የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኙ አገሮች በጥቃቅንና በአነስተኛ አምራቾች የሚመረቱ ምርቶችን፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ለማገበያየት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶችን በቀጥታ በመቀበል ወደ ተለያዩ የአገልግሎት የገበያ መዳረሻዎች በዲጂታል የግብይት ሥርዓት ለማገበያየት፣ ከዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት ድርጅትና ከጀርመን ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ጋር ሥራ መጀመሩን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሐና አርዓያ ሥላሴ አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለይም በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል ለገበያ ተደራሽ ባልሆኑ አካባቢዎች ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ምርቶችን የማስተዋወቅና ለሽያጭ የሚቀርቡበትን መንገድ ይፈጥራል ተብሏል፡፡
ተቋሙ ምርቶችን ከማገበያየት ባለፈ በአገር ውስጥ በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ለመሰማራት ዕቅድ መያዙንም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ተቋሙን በቀደመው ዘመን ሲሠራባቸው የነበሩትን የፖስታ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ፣ ዘመኑ የደረሰበትን አገልግሎት ማቅረብ እንዲችል የሚያግዘውን የሕግ ማዕቀፍ እያዘጋጀ እንደሆነ ወ/ሮ ሐና አክለው ገልጸዋል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ያለው የፖስታ አገልግሎት የሕግ ማዕቀፍ ከተቋቋመበት የፖስታ መላክና መቀበል አገልግሎት የመስጠት ዓላማ ውጪ እንዲንቀሳቀስ ስለማይፈቅድ፣ እንደ አዲስ እየተሻሻለ እንደሆነና ይህም ተቋሙ አሁን እየቀነሰ ከመጣው የፖስታ አገልግሎት ተጠቃሚነት ወደ ሌላ ዘመናዊ እንቅስቃሴዎች እንዲገባ ያግዘዋል ተብሏል፡፡
ከዚህ ባለፈ እየተዘጋጀ ያለው የሕግ ማዕቀፍ በኢትየጵያ በሕገወጥ መንገድ መልዕክት የመላክና የመቀበል ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላትን ፈቃድ አውጥተው እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በ2013 ዓ.ም. የመጀመርያ ግማሽ ዓመት በኮሮና ወረርሽኝና በትግራይ ክልል ከተፈጠረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተገናኘ፣ በተለያዩ ቦታዎች ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አስቸጋሪ ሁኔታ እንደተፈጠረ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በስድስት ወራት ውስጥ ከፖስታ አገልግሎት ክፍያ ለመሰብሰብ ካቀደው አጠቃላይ ገቢ 230 ሚሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 92 በመቶ ማሳካት እንደቻለ አክለው አስረድተዋል፡፡
በመላ አገሪቱ በሚገኙ ከ900 በላይ ቅርንጫፎቹ ወደ 90 አገሮች መልዕክቶችን እያደረሰ እንደሆነ፣ አልፎ አልፎ የሚታዩ የመልዕክት መጥፋትና መዘግየት ችግሮችን በማስተካከልና ለመቀነስ እየሠራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