በትግራይ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲያስፈጽም የተቋቋመው ግብረሃይል የሚመሩት አዛዥ ተቀየሩ።
በትግራይ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ ግብረሃይል በሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር እንዲመራና ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚንስትሩ እንደሚሆን በአዋጁ የተደነገገ ሲሆን በዚሁ መሠረት እስከ ዛሬ የካቲት 24 ቀን 2013 ዓም በጄነራል ብርሃኑ ጁላ ሲመራ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ የካቲት 24 ቀን 2013 ዓም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ ግብርሃይል ጋር ከተወያዩ በኋላ በግብረሃይሉ አመራር ላይ ለውጥ መደረጉን አስታውቀዋል።
ይህንን ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ቃል ከቀባይ አመሻሹን ባወጣው መግለጫም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ ግብረሃይል በጄነራል ዮሐንስ ገብረ መስቀል ተስፋ እንዲመራ መወሰኑን አስታውቋል።
ከዚህም ባሻገር በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ የተራድኦ ድርጅቶች ለሠላም ሚንስቴር ብቻ እያሳወቁ በክልሉ በየትኛውም ቦታ የሀገሪቱን ህጎች አክብረው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የተወሰነ ሲሆን ፤ የተራድኦ ተቋማቱ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለሚደርስባቸው ማንኛውም አደጋ ኃላፊነቱን እራሳቸው እንደሚወስዱም አስታውቋል።