Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልበሴቶች ቀን ሴት አርበኞች ሲታወሱ

በሴቶች ቀን ሴት አርበኞች ሲታወሱ

ቀን:

ይህች እመ-ገድል እመ-ድርሳን የሆነች ኢትዮጵያ በ19ኛውና በ20ኛው ምዕት ዓመት ከጣሊያን ጋር ሦስት ጦርነቶችን በዶጋሊ (1879 ዓ.ም. በአፄ ዮሐንስ ፬ኛ ዘመን)፣ በዓድዋ (1888 ዓ.ም. በአፄ ምኒልክ ፪ኛ ዘመን) እና በአምስቱ የፋሺስቶች ወረራ (1928-33 ዓ.ም. በአፄ ኃይለ ሥላሴ ፩ኛ ዘመን) አካሂዳ በድል ተወጥታለች፡፡

በሦስቱ ተጋድሎዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ በአትንኩኝ ባይነቱ እንደፀና፣ በእምቢኝ ለሀገሬነቱ እንደጀገነ፣ በእርመኛ አርበኝነቱ ወራሪን አሳፍሮ መልሷል፡፡ ከእነዚያ ገናና ተጋዳይ አርበኞች መካከል ሴቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዓድዋ የድል አንድ መቶ ሃያ አምስተኛ በዓል አስመልክቶ ባዘጋጀው የበይነ መረብ (ዙም) መድረክ፣ The Significance of Adwa for the Rest of the World በሚል ርዕስ የተናገሩት የታሪክ ምሁሩ ኦፊር ሃልቭሪ (/ር)፣  የጦርነቱ ዓውድን በገለጹበት ወቅት የሴቶች ተሳትፎና ጀግንነት ጎልቶ መታየቱን አውስተዋል፡፡ የተያዘው ወር (ማርች) የሴቶች ቀን የሚታሰብበት መሆኑን ጠቅሰው፣ እቴጌ ጣይቱ በተለይ የአንድ ጦር ክፍል አዛዥ እንደነበሩና አብነታዊ መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያውያን በአንድነት ጣሊያንን ድል በማድረጋቸው ኢትዮጵያን ከኃያላኑ ጎራ እንደትሰለፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

- Advertisement -

በዓድዋው ዘመቻ የሴቶች ተሳትፎ በወሳኝነት ይታወቃል፡፡ እቴጌ ጣይቱ ከአፄ ምኒልክ ጦር ጋር የራሳቸውን ፈረሰኛ ጦርና እግረኛ ሠራዊት እየመሩ ከመዝመታቸውም በተጨማሪ ለቁስለኞች የሚያስፈልገውን ዝግጅት፣ ለስንቅ የሚያስፈልገውን ምግብም አሰናድተዋል፡፡ በቤተ መንግሥት ያካበቱት ዕውቀት በጦር ሜዳም አገልግሏቸው ኖሮ፣ እንዳ ኢየሱስ ላይ ጣሊያን የመሸገበትን ለማስለቀቅ በኃይል ሳይሆን በብልሃት ብለው በነደፉት እቅድ መሠረት የእቴጌ ጣይቱ ጦር ጠላትን ማርኳል፡፡

ከእቴጌ ጣይቱ አንስቶ እስከ ታች ድረስ የነበሩት አገልግሎታቸው ለድሉ ስኬት ያስጠቅሳቸዋል፡፡ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት በነበሩበት ዐውደ ግንባር የታዘቡትን እንዲህ ጽፈውታል፡፡

በሴቶች ቀን ሴት አርበኞች ሲታወሱ

 

“ሴት አገልጋይ የተባለችው (የቤት ውልድ ነች ወለተ አማኔል የእንኮዬ ወለተ ማርያም ልጅ ከኛው ጋር ያደገች ነች) ከዘመቻው ላይ በጣም አገለገለች፤ ከቶ እሷ ባትኖር እንዴት እሆን ኖሯል፡፡ እያልኩ ዘወትር ሳስበው ያስደንቀኛል፡፡ እቃ ተሸክማ ስትሄድ ትውላለች፡፡ ከሰፈርን በኋላ ውሃ ቀድታ፣ እንጨት ለቅማ፣ ቂጣ ጋግራ፣ ወጥ ሰርታ ታበላናለች፡፡ ወዲያው እንደዚሁ ለማታ ታሰናዳለች፡፡ እንደዚህ የወለተ አማኔልን አገልግሎት እያሰብኩ ስደነቅ ደግሞ፣ በየሰፈሩ እንደዚህ እንደርሷ ስንት ሴቶች እንደሚያገለግሉ ይታሰበኛል፡፡

