Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በተከፈለ 5.9 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተው አማራ ባንክ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደ አዲስ ታሪክ ሊጠቀስ የሚችለውን ከፍተኛ ካፒታልና ባለአክሲዮኖች ይዞ የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሥረታውን ዕውን አድርጓል፡፡

  በምሥረታ ፕሮግራሙ ላይ እንደተገለጸውም ሆነ፣ የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ የተመለከቱ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የአማራ ባንክ በአገሪቱ የባንክ ምሥረታ ታሪክ ከፍተኛ የሚባለውን ካፒታል ይዞ ኢንዱስትሪን የሚቀላቀል ይሆናል፡፡

  እስከ ቅርብ ጊዜ ያሉ መረጃዎች የሚያሳዩትም፣ አንድ ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ የተቋቋመ ባንክ አለመኖሩ ነው፡፡ አማራ ባንክ ግን ከዚህ በተለየ 5.9 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ የተመሠረተ የመጀመርያው ባንክ ሆኗል፡፡

  ባንኩን አሁን ካለውና በምሥረታ ካሉ ባንኮች በተለየ እንዲታይ የሚያደርገው ደግሞ፣ በባንክ ኢንዱስትሪውም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ከተመሠረቱ አክሲዮን ኩባንያዎች ሁሉ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ባለአክሲዮኖች መያዙ ነው፡፡ እስከ ምሥረታው ዕለት የባንኩ ባለአክሲዮኖች 188 ሺሕ ደርሰዋል፡፡

  በባንኩ የአደራጆች ኮሚቴ ሪፖርት መሠረት፣ ከነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ሽያጩ እስከ ቆመበት ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 188 ሺሕ ከሚሆኑ ባለአክሲዮኖቹ 5.90 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አክሲዮን ሽያጭ አሰባስቧል፡፡ የተፈቀደ ካፒታሉ ደግሞ 7.9 ቢሊዮን ብር እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የተፈረመ ካፒታሉና ያልተከፈለ ደግሞ 2.02 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡

  ከአክሲዮን ሽያጭ አገልግሎት ክፍያ 396.55 ሚሊዮን ብር አሰባስቧል፡፡ ከአክሲዮን ሽያጭ የተገኘውን ገንዘብ በባንክ በማስቀመጥም 9.19 ሚሊዮን ብር የወለድ ገቢ አግኝቷል፡፡ ባንኩ ያስመዘገበው የአክሲዮን ሽያጭ መጠንና ያሰባሰበው የአገልግሎት ክፍያ እስካሁን በኢንዱስትሪው ውስጥ ያልታየ ከፍተኛው ካፒታል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

  በአክሲዮን ሽያጭ መረጃው መሠረት፣ የውጭ አገር ዜግነት ላላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በውጭ ምንዛሪ መሸጥ ሲገባው በብር የሸጠ ቢሆንም፣ ኋላ ላይ በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት መስተካከሉና ይህም በባለአክሲዮኖች ቁጥርም ሆነ በተከፈለውና በተፈረመው የካፒታል መጠን ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዳላመጣ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ የአክሲዮን ግዥ ሥርጭቱን በተመለከተ 50 በመቶ በአዲስ አበባ፣ 30 በመቶ በሌሎች ክልሎችና 20 በመቶ በአማራ ክልል የተፈጸመ እንደሆነም ይኼው የአደራጆች የምሥረታ ሪፖርት አሳይቷል፡፡

  ከተሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያና ወለድ ውስጥ እስካሁን ድረስ ለተከናወኑ ሥራዎች 16.27 ሚሊዮን ብር ብቻ ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ ቀሪ 389.4 ሚሊዮን ብር እስከ ምሥረታው ዕለት ድረስ የሚወጡ ወጪዎችን በመቀነስ ለባንኩ የሚተላለፍ እንደሆነም በዕለቱ ለባለአክሲዮኖች የቀረበው ሪፖርት አመልክቷል፡፡

