Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊጉ ጎልቶ የወጣው ፋሲል ከነማ

በቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊጉ ጎልቶ የወጣው ፋሲል ከነማ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ1990 ዓ.ም. እንደ አዲስ ተዋቅሮ ውድድር ከጀመረ ወዲህ ክለቦች ወደተለያዩ የክልል ከተሞች እየተጓዙ ውድድሮቻቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት አብዛኞቹ ክለቦች ከሜዳቸው ውጪ ተንቀሳቅሰው የሚያደርጓቸው ግጥሚያዎች ከፍተኛ ፈተና ይገጥማቸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ አሁን ላይ ኮቪድ-19 እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ ከባድ ቢሆንም፣ በብዙ ፈተና ውስጥ ሲያልፍ ለነበረው የኢትዮጰያ ፕሪሚየር ሊግ ግን በብዙ መልኩ የተሻለ መሆኑ የሚናገሩ አልጠፉም፡፡

በተለይም ካለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ወዲህ እየተባባሰ በመጣውና የስፖርት መንደሩ ሳይቀር በጎበኘው የጦዘ የብሔር ፖለቲካ ምክንያት፣ አንድ ቡድን ወደ ሌላ ቡድን ከተማና ሜዳ ተጉዞ የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ ዘበት እየመሰለ መጥቶም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የቡድኖችን ወጥ አቋምና ብቃት ለመመልከትና ለመገምገም አስቸጋሪ አድርጎት መቆየቱ አስረጅ የማያስፈልገው የአደባባይ ምስጢርም ነበር፡፡

በዚህ ዓመት እየተከናወነ የሚገኘው የቤትኪንግ የፕሪሚየር ሊግ፣ እንዲህ ያሉ ዝብርቅርቆችን ብቻ ሳይሆን የቡድኖች ብቃት ምን ይመስላል የሚለውን ጭምር ለመገምገምና ለማነጻጸር ይቻል ዘንድ ችግሩን በመጠኑም ቢሆን እንደቀነሰው የሚናገሩ አሉ፡፡ የዘንድሮ ውድድር በአምስት ከተሞች ማለትም በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በባህር ዳር፣ በድሬዳዋ እና በሐዋሳ ከተሞች እንዲካሄድ በመወሰኑ የሜዳ ተጠቃሚነት ሳይሆን የቡድኖች ጥንካሬ ጎልቶ እንዲወጣ በር መክፈቱን ጭምር ይናገራሉ፡፡

ለዚህ በማሳያነት የሚጠቅሱት ሊጉን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ በ38 ነጥብ እየመራ የሚገኘው የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የሚያሳየውን ወጥ አቋም ሲሆን፣ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎች በየከተማው የሚካሄዱ ቢሆን ኖሮ፣ ፋሲል አሁን የሚገኝበት ደረጃ እያሳየ የሚገኘውን ወጥ አቋም ለማሳየት አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን የማይታሰብ ሊሆንበት እንደሚችል የሚያነሱ አሉ፡፡

ፋሲል ከነማ እስከ አሁን ካደረጋቸው ጨዋታዎች በአንድ ጨዋታ ተሸንፎ በሁለት ጨዋታ አቻ ተለያይቶ፣ ቀሪውን አሸንፎ በውጤታማነት ጉዞው ቀጥሏል፡፡ በሊጉ ታላላቅ የሚባሉትን ቡድኖች በተለይም የአዲስ አበባዎቹን ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፉ ከወዲሁ ለሊጉ አሸናፊነት ቅድመ ግምት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡

የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲጀመር በክለቡ ደጋፊዎችና አንዳንድ አመራሮች ክፉኛ ትችትና ተቃውሞ ሲገጥማቸው የነበረው የፋሲል ከተማ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ፣ አሁን ላይ ተችዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪዎቻቸውን ጭምር አፍ አዘግተዋል፡፡ አሠልጣኝ ሥዩም ቅዱስ ጊዮርጊስንና ኢትዮጵያ ቡናን ድል በነሱ ማግስት በሊጉ ደረጃ ግርጌ ላይ የሚገኘው ጅማ ከነማን በጥሩ የጨዋታ ብልጫ ሦስት ነጥባቸውን ካሳኩ በኋላ ለሱፐር ስፖርት በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ የባህር ዳር ቆይታቸውን አስመልክቶ ከአምስት ጨዋታ በአንድ ጨዋታ ነጥብ ቢጥሉም፣ አራቱን ጨዋታ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ መቻላቸው ቡድናቸው በምን ያህል የአቋም ብቃት ላይ እንዳለ የሚያሳይ ስለመሆኑ ጭምር ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

