Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ሊያረጋጋ የሚችል ባዛርና ሲምፖዚየም ሊካሄድ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኘውን የዋጋ ግሽበት በመጠኑም ቢሆን ሊያረጋጋ ይችላል የተባለ ባዛርና ሲምፖዚየም ሊካሄድ ነው፡፡

ባዛርና ሲምፖዚየሙ የሚካሄደው በአገር አቀፍ ደረጃ ሲሆን፣ 66 የሚሆኑ አገር በቀል የኅብረት ሥራ ማኅበሮች እንደሚሳተፉበትና ከ500 በላይ የግብርናና የኢንዱስትሪ አምራቾች ምርቶቻቸውን እንደሚያቀርቡ፣ የፌዴራል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

ኤጀንሲው ዓርብ መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ያላቸውን ልምድ በመጠቀም፣ በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ላይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጡ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር እንዳብራሩት፣ ሲምፖዚየሙ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ለስምንተኛ ጊዜ ነው፡፡ ሲምፖዚየሙ አምራቾችን ከሸማቾች ጋር በቀጥታ በማገናኘት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያለመና በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ሊያረጋጋ እንደሚችል ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡

አገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ኤግዚቢሽን ባዛርና ሲምፖዚየሙ የሚካሄደው ‹‹የኅብረት ሥራ ግብይት ለዘላቂ ሰላም›› በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 9 እስከ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ሲሆን፣ የመክፈቻው ሥነ ሥርዓት በሸራተን አዲስ ይካሄዳል፡፡ በሲምፖዚየሙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚመለከቱ አዳዲስ አሠራሮች እንደሚቀርቡም ተጠቁሟል፡፡

ማኅበራቱ ከአራት እስከ አምስት ሺሕ ኩንታል የምግብ እህሎችንና ሌሎች የግብርና ምርቶችንም በማቅረብ፣ የቀጥታ ሽያጭ እንደሚያካሂዱ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስሩ እንዲፈጠር ከ30 ሺሕ ኩንታል በላይ የሚሆኑ የምግብ እህሎችን ለማቅረብ በአምራቾቹና ሸማቾች ጋር ስምምነት እንደሚፈረምም አክለዋል፡፡ ሲምፖዚየሙ በኦሮሚያ ባህል ማዕከልም እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳት ተዋጽኦ፣ በደን ውጤቶች፣ በኢንዱስትሪ ዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ በማዳበሪያና በሌሎች አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ተግባራት ላይ ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአገሪቱም 1,154 የሚሆኑ የኅብረት ሥራ ማኅበራት 1,649 የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም፣ ለኢንዱስትሪ ዕድገትና ለዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች