የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ አዲስ ደረቅ ወደብ ሊገነባ እንደሆነ አስታወቀ፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከዚህ በፊት ኮምቦልቻ ድርጅቱ የሚገለገልበት ደረቅ ወደብ ነበር፡፡ ሆኖም ደረቅ ወደቡ በቤቶች የተከበበና የተሟላ መሠረተ ልማት እንደሌለው ገልጸው፣ ለኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ለአውሮፕላን ማረፊያው፣ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልዲያ ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ማዕከል ያደረገ፣ የደረቅ ወደብ ግንባታ ቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡
በኮምቦልቻ የሚገነባው ደረቅ ወደብ 10,000 ኮንቴይነሮችን እንደሚይዝ፣ ከተማዋ የኢንዱስትሪ ማዕከልነቷ ዕያደገ በመሆኑና ወደፊትም የሎጂስቲክስ መዳረሻነቷን ከግምት ውስጥ በማስገባት የታቀደ ፕሮጀክት እንደሆነ አቶ ሮባ ገልጸዋል፡፡
የደረቅ ወደብ ግንባታውን ሥራ ለማስጀመር ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ያስታወቁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ለግንባታ የሚውለውን መሬት ዝግጁ ለማድረግ በከተማ አስተዳደሩ በኩል ችግሮች ባይኖሩም፣ በአመራር መለዋወጥ ምክንያት የጥያቄው መዘግየት ተስተውሏል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ሮባ ገለጻ የደረቅ ወደቡን ለመገንባት የሚያስፈልገው 25 ሔክታር መሬት በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በኩል ለማቅረብ፣ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህም የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጀት ከሌሎች አገልግሎት አቅራቢ ተቋማት ጋር በመሆን ለደንበኞች የቀረበ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ይሆናል ብለዋል፡፡
ድርጅቱ በዚህ ወቅት የግንባታ መሬቱን ለመረከብ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ ሮባ፣ በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በኩል ከካሳና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮች እንደተጠናቀቁ ወደ ግንባታ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የአዋጭነት ጥናትና የፕሮጀክት ዲዛይን ሥራው እንደተጠናቀቀ ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የካሳ ግምት ክፍያው በውል ባለመታወቁ ምክንያት ለግንባታው የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን በትክክል ባይታወቅም፣ ድርጅቱ ከዚህ በፊት ካለው ልምድ በመነሳት የባቡር መስመር አገናኝ ሥራዎችን ጨምሮ ለደረቅ ወደቡ ግንባታ፣ ከአንድ እስከ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስወጣው አስረድተዋል፡፡
በሞጆና በድሬዳዋ ደረቅ ወደቦች ግንባታ ላይ የባቡር አገናኝ መስመር የሠራው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ በዚህም ፕሮጀክት ከባቡር ጋር አገናኝ የሆነውን መስመር ሥራ ድርጅቱን በመወከል እንደሚቆጣጠር የታወቀ ሲሆን፣ አጠቃላይ የደረቅ ወደብ ግንባታ ሥራው በቀጣይ በሚወጣ ጨረታ ሥራ ተቋራጭ የመቅጠር ሒደት የሚከናወን እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ከግዥ ሥርዓት ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች እንቅፋት ካልሆኑ በስተቀር፣ ድርጅቱ የደረቅ ወደቡን ግንባታ በሁለት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ማቀዱን ያስታወቁት አቶ ሮባ፣ ከዚህ በፊት ሲያገለግል የነበረውን የደረቅ ወደብ ለከተማው አስተዳደር በማስረከብ ወደ አዲሱ ደረቅ ወደብ የመሸጋገር እንቅስቃሴ በግንባታው ሒደት ወቅት እንደሚከናወን ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ግንባታውን ለማስጀመር ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳለው፣ በኅብረተሰቡም በኩል የደረቅ ወደብ ግንባታውን መጀመር በትልቅ ጉጉት እንደሚጠብቀው ያስታወቁት አቶ ሮባ፣ ከተሞችን ከመቀየር አንፃር ግንባታው ያለው አስተዋጽኦ በቀላሉ ሊታይ እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡ የወረታ ደረቅ ወደብን ምሳሌ አድርገው ያወሱት አቶ ሮባ፣ በከተማዋ አነስተኛ የደረቅ ወደብ በመገንባቱ የአካባቢው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደጨመረና የተፈጠረው የሥራ ዕድልም በእዚያው ልክ የሰፋ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ድርጅቱ ወደፊት ሌሎች ደረቅ ወደቦችን የማስፋት ሥራ እንደሚያከናውን፣ ከወዲሁም ወረታ ያለውን በሦስት ሔክታር ላይ ያረፈ ወደብ ወደ 20 ሔክታር የማሳደግ፣ መቀሌ ባለው ወደብ ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራዎች እንደሚኖሩ፣ ሞጆ የሚገኘውን ደረቅ ወደብ ከዓለም ባንክ በተገኘ 20 ሚሊዮን ዶላር በዘመናዊ ማሽነሪዎች የማስፋፋትና የመደራጀት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ሮባ አስታውቀዋል፡፡