ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ከተቋቋሙ የግል ባንኮች መካከል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የሚመደበው ዳሸን ባንክ የ25ኛ ዓመት ኢዮ ቤልዩ በዓሉን ለስድስት ወራት በሚዘልቅ የተለያዩ ዝግጅቶች ማክበር ጀምሯል፡፡
ባንኩ የ25ኛ ዓመት ኢዮ ቤልዩውን በማስመልከት በጀመረው ዝግጅት ሐሙስ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ የባንኩን ደንበኞች፣ ሠራተኞችና የቀድሞ የባንኩ አመራሮችን ጨምሮ ከባንኩ ጋር አብረው ለተጓዙ አካላት ምስጋና ማቅረብና ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
በዕለቱ የክብር እንግዳ በመሆን የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ባንኩን አስመልክቶ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ባንኮች በሥራ አፈጻጸማቸው ቀዳሚ ከሚባሉት ባንኮች አንዱ ዳሸን ባንክ ነው፡፡
ከዝግጅቱ አስቀድሞ መግለጫ የሰጡት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ፣ ባንኩ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ በስኬት መጓዙን ገልጸው፣ ቀጣዩን የባንኩን ጉዞ ለማጠናከር የአሥር ዓመት ስትራቴጂ በመቅረፅ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህ ስትራቴጂ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ባንኩን ከአፍሪካ ምርጥ ባንኮች አንዱ ማድረግ እንደሆነ ያስረዱት አቶ አስፋው፣ በቀጣይ በኢንዱስትሪው ውስጥ ሊኖር ለሚችለው ውድድር እየተዘጋጁ ስለመሆናቸውና ምናልባት ወደፊት ብዙ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ህልማቸውን ለማሳካት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
ባንኩ ቀጣዩን ጊዜ የሚመጥን የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ውጥንም በራሱ ባለሙያዎችና በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በመታገዝ የበለጠ ለመሥራት ዝግጅት አድርጓል ብለዋል፡፡
በቅርቡ ኢንዱስትሪውን የሚቀላቀሉ አዳዲስ ባንኮች ከመኖራቸው አንፃር ባንኩ በራሱ ስትራቴጂ ለውድድር መዘጋጀቱንና ውድድር መኖሩ ጥንካሬን እንደሚፈጥር አክለዋል፡፡
የ25ኛ ዓመት ክብረ በዓል ማስጀመርያ ላይ የተገኙት ዶ/ር ይናገር በበኩላቸው፣ ዳሸን ባንክ እንደስያሜው በከፍታ ጉዞ ላይ እንዲታይ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡
ባንኩ አሁን ያለበት ደረጃ በኢንዱስትሪው ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ስለመሆኑ ያመለከቱት ዶ/ር ይናገር፣ የባንኩ ከፍታ በየጊዜው እያደገና የባንኩ አስተዳደር ጥንካሬም በኢንዱስትሪው ውስጥ ከአንድ እስከ ሦስት ባለው ደረጃ ውስጥ የሚቀመጥ በመሆኑ የባንኩን አመራሮች አመሥግነዋል፡፡
ለስድስት ወራት በሚከበረው በዓል በዕለቱ በአዲስ አበባ በሃያ አውቶቡሶች ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ የደንበኞች ቀንና ሌሎች ተያያዥ ፕሮግራሞች የሚከናወኑ ሲሆን፣ በተለይም ዳሸን ባንክ ከአገሪቱ ትልቅ ተራራ ስያሜውን የወሰደ በመሆኑ ወደ ዳሸን ተራራ ቋሚ የጉዞ ፕሮግራም በማዘጋጀት በየጊዜው በአካባቢው የችግኝ ተከላ እንዲካሄድ ስለመወሰኑም ተገልጿል፡፡ በየዓመቱ በቋሚነት የጉዞና የሩጫ ፕሮግራም የሚካሄድም ይሆናል፡፡
ዳሸን ባንክ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ የግል ባንኮች ሲቋቋሙ ሦስተኛው ባንክ በመሆን ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ወደ ሰባ ቢሊዮን ብር የተጠጋ ነው፡፡ ይህም በኢንዱስትሪው ከግል ባንኮች ሁለተኛ ከፍተኛ የሀብት መጠን ያለው ሲሆን፣ የባንኩ አስቀማጮች ቁጥር ደግሞ 2.5 ሚሊዮን ደርሷል፡፡
ባንኩ ሥራ የጀመረው በ50 ሚሊዮን ብር ካፒታልና በአሥር ቅርንጫፎች ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የቅርንጫፎቹን ቁጥር 450 አድርሷል፡፡