Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ድርሻ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት ችግር እንዳለበት፣ በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሚደርሳቸው ክልሎች ውስጥ አንዱ መሆኑን፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘው ተሻገር ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን የገለጹት ሐሙስ የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ ዞን በእንሳሮ ወረዳ፣ የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ በተቀመጠበት ሥነ ሥርዓት ላይ ነው፡፡

አቶ አገኘሁ በመሠረተ ልማት ረገድ በተለይ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ በክልሉ ከፍተኛ ችግር ስለመኖሩ እንደ ምሳሌ የጠቀሱት፣ በዕለቱ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለትን ግዙፍ ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል በማስፈለጉ ነው፡፡ ‹‹የኤሌክትሪክ ኃይል ካልቀረበ ግንባታው ትርጉም የለውም፤›› በማለት ያለውን ችግር ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ያለውን ችግር በተለየ መንገድ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ባለሀብቶች መዕዋለ ንዋይ ለማፍሰስ ቢመጡም፣ ክልሉ ለማስተናገድ መቸገሩን ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሊሻሻል የሚገባ መሆኑን፣ ‹‹ቢያንስ ከሌሎች ጋር የሚመጥነን ያህል የመሠረተ ልማት አቅርቦት ሊደረግልን ይገባል፤›› በማለት ጥያቄያቸውን በቀጥታ ለዕለቱ የክብር እንግዳ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አቅርበዋል፡፡

በአንፃሩ ባለፉት ዓመታት በተለይ ከለውጡ በኋላ በመንገድ መሠረተ ልማት እየተደረገ ያለው ለውጥ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረው፣ ነገር ግን ከኤሌክትሪክ ኃይል አንፃር ገና ነው ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ይህንን የሚያህል ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ ገንብተን የኤሌክትሪክ ኃይል ከሌለ መገንባቱ ትርጉም አይኖረውም›› ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹እዚህ የምትገኙ በተለያየ ደረጃ ያላችሁ የመንግሥት ኃላፊዎች ከኃይል አንፃር ያለብንን ችግር ተደጋግፈን ችግሩን ልንፈታ ይገባል፤›› ሲሉ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት አቶ አገኘሁ፣ ከአገር አቅም በላይ ይሰጠን ማለታቸው እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ የክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በተመለከተ ካደረጉት ንግግር መረዳት እንደተቻለው፣ ወደ ክልሉ የሚመጡ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች እየተበራከቱ ናቸው፡፡

በደብረ ብርሃን ከፍተኛ የሆነ የኢንዱስትሪ ጥያቄ እንዳለና ወደ ክልሉ ፋብሪካዎች በስፋት እየመጡ መሆናቸውን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ይህ የሆነበት ምክንያት በክልሉ አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ በምንም ሁኔታ የአማራ ክልል ሕዝብና ወጣቶች ፋብሪካዎችን አያቃጥሉም በማለት፣ ክልሉ ለኢንቨስመንት ምቹ መሆኑንና በተለይ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች