ግንባታ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በገደቡ ምክንያት ሥራቸው እንዳይስተጓጎል ተሰግቷል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድርጅቶች ከባንክ ውጪ ማንቀሳቀስ የሚችሉትን ጥሬ ገንዘብ መጠን ከ1.5 ሚሊዮን ብር ወደ 200 ሺሕ ብር ዝቅ አደረገ።
ከባንክ ውጪ የሚደረጉ የጥሬ ገንዘብ ግብይቶችን ለመቀነስ ያለመው አዲሱ መመርያ፣ ግለሰቦች ማንቀሳቀስ የሚችሉትን የገንዘብ መጠን ከ200 ሺሕ ብር ወደ 100 ሺሕ ብር ዝቅ አድርጎታል።
ከነሐሴ 2012 ዓ.ም. አንስቶ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት ድርጅቶች እስከ ከ1.5 ሚሊዮን ብር ድረስ ጥሬ ገንዘብ መያዝ ይችሉ የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ገንዘብ በላይ ይዘው በሚገኙ ቅጣት እንደሚጠልባቸው ተገለጾ ነበር።
በውቅቱ ገደቡ የተቀመጠው ግለሰቦችና ድርጅቶች በቤትና በመሥሪያ ቤቶቻቸው ውስጥ በርካታ ጥሬ ገንዘብ ስለሚያስቀምጡና ይህንን ለማስቀረት እንደነበር ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ግብር መሰወርና ማጭበርበርንም ያስቀራል ተብሎ ነበር።
በተመሳሳይ ይበልጥኑ ዝቅ የተደረገው አዲሱ ገደብ ጥሬ ገንዘብ ከባንክ ውጪ የማስቀመጥን ልምድ ያስቀራል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም፣ እንደ ግንባታና ሌሎች ከፍተኛ ገንዘብ የሚፈልጉ የቢዝነስ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች የሥራ እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ሥጋታቸውን ከወዲሁ እየገለጹ ነው።
የኮንስትራክሽን ኩባንያ አስቸኳይ ክፍያዎችን ለመፈጸም ከአንድ እስከ አሥር ሚሊዮን ጥሬ ገንዘብ መያዝ ሊያስፈልገው ይችላል የሚሉት የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጭ ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት ግርማ ሀብተማርያም (ኢንጂነር)፣ ገደቡ ወደ 200 ሺሕ ብር መቀነሱ ከዚህ ቀደም ይገጥማቸው የነበረውን ችግር ሊያባብሰው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በተለይም በመንገድና መስኖ ግንባታ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በሥራቸው የሚያሰሯቸው አነስተኛ ደረጃ ያላቸው ተቋራጮችና ለቀን ሠራተኞቻቸው አስቸኳይ ክፍያ ለመፈጸም እንዲሁም የተለያዩ ምርቶችን ለመግዛት ጥሬ ገንዘብ ስለሚያስፈልጋቸው፣ ገደቡ መቀነሱ ሥራቸው ላይ መስተጓጎል መፍጠሩ አይቀሬ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም ግንባታዎችን ሊያዘገይ ስለሚችል ብሔራዊ ባንክ ውሳኔውን በድጋሚ ሊያጤነው እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተጨማሪ አበባ ምርት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች አዲስ የተጣለው ገደብ ሥራቸው ላይ እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፣ ለሠራተኞች ክፍያ ከፍተኛ የሆነ ጥሬ ገንዘብ ስለሚያስፈልጋቸው መመርያው አሉታዊ ተፅዕኖ ሊፈጥርባቸው እንደሚችል በዘርፉ ላይ የተሰማሩ አንድ ባለሙያ ተናግረዋል።
ብሔራዊ ባንክ ከባለፈው ዓመት መጨረሻ አንስቶ የጥሬ ገንዘብ ግብይትን ለማስቀረት የተለያዩ ዕርምጃዎች መውሰዱ ይታወሳል። የገንዘብ ቅየራና ከባንኮች በሚወጣ የጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ የተጣለው ገደብ ተግባር ላይ ከዋሉት ውሳኔዎች መካከል ነበሩ።