Adwaበሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፣ ትውፊታዊ ሠዓሊያኑ የዓድዋውን ድል በሥዕላቸው የዘከሩበት መንገድ ለኢትዮጵያ ባህላዊ አሣሣል ዕድገት አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሥዕሎች የአፄ ምኒልክ አማካሪ በነበሩት አልፍሬድ ኢልግ ስብስብ ውስጥ በስዊዘርላንድ ሲገኙ፣ የሆልትዝ ስብስብ በበርሊንና የሆፍማን ስብስብ በዋሽንግተን ይገኛሉ፡፡ ... 1905 አካባቢ የተሣሉት ከነዚህ ሥዕሎች መካከል የአለቃ ኤሊያስ፣ የአለቃ ኅሩይና የፍሬ ሕይወት ይገኙበታል፡፡

በሥዕሉ ጐልተው ከሚታዩት ከጠቅላይ አዝማቹ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በተጨማሪ አዝማቾች፣ መካከል ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላ፣  ራስ አባተ፣ ደጃዝማች ባልቻ ይጠቀሳሉ፡፡ ከአዝማሪዎች መካከልም አዝማሪ ፃዲቄ እየሸለለችና እየፎከረች ስታዋጋ የሚያሳይ ሥዕልም አለበት፡፡

የዓድዋ ጦርነት የተካሄደበት ዕለት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የበዓላት ትውፊት መሠረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀን ነው፡፡ ከቀደመው ጊዜ አንስቶ እስካሁን «ጠባቂ ቅዱስ» ( ፓትረን ሴንት) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ዘመን የተሻገረው ዝማሬም፡-

«የዓድዋ አርበኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከምኒልክ ጋር አብሮ ሲቀድስ፤
ምኒልክ በጦሩ ጊዮርጊስ በፈረሱ
ጣሊያንን ድል አደረጉ ደም እያፈሰሱ» የሚለው ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...