Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዜማ ከዕጩዎች ምዝገባ ጋር ለደረሰበት መጉላላት ቦርዱንና መንግሥትን ወቀሰ

ኢዜማ ከዕጩዎች ምዝገባ ጋር ለደረሰበት መጉላላት ቦርዱንና መንግሥትን ወቀሰ

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል በበርካታ የምርጫ ክልሎች ቢሮ በወቅቱ ባለመከፈቱ፣ በፀጥታ ችግርና በመዝጋቢዎች ተባባሪ አለመሆን ምክንያት በርካታ ዕጩዎቹን ማስመዝገብ አለመቻሉንና መጉላላት ተጠያቂው ወይም ተወቃሹ መንግሥት መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አስታወቀ፡፡

ፓርቲው ይህንን ያስታወቀው ዓርብ መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮችና ከዕጩዎች ምዝገባ ጋር የገጠሙትን ተግዳሮቶች ለማሳወቅ፣ ለአገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙኃን በዋና ጽሕፈት ቤቱ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ጠቅላላ ምርጫ፣ የዕጩዎች ምዝገባ የካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ተጀምሮ፣ የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም.  በይፋ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ከዚህ አንፃር ኢዜማ በዕጩዎች ምዝገባ ሒደት ወቅት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ እንዲሁም ከመንግሥት አካላት ደረሰብኝ ያለውን ሳንካ በዝርዝር አቅርቧል፡፡

በዚህም መሠረት የምርጫ ቦርድ የወረዳ ቢሮዎችን በጊዜ ሰሌዳው መሠረት አለመክፈቱ፣ ከሕግ፣ ከደንብና ከመመርያ ውጪ እንዲሟሉ የሚቀርቡ ጥያቄዎች በየምርጫ ክልል ቢሮዎች በተመደቡ የምርጫ አስፈጻሚዎች ወይም ዕጩ መዝጋቢዎች አቅምና ብቃት ውስንነት፣ እንዲሁም በተወሰኑ አካባቢዎች የምርጫ ክልል ቢሮዎች በዕጩነት የሚመዘገቡ አካል ጉዳተኞችን ከግምት ያስገባ አለመሆኑ፣ በቦርዱ የታዩ ክፍተቶች ናቸው በማለት ኢዜማ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ፓርቲው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባሉ የምርጫ ወረዳዎች ያቀረባቸው ዕጩዎች ከመመዝገባቸው በፊት ዛቻና ማስፈራራት፣ በፀጥታ ሁኔታው ዕጩ ለማስመዝገብ የማይቻልባቸው ቦታዎች መኖር፣ በተለያዩ አካባቢዎች የኢዜማ ዕጩዎች ከተመዘገቡ በኋላ ያለመከሰስ ሙሉ መብት እንዳላቸው እየታወቀ፣ ዕጩዎችን ማሰር፣ መደብደብና የመሳሰሉት ደግሞ ከመንግሥት ጋር በተያያዘ የገጠሙት ችግሮች መሆናቸውን ፓርቲው በዝርዝር አቅርቧል፡፡

በዚህም ምክንያት ፓርቲው፣ ‹‹በኦሮሚያ ክልል ቢያንስ በ46 የምርጫ ወረዳዎች ዕጩዎቻችንን ማስመዝገብ አልቻልንም፤›› በማለት ፓርቲው ቅሬታውን አቅርቧል፡፡ ‹‹ምርጫን ዴሞክራሲያዊ በማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ሒደቱ ትልቅ ሚና አለው፡፡ ሒደቱን ካበላሸነው ውጤቱን ይወስነዋል፡፡ አሁን እንደምናየው ብልፅግና ኦሮሚያ ላይ ብቻውን ለመወዳደር እየሄደበት ያለው መንገድ አገርንም ጭምር ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል፤›› ሲሉ፣ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ አስጠንቅቀዋል፡፡

ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ አስመልክቶ መንግሥት የዜጎችን ፀጥታና ደኅንነት እንዲያስጠብቅና እንዲያስከብር ፓርቲው በአፅንኦት ጠይቋል፡፡ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በቡራዩ፣ በሻሸመኔ፣ በአርሲ፣ በጉራፈርዳ፣ በመተከልና አካባቢው፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በኮንሶና በሌሎችም ቦታዎች ዜጎች በብሔርና በማንነታቸው ምክንያት በግፍ መገደላቸውን በማስታወስ፣ ‹‹ለእነዚህ ግድያዎችና የዘር ማፅዳት ወንጀሎች ሕወሓት ዋነኛ ተጠያቂ እንደሆነ ሲነገር ቢቆይም፣ ከሕወሓት መወገድ በኋላም አልተቋረጡም፡፡ ይህ ክፍተት በመንግሥት ደረጃ ያለውን አቅም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፤›› በማለት፣ መንግሥት ከዚህ አኳያ የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...