  የአክሲዮን ሽያጩ ከተጀመረ በኋላ ባንኩን ለመመሥረት የሚያስፈልገው የተፈረመና የተከፈለ ካፒታል በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሟላ ቢሆንም፣ አክሲዮን ሽያጩ ለሦስት ጊዜ ተራዝሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡

  የአክሲዮን ሽያጩ መራዘም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በባንኩ ምሥረታ እንዲሳተፍ ዕድል የፈጠረ፣ ከፍተኛ ሀብት ለማሰባሰብ ያስቻለና የባንኩን የወደፊት ደንበኞች ማኅበራዊ መሠረት ማስፋት ያስቻለ ቢሆንም፣ አክሲዮን በገዙና ባንኩ በአፋጣኝ እንዲመሠረት ጉጉት በነበራቸው ባለአክሲዮኖች ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና እንደፈጠረም ተገልጿል፡፡ ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ የአንድ ባንክ ምሥረታ ከሚወስደው አማካይ ጊዜ አንፃር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሪከርድ የሰበረ የባለአክሲዮኖች ቁጥርና ካፒታል በማስመዝገብ ባንኩ በዕለቱ መሥራች ጉባዔውን ለማድረግ ስለመቻሉ የአደራጅ ኮሚቴው ሪፖርት ይገልጻል፡፡

  ከሌሎች ባንኮች በተለየ የአማራ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት በተገናኙበት የምሥረታ ጉባዔውን ያካሄደው አማራ ባንክ፣ ይዞ የተነሳውን ካፒታልና ባለአክሲዮኖች ቁጥር በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተስተናገዱበትም ነው፡፡

  በተለይ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ባንኩ የሰበሰበው ካፒታል በኢንዱስትሪው ከፍተኛ የሚባል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የባለአክሲዮን ቁጥርም ከፍተኛውን ድርሻ መያዙን የገለጹት አቶ ዘመዴነህ፣ ‹‹ባንኩ ይህንን ያህል ካፒታልና ባለአክሲዮን መያዙ የሚያሳየው ከተባበርን፣ ለአንድ ዓላማ ከቆምን አገራችንን ማሳደግ እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡

  188 ሺሕ ባለአክሲዮን ማሰባሰብ ቀላል ነገር እንዳልሆነ ስድስት ቢሊዮን ብር ገደማ ማሰባሰብ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገና እየተቀየረ መሆኑን እንደሚያሳይ የተናገሩት አቶ ዘመዴነህ ከተባበሩ ውጤት ይመጣል ብለዋል፡፡

  በአሁኑ ጊዜ ሥራ ላይ ያሉ 16 ባንኮች በአጠቃላይ ተደምረው ያላቸው ባለአክሲዮኖች ቁጥር 140 ሺሕ አካባቢ ሲሆን፣ የአማራ ባንክ ብቻውን 188 ሺሕ ባለአክሲዮኖች በመያዙ የተለየ እንደሚያደርገውም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ ባንኩ ከፍተኛ ካፒታል ይዞ የሚነሳ የመጀመርያው ባንክ ከመሆኑ በላይ፣ አሁን በሥራ ላይ ካሉት ባንኮች አንፃርም ሲታይ የአማራ ባንክ ካፒታል በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡

  በቅርቡ ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2012 ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ እስከ ሰኔ 2012 መጨረሻ ድረስ የአገሪቱ 18ቱም ባንኮች አጠቃላይ የካፒታል መጠን 112.9 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

  ከዚህ ውስጥ ሁለቱ የመንግሥት የሆኑት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጥቅል 57.32 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

  እነዚህ ባንኮች በተናጠል ሲታይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 49.6 ቢሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ 7.6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ በዚሁ የብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት፣ 16ቱ የግል ባንኮች ሰኔ 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ያላቸው የተከፈለ ካፒታል መጠን በጥቅል 55.57 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከ16ቱ የግል ባንኮች ሰኔ 2012 ዓ.ም. ላይ ከፍተኛ ካፒታል የያዘው አዋሽ ባንክ ሲሆን፣ 8.09 ቢሊዮን ብር ካፒታል ሲኖረው፣ ከአዋሽ ባንክ ቀጥሎ የተቀመጠው ዳሸን ባንክ 5.4 ቢሊዮን ብር ካፒታል አለው፡፡ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባንኮች ደግሞ አቢሲኒያ፣ ወጋገን፣ ኅብረትና ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ መሆናቸውን የብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት ያሳያል፡፡   

  ይህ አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየውም፣ የአማራ ባንክ የካፒታል መጠን ላለፉት ዓመታት በሥራ ላይ ካሉ ባንኮች ከአዋሽ ባንክ ቀጥሎ ከፍተኛ የተከፈለ ካፒታል ኖሮት ኢንዱስትሪውን የሚቀላቀል ይሆናል፡፡ በተለይም በምሥረታው ወቅት ስድስት ቢሊዮን ብር የተጠጋ ካፒታል ይዞ የተነሳ የመጀመርያው ባንክ ከመሆኑም በላይ፣ በተፈቀደ ካፒታል መጠን ተጠቃሽ ባንክ ሆኗል፡፡

  ከባንኩ መሥራቶች አንዱና የመሥራቾች የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ መላኩ ፈንታ፣ ‹‹የአማራ ባንክ ምሥረታ ቀን በሕይወቴ ከተደሰትኩበት ቀን አንዱ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ በኢትዮጵያ የአክሲዮን ኩባንያዎች ታሪክ የመጀመርያ የሚባለውን ክንውን የፈጸመ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ብሔር፣ ሃይማኖትና ቋንቋ ሳያግዳቸው አማራ ባንክ የሁላችንም ነው ብለው ከሁሉም የኅበረተሰብ ክፍሎችና ከሁሉም የአገራችን አካባቢዎች በአንድ ጥላ ሥር የተሰባሰቡትና 188 ሺሕ ባለአክሲዮኖች ያሉት ባንክ በአንድነት መንፈስ ካልሆነ በቀር በምንም መንፈስ ይህንን የሚያህል ገንዘብና ሕዝብ ለአንድ ዓላማ ማንቀሳቀስ አይቻልም፤›› ያሉት ደግሞ አዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር ዓባይ ናቸው፡፡ 

  በአማራ ባንክ ምሥረታ ፕሮግራም ላይ የተገኙ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፣ የባንኩን ምሥረታ ከዓድዋ ድል በዓል ጋር አስተሳስረውታል፡፡

  ‹‹ዛሬ በአደባባይ ወጥቶ የታየው የእኔነት ስሜት ነው፡፡ ዛሬ የባለቤትነት ወሰን ነው ያሳየነው፡፡ ከእኔም ባሻገር እኛ የምንለው ሊኖረን እንደሚገባ ያረጋገጥንበት፣ በምጣኔ ሀብት አሻራ ያስቀመጥንበት ታሪካዊ የኢትዮጵያ ቀን ነው፤›› ብለዋል፡፡

  አማራ ባንክ የምሥረታ ጉባዔ ያደረገበትን ዕለትም የጥቁር ሕዝቦች አሸናፊነትና አሻጋሪ ሐሳብ በሆነው የዓድዋ ድል ዋዜማ በመሆኑ ልዩ ታሪካዊ ቀን ያደርገዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ከ125 ዓመታት በፊት በ1888 ዓ.ም. የዓድዋን ድል ስናስታውስ፣ ዛሬ ደግሞ በ188 ሺሕ ባለ አክሲዮኖች የተመሠረተውን ባንክና መሥራቶቹን እናስታውሳለን በማለት፣ አማራ ባንክ ምሥረታና የዓድዋ በዓልን አገጣጥመው ገልጸውታል፡፡

  ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ወደ ዓድዋ ተራራዎች እንደተመሙ ሁሉ፣ በአማራ ባንክም ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ስለመሆኑም በዚሁ ንግግራቸው አክለዋል፡፡ ከድህነት ለመውጣት እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራት የግድ ስለመሆኑም የተናገሩት አቶ አገኘሁ፣ አማራ ባንክ ሕዝብ እንዴት መደራጀት እንዳለበት ያስተማረ ስለመሆኑም አውስተዋል፡፡ የአማራ ባንክ አመሠራረትን ከተመለከቱ መረጃዎች መካከል የአማራ ሕዝብንና አካባቢውን እንዲሁም መላው አገራችንንና ሕዝባችንን ለማልማት በርካታ የፕሮጀክት ሐሳቦች ተፀንሰው እንቅስቃሴ ሲደረግባቸው የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ከተፀነሱ የፕሮጀክት ሐሳቦች መካከል አንዱ የፋይናንስ ሴክሩን በማጠናከር ነው በሚል የተነሳ ነው፡፡

  የፋይናንስ ሴክተሩን በማጠናከርም የልማት ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ለመደገፍና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ባንክ መመሥረት ቅድሚያ ቢሰጠው የሚል ሐሳብ በብዙ ወገኖች ታምኖበት በየአካባቢው አማራ፣ ሐበሻና መሰል ስያሜዎችን በመያዝ ወደ እንቅስቃሴ እንደተገባም ተጠቅሷል፡፡

  የተፈጠረውን ተነሳሽነት ወደ ውጤት ለመቀየር በተለያዩ አካባቢዎች በውጥን ላይ የነበሩ የባንክ ምሥረታ ሐሳቦችን በማወያየትና ወደ አንድ በማምጣት አማራ ባንክ አ.ማ. (በምሥረታ ላይ) በሚል በአንድ ጥላ ሥር በማሰባሰብ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመግባቱም ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዳበቃው ተገልጿል፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከፍተኛ ተወዳዳሪ ባንክ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ በአፍሪካ መሪና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የመሆን ራዕይ ይዞ እንደሚሠራ፣ ለዚህም የሰበሰበው አቅም ከፍተኛ መሆኑ እንደሚያግዘው ተናግሯል፡፡

  ባንኩ የያዘውን አቅም ተጠቅሞ ለመንቀሳቀስ ብዙ ሥራዎች የሚጠብቁት ሲሆን፣ አሁን የያዘውን አቅም ተመርኩዞ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ግን የካፒታል አቅም ብቻውን በቂ አይደለም፡፡

  አቶ ዘመዴነህም ይህንኑ ሐሳብ የሚያጠናክር ገለጻ አድርገዋል፡፡ የተሰበሰበው ካፒታል በኢንዱስትሪው ከፍተኛ ስለመሆኑ የጠቀሱት አቶ ዘመዴነህ፣ ካፒታል ብቻውን አቅም አይሆንም፣ ጥሩ ተወዳዳሪ ሆኖ በመዝለቅ ብዙ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡

  ከዚህም ሌላ እንዲህ ባለው መንገድ ካፒታል አሰባስቦ ለሥራ መብቃት ትልቅ ነገር ቢሆንም ሊታሰብበት ይገባል ያሉት ሌላው ጉዳይ፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉ ባንኮች ተጣምረው ትልቅ ካፒታል ያላቸው አምስት ስድስት ባንኮች መፍጠር እንደሚገባቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አምስት ስድስት ባንክ ነው የሚያስፈልገው የሚል አቋም እንዳላቸው፣ እንደ ምክር ያቀረቡትም አማራ ባንክ አሁን ያሰባሰበውን ወደ ስድስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ይዞ አሁን በሥራ ላይ ከሚገኙት አንድና ሁለት ባንኮች ጋር ቢዋሀድ ከመጀመርያው ጀምሮ የገበያው መሪ መሆን የሚችል መሆኑን ነው፡፡

  ከዚሁ ጋር አያይዘው በአሁኑ ወቅት በፋይናንስ ዘርፉ ብዙ ለውጥ እየታየ መሆኑን፣ ከሁለት ሦስት ዓመታት በኋላ የውጭ ባንኮች ስለሚገቡ ለተወዳዳሪነት መዘጋጀት እንደሚያስፈልግና አማራ ባንክ የሚለው ስያሜም ቢታሰብበት በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች