በየካቲት ወር የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት 20.6 በመቶ መድረሱን ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ። የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት ባለፉት ስድስት ወራት ከተመዘገቡት ውስጥ በጣም ትልቁ ሲሆን፣ ጭማሪው ምርቶች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ያሳዩት ለውጥ ማሳያ መሆኑ ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ የምግብ ዋጋ ግሽበት 22.8 በመቶ ሲደርስ፣ ምግብ ነክ ባልሆኑ ምርቶች ላይ 18 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ መታየቱን ኤጀንሲው አስታውቋል።
በተለይም በእህሎች ላይ የታየው ጭማሪ ለምግብ ዋጋ ግሽበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ ሲሆን የስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ በርበሬ፣ ድንችና ቡና ዋጋዎች መጨመሩ ግሽበቱን እንዳባባሰው የኤጀንሲው ሪፖርት አመላክቷል።
የማዕከላዊ ስታስቲክስ ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ግሽበት የተመዘገበው በትግራይ ክልል ሲሆን 31.6 በመቶ ደርሷል። አነስተኛ የምግብ ዋጋ ግሽበት በመሆን የተመዘገበው በአማራ ክልል (14.1 በመቶ) እንደሆነ የገለጸው ሪፖርቱ፣ በአዲስ አበባ ደግሞ 25.7 በመቶ መድረሱን አመላክቷል።
በተጨማሪ እንደ ነዳጅ፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ እንዲሁም ልብስና ጫማ ላይ የታዩት ጭማሪዎች ምግብ ነክ ላልሆነ የዋጋ ግሽበት መባባስ መንስዔ እንደሆኑ ተጠቁሟል።
የኑሮ ውድነት የኢትዮጵያውያንን ደጃፍ ማንኳኳት ከጀመረ ዓመታት አስቆጥሯል። ከግብርና ምርቶች እስከ ኢንዱስትሪ ውስጥ ተመርተው የሚወጡ ዕቃዎች ሁሉም የዋጋ ጭማሪ ማሳየት ከጀመሩ ወራት ቢቆጠሩም፣ ባለፉት ሦስት ሳምንታት የታየው የዋጋ ጭማሪ ግን ከወትሮው የተለየ መሆኑን ሸማቾች ያስረዳሉ።
በተመሳሳይ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመላክተው፣ በየካቲት ወር የታየው ወርኃዊ ግሽበት (month-on-month inflation) አራት በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህን ዓይነት ጭማሪ በዓመት ውስጥ ታይቶ አይታወቅም።
በተለይም መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ ማሻሻያ ካደረገ ጊዜ አንስቶ ሁሉም የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል። ለአብነት በአዲስ አበባ በአንድ ወራት ውስጥ ብቻ የታየውን ግሽበት ማንሳት ይቻላል። ከሁሉም ምግቦች በላይ ተፈላጊ የሆነው ጤፍ በኩንታል ከ4,300 ብር ወደ 5,000 ብር ከፍ ሲል የስንዴ ዱቄት ዋጋ በእጥፍ ጨምሮ 4,000 ብር ሊገባ ችሏል።
በተመሳሳይ የአምስት ሊትር ዘይት ዋጋ ከ360 ብር ወደ 470 ብር የጨመረ ሲሆን፣ የእንቁላል ዋጋ ከአምስት ብር ወደ ሰባት ብር ከፍ ብሏል። ለሁሉም ጭማሪዎች እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ የሚወሳው የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ 20 በመቶ ጭማሪ የታየ ሲሆን፣ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ መኪናዎችም ከ30 እስከ 50 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ማስተካከያ አድርገዋል።
ከታየው ጭማሪ በላይ ምክንያቱ አሁንም ለብዙዎች በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል። ቸርቻሪዎች አከፋፋዮች ላይ እጃቸውን ሲጠቁሙ፣ አከፋፋዮች ደግሞ አስመጪዎችንና ፋብሪካዎችን ተጠያቂ ያደርጓሉ። አስመጪዎችና ፋብሪካዎች በበኩላቸው በቂ የውጭ ምንዛሪ እየቀረበልን አይደለም በማለት መንግሥት ላይ ጣታቸውን ይጠቁማሉ። የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችም ከደሙ ንፁህ ነን በማለት የፖለቲካ አሻጥር ውጤት ነው ሲሉ ይደመጣል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ከሁለት ሳምንት በፊት ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ የኑሮ ውድነት ምክንያቶችን ለመለየት ከመስተዳደሩና ወረዳዎች የተወጣጡ ባለሙያዎችና ሥራ ኃላፊዎች ያሉበት ግብረ ኃይል መቋቋሙን በመግለጽ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት የፖለቲካ ኃይሎች የፈጠሩት የገበያ አሻጥር ነው በማለት አስታውቀው ነበር።
ምርቶች በብዛት እንዳይመረቱና የተመረቱት ደግሞ ወደ ገበያ እንዳይገቡ በማድረግ ከቸርቻሪዎች ጋር የተለየ ትስስር በመፍጠር የተከናወነ ሴራ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፣ እነዚህ ኃይሎች በኢኮኖሚ ውስጥ ያካበቱትን ጉልበት በመጠቀም በፖለቲካ የደረሰባቸውን ክስረት ለማካካስ እየሞከሩ ነው ብለው ነበር።
በሌላ በኩል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ለተፈጠረው የዋጋ ግሽበት መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሲሆን፣ በተለይም በቅርቡ የተወሰኑ ውሳኔዎች (ማለትም የነዳጅ ጭማሪና የአገልግሎቶች ታሪፍ ማስተካከያዎች)፣ እንዲሁም ካለፈው ዓመት አንስቶ የተፋጠነው የብር አቅም መዳከም ለተፈጠረው የኑሮ ውድነት ምክንያቶች ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ወሰንሰገድ አሰፋ በበኩላቸው የፖለቲካ አሻጥር ለተከሰተው የዋጋ ጭማሪ ላይ ያለው ድርሻ እጅግ አነስተኛ ነው በማለት፣ ችግሩ የመጣው በፖለቲካል ኢኮኖሚ ውሳኔዎች ምክንያት ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ለሪፖርተር አጋርተዋል። ከእነዚህም ውሳኔዎች መካከል አንዱ መንግሥት መር የሆነው የብር መዳከም እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ወሰንሰገድ፣ አገሪቱ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ በመሆኗ የምንዛሪ ዋጋ ማስተካከያው የዕቃዎችን ዋጋ እንዳስወደደ ተናግረዋል።
የውጭ ንግድ ገቢን ለመጨመርና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ በሚል ዓላማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ፣ የብር ዋጋ ከዶላር አንፃር በ47.1 በመቶ እንዲዳከም ተደርጓል። ቁጥሩ በግልጽ ሲቀመጥ እሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ የአንድ ዶላር መገበያያ ዋጋ 27 ብር ከ87 ሳንቲም የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ 41 ብር ደርሷል።
በዚህ መጠን ብር መዳከም የዋጋ ግሽበትን ከማባባስ ውጪ ያመጣው ፋይዳ የለም የሚሉት አቶ ወሰንሰገድ፣ የጠቀመውም ምርታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለሚልኩና አገሪቱ ውስጥ የሚመረቱ የግብርና ዕቃዎችን ለሚገዙ አገሮች ነው በማለት የመንግሥትን አካሄድ ተችተዋል።
የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከመኖሩ ጋር ተዳምሮ የብር መዳከም በትይዩ ገበያ ላይ ያለውን የምንዛሪ ዋጋ በመጨመሩ፣ የዕቃዎችን ዋጋ እንዳናረው ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡ ይህም አገሪቱን ውጫዊ ለሆነ ዋጋ ግሽበት (imported inflation) እንዳጋለጣት ባለሙያዎች ያወሳሉ። በተለይም በትግራይ ክልል ያለው ግጭት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ሳይባብሰው እንዳልቀረ የተጠቆመ ሲሆን፣ በተለይም ከዚህ ቀደም ምርቶችን ለማስገባት ይውል የነበረ የውጭ ምንዛሪ ለመከላከያና ለደኅንነት የሚውልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ የሌሎች አገሮች ልምድን በማውሳት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ሌላው ለዋጋ ግሽበት መጨመር ምክንያት ተደርጎ በባለሙያዎች ዘንድ የሚነሳው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ነው። ኮሮና ቫይረስ የተከሰተ ሰሞን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዜሮ ዶላር በታች ሲሸጥ የነበረው ነዳጅ በዚህ ደረጃ ቅናሽ ሲያሳይ የዋጋ ማስተካከያ ያላደረገው መንግሥት፣ ከሁለት ወራት ወዲህ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ ለሦስት ጊዜ ያህል ማስተካከያ አድርጓል።
የመጀመሪያው ጭማሪ በጥቅምት ወር ላይ የተደረገ ሲሆን፣ ማስተካከያው በአማካይ አሥር በመቶ አካባቢ ነበር። ከዚያም በጥር ወር መሸጫ ላይ ተመሳሳይ የአሥር በመቶ ማስተካከያ ከተደረገ በኋላ፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ እስከ አንድ በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ተደርጓል።
የነዳጅ ምርቶች በጎረቤት አገሮች ከዚህ እጥፍ በሆነ ዋጋ እየተሸጠ በመሆናቸው ኮንትሮባንድን ለመከላከል መጨመሩ ተገቢ ቢሆንም፣ ወቅቱን ያማከለ እንዳልሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ያስረዳሉ። በተለይም የዋጋ ግሽበት ባልተረጋጋበት ወቅት የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ መደረጉ ጭማሪውን እንዳባባሰው ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከሁለት ወራት በፊት በዓለም አቀፍ ዋጋ ላይ ጭማሪ በመታየቱ፣ መንግሥት ነዳጅ ከውጭ ለመግዛት የሚያወጣው ወጪ በ1.5 ቢሊዮን ብር በማደጉ ድጎማውን ለመቀነስ መገደዱን ማስታወቁ ይታወሳል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በጥቅሉ ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ ያደረገው መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ ከ100 በመቶ ወደ 75 በመቶ መቀነሱን፣ ከሁለት ወራት በፊት ለሕዝብ ይፋ አድርጎ ነበር። ይህም ተገቢ አይደለም ያሉት ባለሙያው፣ ድጎማውም ሆነ ጭማሪ ቀስ በቀስ ሊደረጉ ይገባ እንደነበር ጠቁመዋል።
ሌላው አገሪቱን ለዋጋ ግሽበት ያጋለጣት የመንግሥት ውሳኔ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረገው የወለድ መጠን ማስተካከያ እንደሆነ ይወሳል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባንኩ ያደረገው የወለድ መጠን ማስተካከያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግዙፍ እንደ መሆኑ መጠን በተለያዩ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ላይ ጫና ስለሚፈጥር ዋጋ እንዲጨምሩ ሊገፋፋቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።