ባንኩ ዛሬ ከኢትዮጵያ ጋር የዕርዳታ ስምምነት ይፈራረማል
የዓለም ባንክ የአውሮፓ ኅብረት ውትወታን ተከትሎ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች አያይዝን በተመለከተ DAG (Development Assistance Group) ከሚባለው የኢትዮጵያ ለጋሽ አገሮች ቡድን አባልት ጋር በመምከር ሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ እንዲከበሩ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
ባንኩ ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት በእጅጉ እንደሚያሳስበው የገለጸ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ባለፉት ቅርብ ዓመታት ባስመዘገበችው አበረታች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል አስታውቋል።
ባንኩ የልማት ተቋም እንደመሆኑ መጠን በአባል አገሮች ውስጣዊ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ውስጥ የመግባት ሥልጣን እንደሌለው የሚገልጸው መግለጫው፣ ነገር ግን የሰብዓዊ መብቶች መከበር ባንኩ ከሚገዛባቸው የአሠራር መርህዎች ውስጥ አንዱ አንኳር መመዘኛ እንደሆነ አስታውቋል።
በተጨማሪም ባንኩ የዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር አባል እንደመሆኑ መጠን፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና እንዲረጋገጡ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክር አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ለጋሽ አገሮች ቡድን (DAG) አባላት 27 ለጋሽ አገሮችና የተራድኦ ተቋማትን ያካተተ ሲሆን፣ ከሞላ ጎደል ሁሉም የአውሮፓ አገሮች የሚሳተፉበትና አሜሪካና ካናዳም በአባልነት ያካተተ ነው።
በተጨማሪም የዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፋ የገንዘብ ድርጅትና ሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ልማት ድርጅቶችም የቡድኑ አባላት ናቸው። ከአንድ ወር በፊት የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ስላለው ሰብዓዊ ቀውስ የመከረ ሲሆን፣ ይህንንም መሠረት አድርጎ በክልሉ ያለው ሰብዓዊ ቀውስን የኢትዮጵያ መንግሥት ካላረመና የውጭ ተራድኦ ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብት ተቋማት በትግራይ ክልል እንዲንቀሳቀሱ እስኪፈቀድ ድረስ፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት እ.ኤ.አ. 2020 ከተለመደው የቀጥታ በጀት ድጋፍ ውስጥ ቀሪውን 88 ሚሊዮን ዩሮ እንደማይለቅ አስታውቋል።
የአውሮፓ ኅብረት ውሳኔን ተከትሎ ለውጭ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የኅብረቱ ዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን፣ ኅብረቱ በ2021 ለኢትዮጵያ የሚሰጠው 120 ሚሊዮን ዶላር የበጀት ድጋፍም መሻሻሎች እስካልታዩ ድረስ እንደማይለቀቁ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኅብረቱ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለኢትዮጵያ የሚያደርገው የበጀት ድጋፍም ጥያቄ ውስጥ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ ለነበሩ አምስት ዓመታት 966 ሚሊዮን ዶላር ከአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ ማግኘቷን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማስተካከል በአውሮፓ ኅብረት ከአባል አገሮች የሚደረገው ጫና ብቻውን በቂ ባለመሆኑ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወስዱ ኅብረቱ እያነጋገራቸው እንደሆነም ከአንድ ወር በፊት ገልጸው ነበር።
የዓለም ባንክ ሰሞኑን ያወጣው መግለጫ ይህንን የኅብረቱን ውትወታ ተከትሎ ቢሆንም፣ መግለጫው ግን በቀጥታ ይህንን አላመለከተም።
የዓለም ባንክ የተጠቀሰውን መግለጫ ያወጣ ቢሆንም አንድ የዕርዳታ ስምምነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፈራረማል።