ኢትዮጵያ ወደ ምርጫ የሚወስደውን ጎዳና ተያይዛዋለች፡፡ ምርጫው የይስሙላ እንዳይሆን ግን የምርጫው ተዋንያን ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በአገርና በሕዝብ ላይ የተቀለደው ይበቃል፡፡ በሠለጠነ ዘመን ውስጥ እየኖሩ እንዳልሠለጠነ መሆን አሳፋሪ በመሆኑ፣ ከፊታችን የሚጠብቀንን ምርጫ በከፍተኛ ኃላፊነትና ብቃት ለማከናወን መዘጋጀት ግዴታ መሆን አለበት፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪዎች፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሲቪል ማኅበረሰቡ፣ ሚዲያውና ሌሎች የምርጫው ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ አካላት በሙሉ ዘመኑ የሚጠይቀው ደረጃ ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ዘመኑን የማይመጥን ቁመና ላይ ተቸንክሮ መቅረት አያዋጣም፡፡ የአገሪቱ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይከበር፡፡ ሕዝብ ሲከበር በነፃነት የሚፈልገውን እንዲመርጥ ዕድሉ ይመቻችለታል፡፡ የምርጫው ፉክክር ትኩረቱ ጡንቻ ሳይሆን የሐሳብ ልዕልና መሆን ይኖርበታል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ እየኖሩ ኋላቀር ድርጊቶች ላይ መገኘትም ሆነ አስተሳሰብን አለማዘመን አሳፋሪ ነው፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረው ሰላማዊና ተዓማኒ ምርጫ ማከናወን የሚቻለው፣ ዘመኑ የደረሰበትን የአስተሳሰብ ደረጃ መጎናፀፍ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ አማተር ድርጊቶችና የዘመኑን አስተሳሰብ የማይመጥኑ ተግባራት መገታት አለባቸው፡፡ ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋራ እኩል መራመድ አለመቻል ያስንቃል፡፡ ዘመኑን ሳይመጥኑ አደባባይ መውጣት አሳፋሪ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ሕዝብ ይከበር፡፡
የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰው እንደ 15ኛው ክፍለ ዘመን ሰው ልሁን ካለ ችግር አለ፡፡ ያለንበት ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ ምጡቅ አዕምሮ ውጤት የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ዓለምን ጠባብ መንደር እያደረጉ ሲሆን፣ ለማመን የሚያዳግቱ በርካታ አስደማሚ ተግባራትም ይከናወኑበታል፡፡ የሰው ልጅ አዕምሮ እጅግ በጣም ከመዳበሩ የተነሳ፣ በደቂቃዎችና በሰከንዶች ልዩነት አስገራሚ ክስተቶች ይስተዋላሉ፡፡ የዘመኑ ዕውቀት በበለፀጉ የሳይንስ ንድፈ ሐሳቦችና የተግባር ልምምዶች የተጠናከረ በመሆኑ፣ በዓለም ዙሪያ ጥራት ያላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች በስፋት እየተዳረሱ ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በወታደራዊ፣ በሕክምና፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ ወዘተ መስኮች የታላላቅ ክንውኖች ባለቤት የሆኑ አገሮች በሀብት ላይ ሀብት ሲደራርቡ፣ ተመሳሳይ ጎዳና የያዙ ታዳጊ አገሮችም እየተሳካላቸው ነው፡፡ በዚህ ዘመን በድህነት፣ በኋላቀርነት፣ በግጭትና በመሳሰሉት ከንቱ ነገሮች ውስጥ መገኘት ያስንቃል፡፡ ይህንን የምጡቅ አዕምሮ ዘመን ሳይጠቀሙበት አክሳሪ ድርጊቶች ውስጥ መገኘት ሕዝብ መናቅ ነው፡፡ ሕዝብ ይከበር፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ዘመን የማይመጥን ድርጊት ውስጥ መገኘት የለብንም፡፡ በቀና መንፈስ ታሪካችንን መርምረን የተበላሹትን በማስተካከልና አኩሪ የነበሩትን በማጠናከር፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት መቆም ከቻልን ተዓምር መሥራት አያቅተንም፡፡ ከ110 ሚሊዮን በላይ ከሚሆነው አጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ታዳጊዎችና ወጣቶች መሆናቸው ትልቅ ተስፋና ዕድል ነው፡፡ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ መገኘታቸው፣ ለኢትዮጵያ ትንሳዔ ትልቅ መልዕክት አለው፡፡ በልሂቃኑ መካከል የሰፈነውን የዘመናት መናናቅ፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና አጓጉል ድርጊቶችን ፈር ማስያዝ ከተቻለ ለሰላምና ለመረጋጋት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት በጋራ አብሮ የመኖርና አገር የመውደድ ታላቅ ፍቅር በዚህ ትውልድ ማስቀጠል የሚቻል ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር እንደምትሆን አያጠራጥርም፡፡ ይኼንን መልካም ምኞት ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው ግን ኋላቀር ድርጊቶችንና አስተሳሰቦችን በማስወገድ ነው፡፡ ዘመኑን በሚመጥኑ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች መተካት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ሕዝብን ማክበር ያስፈልጋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ አገር የሚመሩ፣ በዲፕሎማሲ የተሰማሩ፣ የፖለቲካ ፓርቲ የሚያደራጁም ሆነ የሚመሩ፣ በተለያዩ መስኮች አገራቸውን የሚያገለግሉ፣ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙም ሆኑ ሌሎች አስተሳሰቦቻቸውን ማዘመን ይጠበቅባቸዋል፡፡ አስተሳሰብ ሲዘምን ድርጊትም ይዘምናል፡፡ አስተሳሰብና ድርጊት ሲዘምኑ ከዘመኑ ጋር የማይመጥኑ ነገሮች በሙሉ ይወገዳሉ፡፡ በዘርና በተለያዩ ጉድኝቶች ተቧድኖ ሌሎችን ማጥቃት፣ መዝረፍ፣ መግደል፣ ማፈናቀልና የመሳሰሉት ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ ይልቁንም በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሕዊነት የሚኖሩበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ የሕግ የበላይነት የሁሉም መመኪያ ይሆናል፡፡ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ይናቃሉ፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰው አዕምሮው በዕውቀት የዳበረ ስለሆነ፣ ማንም እየተነሳ በቀደደው ቦይ አያፈሰውም፡፡ እንደ መንጋ እያሰማራ ለጥፋት አያውለውም፡፡ መቼ? የት? ለምን? እንዴት? ምን? የመሳሰሉትን ወርቃማ ጥያቄዎች ይዞ ይሞግታል እንጂ፣ የተነገረውን ሁሉ አንጠልጥሎ በስሜት አይነዳም፡፡ ኢትዮጵያዊያን በዚህ በሠለጠነ ዘመን ከአሉባልታና ከሐሜት ይልቅ፣ በመረጃና በማስረጃ የተጠናከረ እውነት ነው መፈለግ ያለባቸው፡፡ የሠለጠነው ዓለም እንዲህ ነው ተከብሮ የሚኖረው፡፡ ሕዝብ ይከበር፡፡
በራሳቸው ለመቆም የማይቻላቸው ደካሞች በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ መደበቅ ስለሚወዱ፣ ለነውረኛ ድርጊቶቻቸው የማያግዟቸው የዋሆችን ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ሲሉ ሁሉንም ነገር ከሰብዓዊ ፍጡር በተቃራኒ ግዑዝ ያደርጋሉ፡፡ በማንነት ውስጥ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ነፍሶች የሌሉ ይመስል፣ ብሔሩን ወይም ብሔረሰቡን አግዝፈው ግለሰቡን ይጨፈልቁታል፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ልዩነትን ለማጉላት ደግሞ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት፣ ወዘተ እያሉ ይከፋፍላሉ፡፡ ሰው በባህሪው የራስ የሚለው ጉዳይ የሌለው ይመስል ድምፁን ይውጡበታል፡፡ ለቀለም፣ ለሙዚቃ፣ ለውበት፣ ለምግብ ወይም ለሌላ የራሱ ምርጫ ዕድል አይሰጡትም፡፡ በስመ መብት ተሟጋችነት የጠረነፉትን ስብስብ እንደ ሎሌ ይጠቀሙበታል፡፡ እርግጥ ነው የሰው ልጅ የራሱ የሆነ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነትና የመሳሰሉት ይኖሩታል፡፡ ነገር ግን ራሱን እዚያ ውስጥ ብቻ አጥሮ እንዲኖር ማስገደድ ወይም ማታለል ወንጀል ነው፡፡ አንድ ሰው ከኢትዮጵያ አንዲት ገጠር ውስጥ ወጥቶ በችሎታው ብቻ የአሜሪካ፣ የጀርመን ወይም የሩሲያ ሳይንቲስት ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ዓለም እንደ መንደር በጠበበችበት በዚህ ዘመን፣ የምጡቅ አዕምሮ ባለቤቶችን ፈላጊዎቻቸው በጣም ብዙ ናቸው፡፡ የእነዚህን ሰዎች መብት እየተጋፉ ዕድላቸውን ማበላሸት ለዚህ ዘመን አይመጥንም፡፡ ለዓለም የሚተርፍ ጭንቅላት ሊኖረው የሚችልን ሰው መንደር ውስጥ እንዲቀር ማድረግ ነውር ነው፡፡ ወጣቶችን ማብቃት ሲገባ የከንቱ ዓላማ ተሸካሚ በማድረግ በሕይወታቸው መቀለድ፣ ለዘመኑ የማይመጥን ነውረኛ ድርጊት ነው፡፡ ሕዝብን አለማክበር ውጤቱ ውድቀት ነው፡፡
አገራቸውንና ሕዝባቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን ከሴራ፣ ከተንኮል፣ ከጥላቻና ከቂም በቀል የፀዱ ናቸው፡፡ በገዛ ወገናቸው ላይ በደል አይፈጽሙም፡፡ እናት አገራቸውን የመከራ ቋት አያደርጉም፡፡ ለባዕዳን ፍርፋሪ ሲሉ የአገራቸውን ሚስጥር አሳልፈው አይሰጡም፡፡ አገራቸው የሰላም፣ የብልፅግና፣ የደስታና የዴሞክራሲ አምባ ሆና ሕዝባቸው በነፃነት እንዲኖር መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ በሕዝብ ደም እየነገዱ ሥልጣን፣ ክብርና ሀብት አያጋብሱም፡፡ በቅናትና በምቀኝነት ተነሳስተው ወዳጆቻቸውን አያጠፉም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ያሉት ግን መታወቂያቸው መግደል፣ ማፈናቀል፣ መከፋፈል፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ማነሳሳት፣ መዝረፍ፣ አገርን መዳከምና የመሳሰሉት ዕኩይ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን አስተሳሰብ ይዘው ክፋት ይዘራሉ፡፡ አዲሱን ትውልድ ይመርዛሉ፣ የአገር ሰላም ያቃውሳሉ፣ በዕድገት ፈንታ ውድቀት ያጣድፋሉ፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር ስለሌላቸው አንደበታቸው የሚተፋው መርዝ ነው፣ ከአገር አንድነት ይልቅ ስለመነጣጠል ይደሰኩራሉ፣ ስለተጠናከረች ኢትዮጵያ ሳይሆን ስለምትፈራርሰው ኢትዮጵያ ነጋ ጠባ ይሰብካሉ፡፡ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው ከዘመኑ ጋር ስለማይመጥን፣ የሚያሴሩት ሁሉ በግልጽ ይታወቃል፡፡ አገራችሁንና ሕዝባችሁን ከልብ የምትወዱ ኢትዮጵያዊያን ግን፣ በግልጽና በድፍረት ወጥታችሁ ዘመኑን እንደምትመጥኑ በተግባር አሳዩ፡፡ ወጣቶችን በዕውቀት ለማነፅ ትጉ፡፡ ለማይረባ የፖለቲካ ዓላማ ሲሉ አልባሌ ቦታ እንዲውሉ አትፍቀዱ፡፡ መጪውን ምርጫ ከጠብ፣ ከሴራና ከውንብድና ድርጊቶች የነፃ ለማድረግ ታገሉ፡፡ አስተሳሰቦቻችሁና ድርጊቶቻችሁ ዘመኑን እንደሚመጥኑ አስመስክሩ፡፡ ዘመኑ የደረሰበት ከፍታ ላይ አለመገኘት አሳፋሪ መሆኑን ተገንዘቡ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተከብሮ እንዲኖር ታገሉ!