Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበደቡብ ክልል የአማሮ ልዩ ወረዳ ስድስት የዕርቅ መልዕክተኞች ተገደሉ

በደቡብ ክልል የአማሮ ልዩ ወረዳ ስድስት የዕርቅ መልዕክተኞች ተገደሉ

ቀን:

የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ ሲገደሉ

የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

በተደጋጋሚ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን አጎራባች ወረዳዎች ጋር የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማርገብ ወደ ዞኑ ገላና ወረዳ ጀርሜ መጣሬ ቀበሌ ያቀኑ ስድስት የደቡብ ክልል የአማሮ ልዩ ወረዳ አመራሮችና የዕርቅ ኮሚቴ አባላት፣ ሰኞ የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በታጣቂዎች ተገደሉ፡፡

የልዩ ወረዳዋ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ዳኛቸው አኬና፣ ኮንስታብል ተመስገን ዳንኤል፣ አርሶ አደር መብራቱ መለሰ፣ ወጣት መስኪ መብራቴ፣ አቶ መኤሾ መራፌ፣ እንዲሁም ትንሳዔ ታመነ በታጣቂዎች በተከፈተባቸው ተኩስ ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የልዩ ወረዳዋን ዋና አስተዳዳሪ ጨምሮ ሰባት ግለሰቦች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ስድስቱ በአማሮ ኬሌ ሆስፒታል፣ የልዩ ወረዳዋ አስተዳዳሪ ደግሞ በአርባ ምንጭ ከተማ የሕክምና ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ የአማሮ ልዩ ወረዳ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዳም ፍሬው ታሪኩ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

አመራሮቹ ከአማሮ ልዩ ወረዳ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችንና አርሶ አደሮችን፣ እንዲሁም የወጣቶች ተወካዮችን ይዘው በምዕራብ ጉጂ ዞንና በአማሮ ልዩ ወረዳ አጎራባቾች ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስወገድ የሚያግዝ የሰላም ኮንፈረንስ ለማካሄድ ነበር በኦሮሚያ ክልል ጀርሜ መጣሬ ቀበሌ የተገኙት፡፡ ይሁንና ድንገት በታጠቁ ግለሰቦች በተከፈተባቸው ጥቃት የስድስት ግለሰቦች ሕይወት ሲያልፍ፣ ሰባት ግለሰቦች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

ጥቃቱን የፈጸሙት በአካባቢው እንደሚንቀሳቀሱ የሚነገርላቸውና የቀድሞ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ወታደራዊ ክንፍ የሆነውና በኋላ ኦነግ ከወታደራዊ ክንፉ ጋር መለያየቱን ማስታወቁን ተከትሎ መንግሥት ‹‹ኦነግ ሸኔ›› በማለት የሚጠራው ኃይል አባላት እንደሆኑ የተጠየቁት አቶ አዳም፣ ይኼንን ለማለት እንደሚያስቸግራቸው ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል ሚሊሻዎችና ፖሊሶች ጥቅም ላይ የሚውሉ የደንብ ልብሶችን የለበሱ እንደነበሩ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ጥቃቱን የፈጸሙት ሰዎች የኦነግ ሸኔ አባላት ናቸው›› የሚለውም ማሳበቢያ፣ ትክክለኛ አጥፊዎች እንዳይገኙና ፍትሕ እንዳይሰጥ የሚደረግ ማደባበስ ነው ብለዋል፡፡ በግጭቶች ምክንያትም በሕዝቡ ላይ ጫና የመፍጠር ፍላጎቶች መኖራቸውንም አልሸሸጉም፡፡

‹‹በተለይ የለውጡ መንግሥት ከመጣ ወዲህ ከኦሮሚያ ክልል አካባቢ ተደጋጋሚ አርሶ አደሮችን የማፈናቀልና የእርሻ ሥፍራዎችን አውድሞ የማባረር ድርጊቶች በርክተዋል፡፡ ይህም የእርሻ ሥፍራዎችን ለመውሰድ የሚደረግ ጥረትም ጭምር ነው፤›› ሲሉ የልዩ ወረዳው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን ደርባቤ፣ ጀሌ፣ ቡኒቲና ሻሁሌ በተባሉ አራት ቀበሌዎች በደረሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች አራቱም ወረዳዎች ከእነ እርሻ ማሳዎቻቸውና ቤቶቻቸው ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውንም የሚናገሩት አቶ አዳም ፍሬው፣ በዚህም ሰበብ የተፈናቀሉ ከ40 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ቀዬአቸው ሊመለሱ አልቻሉም ይላሉ፡፡ ‹‹እነሱን ለመመለስ በማሰብ ነበር የአሁኑ የዕርቅ ኮንፈረንስ የተደረገው፡፡ ተፈናቃዩቹ በመጠለያ ጣቢያዎች ተበታትነው ያለ በቂ ድጋፍ ይገኛሉ፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህንን ችግራቸውን ለደቡብ ክልልና ለፌዴራል መንግሥታት በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም፣ ምንም ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...