አሠልጣኙ ከባህር ዳሩ ጨዋታ በኋላ በሚኖረው የዕረፍት ጊዜ ቡድናቸው በአካልም ሆነ በመንፈስ ተዘጋጅቶ ቀሪውን የጨዋታ መርሐ ግብር በጥሩ ብቃት ለማጠናቀቅ ዕድል እንደሚኖረው ጭምር ተናግረዋል፡፡ የቡድናቸውን ጠንካራ ክፍል አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ አሠልጣኝ ሥዩም፣ ‹‹እንደ እኛ በሁሉም ዲፓርትመንት የኳስ ቁጥጥሮች እየተሻሻሉ ሄደዋል፣ እንደ ቡድን የመከላከል ብቃታቸው ጥሩ ነው፣ ወደ ተቃራኒ ሜዳ ገብተው የሚደርጉት ሙከራ እየተሻሻለ ነው፣ እንደዛም ሆኖ ጎል መሆን እየቻሉ የሚበላሹ አጋጣሚዎች ግን ተወግደዋል ማለት የማንችልበት እንዳለ አይተናል፣ መታረም እንዳለበት እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡

ጨዋታውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሱፐር ስፖርት በቀጥታ ሥርጭት እያስተላለፈ የሚገኘው ኬንያዊው ተንታኝ ጊልበርት በበኩሉ፣ ፋሲል ከነማ አሁን ላይ እያሳየ ባለው ብቃቱ የአሸናፊነት ዕድሉን እንደሚያገኝ ግምቱን አስቀምጧል፡፡ እንደ ተንታኙ ከሆነ፣ ‹‹በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ እየሠለጠነ የሚገኘው ፋሲል ከነማ እያሳየ ያለው እንቅስቃሴና ውጤቱ የሊጉ አሸናፊ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፤›› በማለት ጭምር አስተያየት ሲሰጥ ተደምጧል፡፡

‹‹አሠልጣኙ ከባህር ዳሩ ጨዋታ ቀደም ሲል በተለይም በአዲስ አበባ ስታዲየም በነበረው ጨዋታ በክለቡ ደጋፊዎችና በአንዳንድ ሰዎች ጭምር ተቃውሞ ሲገጥመው እንደነበር አስታውሳለሁ፤ አሁን ግን በአገሪቱ ከሚገኙ አሠልጣኞች መካከል ለእኔ ምርጡ ነው፡፡ ምክንያቱም የአንድ አሠልጣኝ ውጤታማነት መለኪያ ከሆኑ ነጥቦች መካከል ታላላቅ ተብለው የሚጠቀሱትን እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የመሳሰሉትን ቡድኖች አሸንፏል፤›› በማለት ለፋሲል ከነማና ለአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ያለውን አድናቆት ጭምር ኬንያዊው ተንታኝ ሲናገር ተደምጧል፡፡

ከፋሲል ከተማ ውጤታማነት ጀርባ ከሚጠቀሱ አመራሮች መካከል አሁን ላይ የፋሲል ከነማ የቡድን መሪ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ሀብታሙ ዘዋለ ይጠቀሳሉ፡፡ አቶ ሀብታሙ ከ1989 እስከ 1990 ዓ.ም. ለፋሲል ከነማ ወጣት ቡድን፣ ከ1991 እስከ 1993 ዓ.ም. ደግሞ ለዋናው ቡድን እንደተጫወቱ ይናገራሉ፡፡ ከዚያም በጎንደር ከተማ የአባ ጃሌን ወይም የቀበሌ 11 ክፍለ ከተማ ቡድንን በዋና አሠልጣኝነት ይዘው እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ መዝለቃቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ሆነው ለአንድ ዓመት ካገለገሉ በኋላ፣ ከ2002 ጀምሮ እስከ አሁን የክለቡ የቡድን መሪ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ አቶ ሀብታሙን አስመልክቶ የክለቡ ነባር ተጫዋቾች በበኩላቸው፣ ‹‹አቶ ሀብታሙ ፋሲል አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ከራሱና ከቤተሰቡ በላይ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ወሳኝ ጨዋታ በሚኖረን ሰዓት ከተጫዋቾች ሥር ተለይቶ አያውቅም፣ አብሮ ይውላል፣ አብሮ ያድራል፡፡ ከሜዳ ውጪ ቡድን እንዴትና በምን አግባብ መምራት እንዳለበት ያውቃል፣ ለአንድ ቡድን የአሸናፊነት መንፈስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚነግረን በግምት ሳይሆን በእውቀት ነው፡፡ ከሜዳ ውጪም ሆነ በሜዳ ላይ ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ጥንካሬ በቀዳሚነት የምጠራው ሰው ቢኖር አቶ ሀብታሙ ነው፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡

ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው ፋሲል ከነማ ከጀርባው እንደ 12ኛ ተጫዋች የሚነገርላቸው፣ ቡድኑ በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ጨዋታ በሚያደርግበት ክልልና ከተማ ሁሉ ተንቀሳቅሰው ድጋፋቸውን ከመስጠት የማይቦዝኑ ጠንካራ ደጋፊዎች ባለቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም እንደ ደጋፊው ሁሉ የጎንደር ከተማ ከንቲባና የክለቡ ፕሬዚዳንት አቶ ሞላ መልካሙን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች፣ ፋሲል ከነማ  ጨዋታ ሲኖረው ጨዋታውን በቦታው ተገኝተው ከመከታተል ባለፈ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑ ክለቡ እያስመዘገበ ለሚገኘው ውጤት የራሱ ድርሻ እንዳለው የሚናገሩ አሉ፡፡         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...