የሴቶቹን አገልግሎት ስገምት፣ ደግሞ የበቅሎቹ አገልግሎት ይታወሰኛል፡፡ በመጨረሻው ድምሩን ስገምተው፣ የዓድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮችና በበቅሎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል፡፡ ሁሉንም አያይዤ በደምሳሳነት ስመለከተው፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ነፃነቱን ጠብቀው እዚህ አሁን አለንበት ኑሮ ላይ ያደረሱት፣ እነዚህ የዘመቻ ኃይሎች መሆናቸውን አልስተውም፡፡

አዝማሪዎችም ለማጃገን አርበኛ ሆነው እየሸለሉና እየፎከሩ ተሠልፈዋል፡፡ ከሴቶች መካከል አዝማሪ ፃዲቄ አንዷ ናት፡፡ በባህላዊው ሥነ ጥበብ (ትራዲሺናል አርት) አዝማሪዋ  ፃዲቄ  እየሸለለችና  እየፎከረች  ስታዋጋ  የሚያሳይ ምናባዊ ሥዕል ተጠቃሽ ነው፡፡

ሁለተኛውን የጣሊያን ወረራ ለመቀልበስ፣ የኢትዮጵያን ነፃነትና ክብርን የሚሹ የጀግንነት መንፈስን የሰነቁ እርመኛ አርበኞችና ሕዝቡ በስምንቱ ማዕዝናት ተነስተው የአባቶችና የእናቶች የጀግንነት ጋሻ በማንገብ ከአምስት ዓመታት ተጋድሏቸው በኋላ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ድላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በእርመኛ አርበኝነታቸው የድሉን ሰንደቅ ከፍ ካደረጉት መካከልም ሴት አርበኞች ይገኙበታል፡፡

ከባላቸውና ከልጃቸው ጋር የዘመቱት አርበኛዋ ወ/ሮ ልኬለሽ በያን በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ ባለቤታቸው ሰማዕትነትን ሲቀበሉ ያዩትንና እሳቸው የፈጸሙትን ጀብዱ ማመልከታቸውን ፀሐይ ብርሃነ ሥላሴ፣ ኖርዝኢስት አፍሪካን ስተዲስ ባሳተመው መድበል ውስጥ “Women guerrilla fighters” በሚለው መጣጥፋቸው ገልጸውታል፡፡

በሰሜን የማይጨው ግንባር ከዘመቱት ሴቶች መካከል ከአርሶ አደር ቤተሰብ እስከ ልዕልታቱ ይገኙባቸዋል፡፡ “Africa and World War II” በሚል ርዕስ በአሜሪካ ካምብሪጅ ፕሬስ በታተመውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ስለነበረው አፍሪካዊ ገጽታ በሚተነትነው የጥናት መድበል ውስጥ / ኃይሉ ሀብቱ፣ “Fighting Fascism Ethiopian Women Patriots 1935 – 1941” በሚለው ጥናታቸው እንደጠቀሱት፣ ወ/ሮ ዘነበች ወልደየስ ባለቤታቸውን ተከትለው የዘመቱት አርበኛ ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙ ሲሆኑ፣ ሌላዋ ዘማች ልዕልት ሮማነ ወርቅ ኃይለ ሥላሴ ከባለቤታቸው ከባሌው ገዢ ጋር አብረው ከትተዋል፡፡

በተመሳሳይም የሸዋው ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ የልጅ ልጅ ልጅ / ላቀች ደምሰው ከባለቤታቸው ደጃዝማች መንገሻ አቦዬ ጋር የወንድ ልብስ ለብሰው ሽጉጣቸውን ታጥቀው ዘምተዋል፡፡ / ዘነበች ወልደየስ ከባለቤታቸው ከራስ አበበ አረጋይ፣ / ሸዋነሽ አብርሃ አርአያ ከባለቤታቸው ከደጃዝማች ኃይሉ ከበደ (ሌተና ጄኔራል) ጋር እንዲሁ ከትተዋል፡፡

/ ሸዋነሽ አባታቸው ደጃዝማች አብርሃ አርአያ የአፄ ዮሐንስ አጎት የራስ አርአያ ድምፁ ልጅ ናቸው፡፡ ባለቤታቸው ደጃዝማች/ዋግ ሹም ኃይሉ ከበደ እንደ አፄ ዮሐንስ አንገታቸውን በኢትዮጵያ ጠላቶች የተሰየፉ ናቸው፡፡ ፋሺስቶች ከሰየፏቸው በኋላ ጭንቅላታቸውን ወደ ሮም መስደዳቸው ይወሳል፡፡

የአፄ ዮሐንስ የልጅ ልጅ ልጅ፣ የልዕልት ከበደች ሥዩም መንገሻ ባለቤት ደጃዝማች አበራ ካሳ፣ ለፋሺስቶች እጅ መስጠትና መገደል፣ ልዕልት ከበደችን ከተዋጊነት አልመለሳቸውም፡፡ አርባ ወታደሮችን ይዘው ከሌሎች ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር ፍልሚያውን ተቀላቅለውታል፡፡

ስመ ጥር አርበኛውና ታሪክ ጸሐፊው አቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ፣ በ1948 ዓ.ም. በጻፉት “ሀገሬ የሕይወቴ ጥሪ” መጽሐፋቸው የአርበኛዋን ልዕልት ከበደች ሥዩምን ገድል ከዘረዘሩ በኋላ ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር ያስተሳስራቸዋል፡፡

“የሸዋን ቤተ መንግሥት መሥርተው ያቋቋሙ፣ በዓድዋም የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት እንዲነሣ ያደረጉና ድልም የመቱን እኒያ ደፋር በኃይለኝነታቸው የሚያንቀጠቅጡት ሴት እቴጌ ጣይቱ ናቸው” ብሎ ኮንተ አንቶነሊ ራሱ ጠላታቸው መሰከረላቸው፡፡ እንደዚሁ የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ጀግንነት የወረሱ ደፋር የሴት አርበኛ ወይዘሮ ከበደች ሥዩም መንገሻ ናቸው፡፡”

በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ ከአምስት አሠርታት በፊት በተጻፈው የአርበኞች ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ፣ ስማቸው ጎልቶ የተጠቀሰው ሴት አርበኛ ወ/ሮ አበባ በላቸው ናቸው፡፡ ወ/ሮ አበባ  ከባለቤታቸው ከሜታ ሮቢ ባላባት ልጅ ስመ ጥሩው አርበኛ ከልጅ ገርቢ ቡልቶ ጋር አራት ዓመት ከነራስ አበበ፣ ከነልጅ ኃይለ ማርያም ማሞ ጋር እስከ 5,000 በተቆጠሩ ወታደሮች ጋር ሆነው በመዘዋወር ጀብዱ የሠሩ ናቸው፡፡ የጀግንነት ቦታቸውም በሜታ ሮቢ፣ በዱላ ቆርቻ፣ በሰላሌ፣ በወሊሶና ዓባይ ዳር ነው፡፡ በአንድ ቀን 16 ጣሊያን ከባለቤታቸው ጋር አብረው ማርከው አስረክበዋል ይላል የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፡፡

የጠላትን ሁኔታ ለመሰለል፣ ምስጢራዊ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ፤ ሴቶች ከወንዶች የተሻለ ችሎታ ለማሳየታቸው አንዷ ተጠቃሽ የውስጥ አርበኛዋ / ሸዋረገድ ገድሌ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ተድላ ዘገየ እንደጻፉት፣ አርበኞች የአዲስ ዓለምን ምሽግ ደጋግመው ለማጥቃትና ለመጨረሻም ለማስለቀቅ የቻሉት በቆፍጣናዪቷ / ሸዋረገድ ገድሌ ድጋፍ ጭምር ነው፡፡

በሕክምና ሥራም የረዱ ብዙ ናቸው፡፡ ሰው በቆሰለ ጊዜ ደሙን አጥበው፣ መግሉን አጥበው፣ የተገኘውን የአገር ባህል መድኃኒት አድርገው፣ መግበውና ውኃ አጠጥተው ያድናሉ፡፡ የሞተባቸውም እንደሆነ ለማያውቁት ሰው ጭምር እርር ብለው አልቅሰው ቀባሪ ለምነው ያስቀብራሉ፡፡ ሕክምናን በተመለከተ / ስንዱ ገብሩና / ጽጌ መንገሻ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 

ወ/ሮ ስንዱ ባርበኝነት ጉዟቸው ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋራ በጣሊያኖች እጅ ከወደቁ በኋላ ለሁለት ዓመት ተኩል በጣሊያን ተግዘው ቆይተዋል፡፡ ከድል በኋላ በኢትዮጵያ ፓርላማ ለሕግ መምርያ ምክር ቤት ለሕዝብ እንደራሴነት በአዲስ አበባ ለጉለሌ አካባቢ ተወዳድረው በማሸነፍ ያገለገሉ ሲሆን እስከምክትል ፕሬዚዳንትነትም ደርሰዋል፡፡

በአምስቱ ዘመን በተለያዩ ግንባሮች በውጊያው አውድማ ውስጥ ከዘመቱት በሺዎች ከሚቆጠሩት ሴቶች መካከል ፊታውራሪ በላይነሽ ገብረ አምላክ አንዷ ናቸው፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለኢትዮጵያ ድል 75 ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ ያሳተመው ‹‹እኔ ለአገሬ›› መጽሔት የፊታውራሪ በላይነሽን ገድል ዘርዝሮታል፡፡

‹‹ጣሊያን አሁንም ዋጩ በሚባል አገር ለአሰሳ መጣ፡፡ ኃይለ ማርያም መብረቁ ለሚባሉ አርበኛ ወረቀት ጻፍኩና፣ ዕርዱኝአልኩ፡፡ እኔን ለመርዳት ብዙዎች ብረት ይዘው መጡልኝ፡፡ ለጋራሙለታው ሰው ለፊታውራሪ ሺመልስ ሀብቴም ወረቀት ጽፌ መሣሪያ ይርዱኝ ብዬ ላኩባቸው፡፡ እሳቸውም አንድ መትረየስና 15 ጠመንጃ ላኩልኝ፡፡ ከዚህ በኋላ አረበረከቴ የነበረውን ጣሊያንን እንዲህ እያልን እያቅራራን እንወጋው ጀመር፡፡

እናንተም ወዲህ እኛም

እንመጣለን

አረበረከቴ ላይ እንገናኝ፡፡

ተጋዳይ፣ ተጋዳይ፣ ተጋዳይ አርበኛ

ገዳይ እቁኒ ላይ ሾላ መገናኛ፡፡

ምናባቱ ፋሽስት፣ ምናባቱ

በረዢም ቁመቱ፣

በደንዳና ባቱ፣

እንወጋዋለን በገዛ ብረቱ፡፡

‹‹ጃንሆይ ከገቡ በኋላ እንደገና መጣሁና እየፎከርን ገብተን ጃንሆይን አገኘናቸው፡፡ እኔ ቀሚስ ለብሼ ከአርበኞቹ ተለይቼ ጃንሆይን እጅ ነሳሁ፡፡ የእኔ ዝና ቀድሞውንም ተሰምቶ ነበርና፣ ደጃዝማች ይገዙ ሀብቴ እጄን ይዘው ለጃንሆይ ጉድ ላሳይዎትብለው አቀረቡኝ፡፡ እኔም ቆንጆ ሆኜ የከተማ ሰው መስዬ ነበር የቀረብኩት፡፡

‹‹ጄኔቭ በነበርንበት ጊዜ፣ በላይነሽ የምትባለው ሴት ትዋጋለች እየተባለ የምንሰማው እሷን ነው?› ብለው ጠየቁ፡፡ ደጃዝማች ይገዙምአዎብለው አቀረቡኝ፡፡ ጃንሆይም በፈገግታ ተቀበሉኝ፡፡አለሽ እንዴ! ማን ትባያለሽ?› አሉኝ፡፡ እኔም፣ፊታውራሪ በላይነሽ ነኝአልኳቸው፡፡በስምሽ ተጠሪበትብለው ሹመቱን አፀደቁልኝ፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...