Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እየከበደን ነው!

ሰላም! ሰላም! አዲስ ያልነው ዘመን እንደ ቀልድ ይኼው አሮጌ ሊባል እየገሰገሰ አይደል? ይገርማል! ‹‹የለበስነውን ሸሚዝ መቀየር ከብዶናል ዘመን ግን መፈራረቁን ቀጥሏል፤›› በማለት ሰሞኑን በሐሳብ ሲብሰለሰል የሰነበተው አንዱ የእኔ ቢጤ ደላላ ነው። እንዲህ ከማለቱ አብሮን የነበረ ሌላው ወዳጃችን፣ ‹‹የተመቻቸው ምን አለባቸው? የኑሮ ውድነት አያጎሳቁላቸው፣ የቤት ኪራይ አያንገበግባቸው፣ የታክሲና የውኃ ወረፋ አያንገሸግሻቸው፣ ኤሌክትሪክ ጠፋ ብለው አይሳቀቁ፣ ኮሮና ቢያሳስባቸውም ስንቃቸውን ይዘው ስለመሸጉ ንኪኪ አይደርስባቸው፣ ሁሉም በእጃቸው ሁሉም በደጃቸው . . .›› አለን። በየምክንያቱ የምናነሳው ጉዳያችን የት ድረስ እንደሚለጠጥ አያችሁ? የባህሪያችንና የአኗኗራችን ጉዳይ ግን ኦዲት ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡ ‹‹ዘመን ሲለወጥ የማይለወጠው የሰው ልጅ ባህሪ ብቻ ነው፤›› እያለ የሚነግረኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር በዚህ ዘመን በተለይ ምን ያምርሃል ብትለኝ ስመ ፖለቲከኞቻችን የባህሪ ለውጥ እንዲያሳዩ ነው፡፡ የዛሬ 40 ምናምን ዓመታት የጀመሩትን ሒሳብ ሳያወራርዱ፣ አምሳያዎቻቸውን ፈጥረውብን ሌላ ጽንፍ ውስጥ እያስገቡን ነው፤›› ሲለኝ ሰነበተ፡፡ ‹‹ከሥልጣን ግብግብ በተጨማሪ ጥንቃቄ ወደሚያስፈልገው የሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ዘው ተብሎ የሚገባበት ነገረኛነትና የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭት መስፋፋት ውስጥ፣ ነገረ ሥራቸው መላ ካልተፈለገለት ውጤቱ ለማንም አይበጅም፤›› ብሎ ዝም አለ፡፡ ሃይማኖትና ፖለቲካ የተለያዩበት አገር ውስጥ፣ ከምንም ነገር በላይ የሕዝብ ደኅንነትና ጤና አሳሳቢ በሆነበት ጊዜ፣ ፖለቲከኞቹን የሚያራኩታቸው ነገር ምን እንደሆነ አልገባንም፡፡ ሳይገባን እንደገባን ባናስመስል ይሻለናል!

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የመስጠት ችሎታና አቅም ስላልነበረኝ ሐሳቤን ለወር ቀለብ የሚያስፈልግ የቤት ወጪ ዝርዝር ላይ ጣድኩት። ሰብስቦ ለመበተን ጠብ ሲል ለመድፈን አይደል የእኛ ኑሮ? በቃ! አንዱ የሠፈራችን ዘናጭ፣ ‹‹እየተለወጠ ያለው ‘ስታይላችን’ እንጂ ‘ስታተሳችን’ አይደለም›› የሚል አባባል አለው። የሚገርማችሁ ታዲያ ከሁለቱ የእንግሊዝኛ ቃላት የማውቀውና ቶሎ የሚገባኝ ‘ስታይል’ የሚባለው ነው። “አቦ ‘ስታይል’ ይኑርህ!”፣ “ስታይለኛ’ ነው እሱ” ማለት የዘወትር ልማዳችን ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፣ በይሉኝታ የታሰረው አኗኗራችን ውጤት ጭምር ይኼንን ቃል በደንብ እንዳውቀው ሳያግዘኝ አልቀረም መሰለኝ። ወሰብሰብ ካለው ነገር ወጥተን እንዲህ ባሉት ነገሮች ዘና ማለት ብንጀምር እኮ ቀለል ይለን ነበር፡፡ ዝም ብዬ ሳስበው የሕይወታችን መስመር ቀያሽ የሆነው አስተሳሰባችን ላይ ካልሠራን አያያዛችን አሁንም ወደፊትም አሥጊ ነው። ‹‹ምን ዋጋ አለው? ዘናጭ ከተማ ገንብተው ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብ ሳያስተካክሉ መውረግረግ?›› የምትለው ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ናት፡፡ ቆይ እስቲ ብዙ ጊዜ ስለኢንቨስትመንት ሲወራ ቁሳዊው ነገር ላይ እንበረታለን፡፡ ለአስተሳሰብና ለአመለካከት ምጥቀት ኢንቨስትመንቱ የታለ? ጥያቄ ነው ብቻ ነው የማቀርበው፡፡ መልስማ ከየት መጥቶ!

እንደምታውቁት የዘመኑ ጨዋታ ዕድሜ ለኢንተርኔት በመረጃ ሆኗል። ምን ሆነ መሰላችሁ? በዚህ አስጨናቂ ጊዜ በስንት መከራ በተገኘ ሥራ ውዷ ማንጠግቦሽ የለመደችው እንዳይቀርባት፣ “ሮጥ ሮጥ ማለት አለብኝ” አልኩና ተፍ ተፍ ማለት ጀመርኩ። የእኛ ነገር ምን ዓይነት ስም ቢወጣለት እንደሚሻል አላውቅም ወዲያው የሚያደናቅፈኝ በዛ። ማንጠግቦሽ ደወለች። “ምን ሆንሽ?” ስላት ሠፈር ውስጥ በጠና ታመው ሲጠበቁ የነበሩ አዛውንት ማረፋቸውን አረዳችኝ። የኑሮ መርዶ በዝቶ ነው መሰል የሰው ሞት ማርዳት እንዲህ ቀላል ይሁን? “እና?” አልኳት እንዳትጠራኝ ፈጣሪን እየተማፀንኩ። “ቶሎ መጥተህ አብረን እንድረሳ፤” ተባልኩላችሁ። በዚህ ጊዜ እንደ ወትሮው ለቅሶ ተቀምጠን እንዴት እንደምንዘልቀው አላውቅም። እሱ ብቻ አይደለም አያ ሞት አጅሬው በዚህ ኑሮ ውድነት ላይ ኮሮናን አስከትሎ ምን እንደሚያጀግነው አልገባኝም። በቅጡ ካስተዋላችሁ ኑሮ ሲከብድ ሞት ይበዛል። ምንም እንኳን ማኅበራዊ የትስስር ገጽ ማኅበራዊ ኑሮውን ቢተካውም፣ ሰው ያለ ሰው አይኖርምና እየተነጫነጭኩ ደረስ ብዬ ለመምጣት ከነፍኩ። ለቅሶ ሳሳድድ ባዶ እጄን እንዳልቀር ነዋ!

