Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተሰርቋል የሚለው ወሬ መሠረተ ቢስ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተሰርቋል የሚለው ወሬ መሠረተ ቢስ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

ቀን:

የ2012 የትምህርት ዘመን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተሰርቋል በሚል በተለያዩ አካላት የተላለፈው መረጃ፣ መሠረተ ቢስ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) የ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና በሰላም መጠናቀቁን በተመለከተ፣ ሐሙስ መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፣ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ‹‹ፈተናው ተሰርቋል›› ተብሎ ሲራገብ የነበረው ወሬ መሠረተ ቢስ እንደሆነና ካለፉት ዓመታት በተሻለ ዘንድሮ የተሰጠው ፈተና በተለያዩ አካላት ርብርብ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

የተወሰኑ ተማሪዎች የእጅ ስልክ አሾልከው በማስገባት ለመኮረጅ ያደረጉት ሙከራ ‹‹ፈተና ተሰርቋል›› የሚያስብል እንዳልሆነ ያስረዱት ሚኒስትሩ፣ በጥቂት ተማሪዎች የተደረገ ተራ የኩረጃ ተግባርን በመጥቀስ ‹‹ፈተናው ተሰርቋል›› ማለት ፈተናውን በአግባቡ እንዲሰጥ የማድረግ ርብርብ ዋጋ የሚያሳንስ ነው ብለዋል፡፡

የፈተናውን ዝግጅት የሚመራ ብሔራዊ ኮማንድ ፖስት እንደተቋቋመ የገለጹት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ ፈተናው እንደ ቀደመው ጊዜ አራት ስብጥር ያለው አንድ ፈተና ሳይሆን 32 ስብጥር ያለው ስምንት ፈተና እንደነበር በማስታወቅ፣ በዚህም በቅድመ ኅትመትና ኅትመት ወቅት ሊያጋጥም ከሚችል አደጋ የተጠበቀ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

በፈተናው ይሸፈናል ከተባለው የትምህርት ርዕስ ውጪ ፈተናው እንዳልተዘጋጀ ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፣ አጠቃላይ ፈተናው የወጣው ተማሪዎቹ 11ኛ ክፍል ከተማሩዋቸው ሁለት ወሰነ ትምህርቶችና ከ12ኛ ክፍል የመጀመርያው ወሰነ ትምህርት ብቻ እንደነበረ ገልጿል፡፡

በሕግ ማስከበር ሒደት የፀጥታ ችግር የነበረባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በተሳካ ሁኔታ ፈተናው እንደተሰጠና በመተከል፣ በሁመራ፣ በወልቃይትና በራያ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በመቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ በራያ ዩኒቨርሲቲ፣ በአክሱምና በሽሬ ካምፓሶች ፈተናው በአግባቡ እንደተሰጠ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

የፀጥታ ችግር ካለባቸው አካባቢዎች መጥተው አዲስ አበባ የነበሩ ተማሪዎችን እንደገና በመመዝገብ በአንድ ተጨማሪ የፈተና ጣቢያ ተማሪዎች መፈተናቸውን የገለጹት ጌታሁን (ዶ/ር)፣ በአጠቃላይ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ (መተከል ዞን) እና በአጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከክልል ፀጥታ መስተዳደሮችና ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር መምህራን ተጨማሪ ድጋፍ በማግኘት ፈተናውን ማከናወን እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡

የአጠቃላይ የትምህርት ሚኒስቴር ትልቁ ኃላፊነት ተማሪዎችን ማስፈተንና ውጤት ማሳወቅ እንደሆነ ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በቅርቡ ውጤት እንደሚገለጽና ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የማካካስ ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡

በትግራይና በመተከል አካባቢዎች ያለውን የፀጥታ ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ትምህርት ሚኒስቴር በምዘና ወቅት እነዚህ አካባቢ ያሉ ተማሪዎችን የማለፍ ውጤት ላይ ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...