Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበቅርቡ መሰጠት የሚጀመረው የኮቪድ-19 ክትባት

በቅርቡ መሰጠት የሚጀመረው የኮቪድ-19 ክትባት

ቀን:

ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ‹‹አስትራ ዜኒካ›› የተባለው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት፣ በቅድሚያ የሚሰጣቸው ማኅበረሰቦች በውል መለየታቸውና ክትባቱንም  በቅርብና በተመሳሳይ ቀናት መስጠት እንደሚጀመር የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በህንድ ተመርቶ ኮቫክስ በተባለ ዓለም አቀፍ ጥምረት የተላከውን የመጀመርያውን ዙር 2.2 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ሚኒስትሯ ከተረከቡ በኋላ እንደገለጹት፣ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ማኅበረሰቦች መካከል በአገሪቱ ባሉት የሕክምና ተቋማት የሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፡፡

ከዚህም ሌላ ተጓዳኝ በሽታ ያሉባቸውና ዕድሜያቸው የገፋ ማኅበረሰቦች እንደ ቅደም ተከተላቸው የክትባቱ ተቋዳሾች እንደሚሆኑ፣ በዓለም ጤና ድርጅት አሠራር መሠረት ተጠቃሚ ማኅበረበሶችን መለየቱ የተከናወነው በብሔራዊ ደረጃ በተቋቋመው ግብረ ኃይል ነው፡፡

- Advertisement -

‹‹በቫይረሱ የሚታመሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ባለበት ሰዓት የክትባቱ መምጣት ትልቅ ዜና ቢሆንም፣ የመከላከሉ ሥራዎቻችንን የሚያስቆም አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሚመጣው የክትባት መጠን ቁጥሩ ትንሽ ነው፡፡ ይህንንም ሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍል መውሰድ አይችልም፡፡ ስለዚህ የመከላከሉ ሥራዎቻችን አሁንም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ብዙ አገሮች የክትባት ምርምርና የማምረት ሥራ እንደጀመሩ፣ በዚህም የተነሳ በርካታ ክትባቶች በመጨረሻ ደረጃ ላይ እንዳሉ፣ ጥቂት የሚባሉት ክትባቶች ደግሞ ወደ ተለያዩ አገሮች ተሠራጭተው ለተጠቃሚዎች እንደቀረቡ ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት፡፡

ይህንን ክትባት ተደራሽ ለማድረግ እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ እንደ ኢትዮጵያ የመሰሉና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ከሌሎች ካደጉ አገሮች ጋር እኩል ማግኘት እንደተሳናቸው፣ በዚህም የተነሳ ‹‹ኮቫክስ›› የተባለው ዓለም አቀፍ ጥምረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ላላቸው 94 አገሮች ክትባቶችን መስጠት እንደቻለ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ያስሚን ውሃብረቢ ክትባቱን ተጋላጭ ለሆኑ ማኅበረሰቦች ለማድረስ በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ ለሎጂስቲክስና ሌሎች ሥራዎች የሚያስፈልገውን ወጪ ሚኒስቴሩ እንደሚሸፍን፣ ለዚህም ዕውን መሆን ከዓለም ባንክ ጋር ባለፈው ሳምንት መፈራረሙን ነው ያመለከቱት፡፡

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ካንትሪ ዳይሬክተር ኡስማን ዳይን (ዶ/ር)፣ ክትባቱን ለማጓጓዝ ዓለም አቀፉ ባንክ የ207,000 ዩሮ ድጋፍ እንደሰጠ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎና ሎጂስቲክስ ሰርቪስ ዳይሬክተር አቶ ፍፁም አባዲ፣ አየር መንገዱ የኮቪድ-19 ክትባቶችን በተለያዩ አምስት አኅጉራት ውስጥ እያጓጓዘ እንደሚገኝ፣ እስካሁንም 390 የቻርተር በረራዎችን እንዳካሄደ ተናግረዋል፡፡

‹‹የአውሮፓ አገሮች ትልልቅ አውሮፕላኖች ቢኖራቸውም፣ የኮቪድ-19 ክትባትን በማጓጓዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ለጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ ቤልጂየም፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ፖርቱጋል፣ ስፔን፣ እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ ካናዳና ሜክሲኮ፣ ላቲን አሜሪካ ውስጥ አርጀንቲና አጓጉዟል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በአፍሪካ ከሚገኙ 54 አገሮች መካከል ለ52ቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማጓጓዝ ክትባቱን እንዲያገኙ በማድረግ የጎላ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል፡፡

የክትባትና ተያያዥ ነገሮች ከፍተኛ አማካሪ ሙሉቀን ዮሐንስ (ዶ/ር) የክትባቱን ሁኔታ በተመለከተ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልስ፣ ‹‹ኢንስቲትዩቱ ያመረታቸው ክትባቶችን ከ70 በላይ አገሮች ተጠቅመውበታል፡፡ የጥራት ችግርም የለበትም፡፡ ክትባቱን በቅድሚያ ከሚያገኙ የጤና ባለሙያዎች መካከል የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ይገኙበታል፤›› ብለዋል፡፡

አንድ ሰው በተለያየ ቀናት ሁለት ጊዜ እንደሚከተብ፣ በዚህም መሠረት የመጀመርያውን ዙር ክትባት የተከተቡት ማኅበረሰቦች ከሁለትና ከሦስት ወራት በኋላ የሚመጣውን ሁለተኛ ዙር ክትባት በድጋሚ እንደሚከተቡ አማካሪው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

አሁን የመጣውንና ወደፊትም የሚመጣውን ክትባት የሚያስቀምጠውና ወደ የክልሎቹም ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያደርገው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ መሆኑን ገልጸው፣ ኤጀንሲው ለዚሁ ተግባር አገልግሎት የሚውሉና ማቀዝቀዣ ያላቸው መጋዘኖችና ተሽከርካሪዎች እንዳሉት ከሙሉቀን ዮሐንስ (ዶ/ር) ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...