ቆይቼም የባህልና የወግ ተፅዕኖን ለያይቼ ለማሰብ እየሞከርኩ ራሴን ለማፅናናት ብዙ ጣርኩ። ድንገት ግን ‘ቆይ ብቀርስ?’ ብዬ መሀል መንገድ ላይ መመለስ ጀመርኩ (ሰው ለካ ወዶ አያብድም እናንተ?)፡፡ የዘንድሮ ሰው እንኳን መንገድ ሰጥተውት እንዲያውም እንዲያው ነው፡፡ አሁን ለቅሶ ቀረ ብሎ መንደርተኛው ሰው ሊያደርገኝ ነው? ብዬ ሳስብ ወደ ሥራ ያዞርኩትን እግሬንና ቀልቤን ወደ ለቅሶ ቤት ቀለበስኩት። አንዱን ሲነሳ አንዱን አያሳጣም፡፡ ለቅሶ ቤት ቁጭ ብዬ ሰው በሹክሹክታ የሚነጋገረውን እየሰማሁ ፈታ አልኩ። በሐሜትና በአሉባልታ የተከበበ ከመሆኑ ባሻገር እውነተኛው የንግግር ነፃነት፣ እውነተኛና ነፃ የሕዝብ ፓርላማ ማለት እንዲህ ያለው መድረክ ነው እስክል ድረስ። አንዳንዴ ሳስበው በሰነፎች የተሞላው መንግሥታችን በቋንቋም በባህሪም ከማያውቃቸው አገሮች ሳይቀር የተለያዩ ተሞክሮዎችን ከሚያሰባስብ፣ የለቅሶ ቤቱን እሴት ሳይንሳዊ ለማድረግ ቢጥር ዴሞክራሲያችን ባልቀጨጨ ያስብላል እኮ። ሰሚ ጠፋ እንጂ እሱስ ሲባል የኖረውማ ‘የሰው ወርቅ አያደምቅ’ ነበር!

  እናላችሁ ለቅሶ ቤት ብቀመጥም ቀልቤና ሐሳቤ እኔ ዘንድ አልነበሩም። በጎን ሞባይል ስልኬ ያለማባራት እየጮኸ ይበጠብጠኛል። እነሳለሁ፣ እቀመጣለሁ። ‘መጣሁ’ እላለሁ እዋሻለሁ። ይህን ያዩት አዛውንቱ ባሻዬ፣ “አንበርብር ኔትወርክ ተመርጦ መሰጠት ጀመረ እንዴ?” ብለው ሳቁ። ሰውን የሚያንቆራጥጠው የኔትወርክ ዕጦት እኔ ስልክ ላይ አለመከሰቱ የገረማቸው ይመስላሉ። “እባክዎን በጠፋ ሥራ አንድ አግኝቼ ስሮጥ ነው የመጣሁት፤” አልኳቸው። ይኼን ጊዜ፣ “እኔ የምለው የ‘ቫት’ ክፍያውን መንግሥት ዘንድ ሄደን እናወራርደዋለን። እንዲህ ለሟች በማይጠቅምና ቋሚን በማያበረታ ጊዜ ማጥፋት የምናቃጥለው ዕድሜ ግን የት ይሆን የሚወራረደው?›› ቢሉኝ ሳቄ መጣብኝና ሰው እስኪታዘበኝ ድረስ ላለመሳቅ ታገልኩ። ማንጠግቦሽም ከሩቅ ዓይታኝ ኖሮ መሰስ ብላ መጥታ፣ “ኧረ አንተ ሰውዬ! ሰው ሲሞት የሚስቅ ቀጣዩ ሟች ነው ይባላል እኮ፤” ስትለኝ ባሰብኝ። ጭራሽ ዕጣ ወጥቶልኝ ይረፈው? ጉድ እኮ ነው ዘንድሮ እባካችሁ!

እየቆየሁ የሞት ፍርኃት ወረሮኝ (ሰው ሲሞት ነው ሞት እንዳለ ትዝ የሚለን) መጨረሻውን ሳላይ የምለው ነገር በዛብኝ። ‘እስኪ አስቡት አልወለድ ያለውን ዴሞክራሲያችንን መጨረሻ፣ አንበላም አንጠጣም ብለን ያዋጣንለትን የህዳሴ ግድባችንን መጠናቀቅ ሳላይ እንዲህ እንደ ቀልድ ጭልጥ? “ዘራፍ አንበርብር!” ስል፣ “ኧረ ጠላትህ!” አሉኝ ባሻዬ። ለካስ ድምፄን ከፍ አድርጌው ኖሯል። ሊሞት አምስት ደቂቃ ብቻ ቀረው የተባለ ሰው በሞት ፍርኃት ፈንታ አምስቱን ደቂቃዎች ለተለያዩ ክንዋኔዎች ከፋፍሎ እንዴት ሊጠቀምባቸው እንደ ሞከረ የባሻዬ ልጅ ያጫወተኝ ትዝ ቢለኝ ደግሞ እመር ብዬ ተነስቼ ወደ ሥራዬ ገሰገስኩ። ታዲያስ! ህያው ለመሥራት መሮጥ እንጂ ለሙታን ሲያለቅስ መኖር አለበት እንዴ? ‘ነፍስ ይማር’ ማለትን አረሳሁም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር አዕምሮዬን ሰቅዞ ይዞታል፡፡ የዛሬ ህያው የነገ ተከታይ መሆኑን ባይረሳ የሚል ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በኮሮና ከሚለዩን ወገኖቻችን በተጨማሪ በምግብ ዕጦት፣ በተለያዩ ደዌዎች፣ በትራፊክ አደጋና በሌሎች ምክንያቶች የሚለዩንን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ቀዳሚና ተከታይ ነንና በሕይወት እያለን መተሳሰቡ ይበልጣል፡፡ ልብ እንግዛ ለማለት ነው!

ደላሎች የምንሰበሰብበት ሥፍራ ስደርስ አካባቢው ቀውጢ ሆኖ ነበር የጠበቀኝ። “ምንድነው እሱ አካባቢውን መካከለኛው ምሥራቅ ያስመሰላችሁት?” ብዬ ብጠይቅ አንዱ፣ “ምነው አንበርብር? መፍትሔ የታጣለትን የሞት ቀጣና ከእኛ ጋር ታመሳስለው?››” አይለኝ መሰላችሁ? ‘ከሰው ጋር ሲኖሩ ተቻችሎ ነው፣ አጥሩም ግድግዳውም ነገረኛ ነው’ ብለው ባሻዬ የሚተርቱት ተረት ወዲያው በአዕምሮዬ አቃጨለና ያላሰብኩትን ያሳሰበኝን ወዳጄን ይቅር ብዬው ሄድኩ። ምን ዘንድሮ እልፍ እያሉ ካልሆነ አየሩ ደስ አይልም። እልፍ ከማለቴ ደለብ ያለ ረብጣ የሚቆጠርባቸው ሥራዎች በመሳሳታቸው ምክንያት ምድረ ደላላ አፉን ከፍቶ ቢውልም፣ አንድ ደህና ሥራ የቀናው ወዳጄ በአጋጣሚ ያገኘውን ሥራ ለእኔ አስተላለፈው። በደላላ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ደግነት ሳይ እኛ ከክፋትና ከምቀኝነታችን ጀርባ፣ የመተሳሰብና የቀናነት ባህሪ ባለቤቶች መሆናችን ገባኝ። ደግሞ መልሼ እንዲህ ያለው መተሳሰብ ርቆን በአገሩ ራስ ወዳድነት በዝቶ፣ ለዘመናት በችግር ላይ ችግር ስንሸምን መኖራችንን አሰላሰልኩና ዝም አልኩ፡፡ ሌላ ምን ይባላል? እንዲህ በሐሳብ ከሙቅ ወደ ቀዝቃዛ፣ ከቀዝቃዛ ወደ ሙቅ ስናውዝ ሳለሁ ራሴን አንድ ጥያቄ ጠየቅኩት፡፡ ‘ለምን ይሆን የማይከፈልበትን ደግነት ስንሸሽ እየኖርን ለክፋት የምንከፍለውን ዕዳ ‘የምናበዛው?’ ስል። እውነቴን አይደል? እስኪ እንነጋገርበት!

