ኮቪድ-19 አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ በአገራችን ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ይገኛል፣ በቫይረሱ የሚያዙ፤ ሕይወታቸውን እያጡ ያሉ፤ ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል እየገቡ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር እያሻቀበ ነው።
የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ለ6,282 ግለሰቦች የኮቪድ-19 የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 1,161 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ቫይረስ ተይዘዋል። ይህም ማለት ናሙና ከሰጡ 100 ግለሰቦች 18 ወይም (18%) ግለሰቦች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ያሳያል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መንገዶችን በአግባቡ አለመተግበራችን ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተይዘው ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥርም እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን፣ እስከ ረቡዕ ዕለት ብቻ 398 ግለሰቦች በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፤ ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ዕለት ጀምሮ ይኼ ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ወደ ኮቪድ-19 የሕክምና ማዕከል ከሚገቡት 100 ግለሰቦች 69 የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ የካቲት 25 ቀን በደረሰን መረጃ ብቻ 19 ያህል ግለሰቦች ሰው ሠራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
አሁንም ልብ ይበሉ! በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር፣ እንዲሁም በኮቪድ-19 ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ስለመጣ እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ማስክ ማድረግ፣ የእጃቸውን ንፅህና በተደጋጋሚ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ተገቢውን የጥንቃቄ መንገዶችን በመተግበር ራስዎንም እንዲሁም ወገንዎን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲጠብቁ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአጽንኦት ያሳስባል፡፡