የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በሥራ ላይ ያዋለውን የአካል ጉዳተኛ መብት ስምምነት ኢትዮጵያ በአዋጅ ቁጥር 676/2002 በማፅደቅ የሕግ አካሏ እንዲሆን አድርጋለች፡፡ ይህ ጉልህ ዕርምጃ በመንግሥት ከተወሰደ ካለፈው አሠርት ወዲህ ለአካል ጉዳተኞች ምላሽ በመስጠት ረገድ መሻሻል ታይቷል፡፡ በዚህ በኩል በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሚከናወኑ ተግባራት ለውጦች መመዝገባቸው ይወሳል፡፡
ይሁን እንጂ በስምምነቱ ውስጥ የተካተቱን ዝርዝር ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት በሚመለከት ክፍተቶች ታይተዋል፡፡ በጤና፣ በትምህርትና ፍትሕ ዘርፎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለአካል ጉዳተኛ ተደራሽ በማድረግ በኩል የሚቀሩ ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በዚህ ምክንያት አካል ጉዳተኞችን በአገራዊና አካባቢያዊ የፖሊሲና የልማት አጀንዳዎች ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ ረገድ በስምምነቱ መሠረት የጎላ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው በእጅጉ መገደቡ ይነገራል፡፡
እነዚህን በመሰሉ ሁኔታዎች ውስጥ በተለይ አካል ጉዳተኛ ልጃገረዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ኮቪድ-19ን ጨምሮ ለተለያየ የከፋ ችግሮችና የተደራሽነት እጦት ተጋላጭ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡
አካል ጉዳተኞችን የሚመለከተው ኖቪብ የሚባል ተቋም አማካሪ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ታከለ እንደሚያብራሩት፣ መንግሥት ማንኛቸውንም ሕግ ሲያወጣና ፖሊሲ ሲቀርፅ አካል ጉዳተኞችንና ጾታን ወይም ተወካዮቻቸውን ማካተት ይገባዋል፡፡ ይህ ዓይነቱም አካሄድ የሚወጣው ሕግና ፖሊሲ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ክፍተት እንዳይኖረው ብዙ ጊዜ ይህን ያለማስተዋል ችግር አለ፡፡
አማካሪው ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ የወጣውን ሕግ ክፍተት እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡ ‹‹የኮቪድ-19 ሕግ አንቀጽ አራት በማንኛውም መንገድ መነካካት ክልክል መሆኑ ይደነግግና ይህን የጣሰ ሰው እስከ 15 ዓመት ለእስር እንደሚደረግ ያመለክታል፡፡ ከዚህ አንፃር ተደራሽነት ባልተሟላበት ሁኔታ አካል ጉዳተኞች በሰው ካልተደገፉ ወይም ካልታገዙ ሊንቀሳቀሱና ደረጃ ሊወጡ አይችሉም፡፡ ይህ ሁኔታ ሊፈጠር የቻለው ሕጉ ሲወጣ አካል ጉዳተኞችን ወይም ተወካዮቻቸውን ሳያማክሩ በመውጣቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የማስታወቂያ አዋጅን በተመለከተ ማስታወቂያ ሲወጣ አካል ጉዳተኞችን የሚያስቀይም፣ ሞራላቸውን የሚነካ መሆን እንደሌለበት፣ ይህ ሆኖ ከተገኘ እንደሚያስቀጣ መግለጹ በጥሩ ጎን ቢታይም፣ በዚህ ላይ የአካል ጉዳተኞችን በሚመለከት ለነሱ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ግን አለመካተታቸውን አማካሪው አስታውሰዋል፡፡
ከአቶ ዮሐንስ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ የአካል ጉዳተኞችን ጥያቄ በተሟላ መልኩ ለመመለስ የሚቻለው በአንዳንድ ሕጎች ውስጥ በማካተት ሳይሆን ራሱን ችሎ እንደ ሕገ መንግሥት ወይም እንደ ጥቅል ሕግ ሆኖ ማውጣት ሲቻል ብቻ ነው፡፡
አካል ጉዳተኝነትንና በሽታን አንድ አድርጎ ማየት የተሳሳተ አመለካከት መሆኑን ያወሱት አማካሪው አካል ጉዳተኝነት ክስተት እንጂ በሽታ እንዳልሆነ፣ የአካል ጉዳተኝነት ችግር የአካባቢያዊ ተደራሽነት እጦትና አለማስተካከል እንጂ የጤንነት እክል እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