እናላችሁ አዲስ የተባለ ‘ግሬደር’ ሊገዛ የሚችል ሰው ፈለግ ፈለግ ሳደርግ ቆየሁ። እንደ ቀልድ ‘ፈለግ ፈለግ’ አልኩ እንጂ እኔ አዲስ አበባን ያካለልኩትን ያህል ቫስኮ ደጋማ ዓለምን አልዞረም ብል ይቀል ነበር። የጠበቅኩትና የለመድኩት ዓይነት ሰው ግን አልገጠመኝም። ገዥ የተባለችው በጣም ወጣት ናት። ልቤ ‘አንበርብር በከንቱ እንዳትለፋ ተጠንቀቅ’ ሲለኝ፣ “እንዴት ነው ቢዝነስ ላይ የወጣት ሴቶች ተሳትፎ እያደገ መጣሳ?” ብዬ ፌስቡክ ያሳደረብኝ ተፅዕኖ እንዳይታወቅብኝ አድርጌ ጠየቅኳት። እሷም ሁኔታዬን ዓይታ ነገሬ ገባት መሰል፣ “ያለፈውን ጊዜ የጭቆናና የግፍ ዘመን ቆጥሮ ይሆናላ!” ብላ ከምፀት አዘል ፈገግታ ጋር መለሰችልኝ። እየቆየን የበለጠ ስንግባባ ቤተሰቦቿ እያገዟት እንዲህ ያለ ‘ቢዝነስ’ ውስጥ እንደገባች አጫወተችኝ። ‘ወንድ ባለ በዕለት ሴት ባለች በዓመት’ የሚሉት ኋላቀር አባባል ሲያልፍ የማይነካት ይህች ታታሪ ወጣት፣ ማሽኑን በደንብ አስፈትሻና በቅድመ ሁኔታዎች ላይ ተደራድራ እንደምትገዛው ስታሳውቅ እኔ ግራ ገባኝ። ምን ግራ የሚያጋባ ነገር አገኘህ አትሉኝም እንዴ? ወሬና ፍቅር እኮ ከአንድ ወገን ሲሆን ጥሩ አይደለም። ከጠየቃችሁኝ ግራ የገባኝ ፈርጀ ብዙው እየሆነ የመጣው የወጣቶች ሕይወት ነው። ገሚሱ ራሱን ለማሻሻል ‘ፀሐይ ሳለ ሩጥ አባት ሳለ አጊጥ’ እያለ ዕድሜውን በአግባቡ ለመጠቀም ሲጥር ታዩታላችሁ። ይማራል፣ ይሠራል፣ ይጥራል፣ ይደክማል። ገሚሱ ደግሞ ትርጉም በሌለው ወሬ ተወጥሮ አገር ላይ መርገምት ለማምጣት የሐሰት መረጃ ይረጫል። በዘረኞችና በሴረኞች ተታሎ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቶ አገር ያተራምሳል። ለሁሉም ማስተዋል ይስጥ እንጂ ሌላ ምን ማለት ይቻላል!

ከመልከ መልካሟ ታታሪ ወጣት ልጅ የተበረከተልኝ የኮሚሽን ገጸ በረከት የሚነገርም አይደል። ከጎልማሳነቴ ጋር አብሮ ጨዋታዬ ስለጣማት በቆይታዋ ተደስታለች። በጥሩ ሁኔታ ስላሳለፍነው የአብሮነት ጊዜያችንን ጭምር ታሳቢ አድርጋ ‘ቦነስ’ ጀባ ብላኝ ስንለያይ፣ የባሻዬን ልጅ ደውዬ በማኪያቶ ተጀምሮ በቢራ ለሚጠናቀቀው ወሬ ቀጠርኩት። ያራዳ ልጅ እኮ ብቻውን በልቶ አያውቅም! ‘. . . ሲያገኝም ያበላል ሲያጣም ያዝናል ሆዱ’ እኮ ነው ግጥሙ። ከባሻዬ ልጅ ጋር ስንስቅ ስንጫወት ሸጋ ጊዜ በማሳለፍ ላይ እንዳለን በድንገት፣ “ስማ እንጂ አንበርብር?” ሲል ቀልቤን ሰበሰበው። “እየሰማሁ ነው…” ስለው፣ ‹‹እንዲህ የምንስቅና የምደሰተው ሠርተን በምናገኘው በላባችን ፍሬ ብቻ ይመስልሃል?” ብሎ ያላሰብኩትን ጠየቀኝ። “ምን ይሆን ሌላው?” ብዬ መልሼ ጠየቅኩት። “ሰላም!” አለኝ። “አስተማማኝ ባይሆንም አገሩ አንፃራዊ ሰላም፣ ውስጣችን መለስተኛ ሰላም፣ ቤታችን ሥጋት ቢኖርም በመጠኑ ሰላም ቢሆን ነው እንጂ። እስኪ ከእነ ጭራሹ ሰላም አጥተው እርስ በእርስ እየተላለቁ የዓለም ሕዝብ መነጋገሪያ የሆኑትን አስባቸው? ወደው መሰለህ ሰላም ተሰናበቶባቸው ነው እንጂ፤” አለኝ። እውነት ነው። አስተናጋጃችን የባሻዬን ልጅ ሰምቶት ይሁን አላውቅም የመሐሙድ አህመድን ‘ሰላም ለሰው ልጆች!’ ዘፈን ደመቅ አድርጎ ከፈተው። እኛም ‘ሰላም ለሰው ልጆች! ሰላም ለአገራችን!’ እየተባባልን አሞቅነው።

በዚህ መሀል አንዱ፣ “ሰላም የሚገኘው በማስገደድ ጉልበት ውስጥ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ድርድር ብቻ ነው፡፡ ይልቁንስ በሰላም ስም እየተሳበበ ስለሚፈጸመው ማኬያቬላዊ ድርጊት መጥፎነት እየተነጋገርን፣ ሁሉንም ወገን በእኩል አሸናፊ ስለሚያደርገው ሰላም እናስብ፤” ሲለን ከቁጣው በቀር አስተሳሰቡ የመጠቀ መሰለኝ፡፡ ሰውዬው ዲስኩሩን ሲቀጥል የባሻዬን ልጅ፣ “ይህ ሰው ምን እያለ ነው?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡ የባሻዬ ልጅም የጠጠረው ሐሳብ እንዳልገባኝ ተረድቶ፣ “ሰውየው የሚለው ሰላምን ለማስፈን ሰላማዊ ሆነን እንቅረብ ነው የሚለው፡፡ ማኬያቬላዊ ያለው በአሻጥርና በተንኮል ከተተበተበ መንፈስ ተላቀን በጋራ በሰላም እንጠቀም ማለቱ መሰለኝ፤” ሲለኝ አሁን ገና ገባኝ፡፡ ‹‹ሰማህ አንበርብር ዙሪያህን ተመልከት፡፡ ሁሉም ቦታ ቅራኔ አለ፡፡ ቤተሰብ ውስጥ፣ በወዳጆች መሀል፣ ሃይማኖት ውስጥ፣ ትምህርት ቤትና በመሳሰሉት ሥፍራዎች ያልተወራረዱ ሒሳቦች አሉ፡፡ በአገሪቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት ያልተወራረዱ የፖለቲካ ሒሳቦችና አሁን ደግሞ ከብሔርተኝነት ጋር የሚደመሩት ችግሮች የሰላም ጠንቅ መሆናቸውን አትዘንጋ፡፡ የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣ የመልካም አስተዳደርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ጥያቄዎች ሳይወራረዱ የተገባበት ሌላ ዙር አንጃ ግራንጃ ያስፈራል፤” ሲለኝ ሁሉም ነገር ግልጽ ሆነልኝ፡፡ ‹‹እስኪ ያልተወራረዱ ሒሳቦች በሰከነ መንፈስ ተወራርደው ለአገር ግንባታ መሠረት እንጣል፡፡ በኮሮና ላይ የሚደረቡ የምርጫ ያልተወራረዱ ሒሳቦች አያደነቃቅፉን፡፡ ግብፅ አሜሪካን ከጀርባዋ አሠልፋ እያጉረጠረጠች እርስ በርስ አንተነኳኮስ፡፡ ከጠብ ግድግዳዎች ይልቅ የፍቅር ኮሪደሮች ይብዙ፡፡ ቀዳሚና ተከታይ በማይታወቅበት ምድራዊ ሕይወታችን ከክፋት ይልቅ ለደግነት ሰፊ ጊዜ እንስጥ፡፡ ነገሮች እየከበዱ ነውና እንተሳሰብ…›› ሲልም በሰመመን ይሰማኛል፡፡ አዎን እየከበደን ስለሆነ ይታሰብበት፡፡ መልካም ሰንበት!            

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት