የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ሦስት መመርያዎችን አሻሽሎ አውጥቷል፡፡ ከእነዚህ ሦስት የተሻሻሉ መመርያዎች ውስጥ ሁለቱ ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
አንደኛው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በውጭ ምንዛሪ የሚያስቀምጡትን ገንዘብ በምን ዓይነት አግባብ መጠቀም እንደሚኖርባቸው የሚያመለክት ሲሆን፣ እስካሁን ሲሠራበት የነበረውን አሠራር በተወሰነ ደረጃ የሚቀይር ነው፡፡ አንድ ዳያስፖራ በውጭ ምንዛሪ የሚያስቀምጠውን የውጭ ምንዛሪ መጠን ቀድሞ ከነበረው አሠራር በተለየ እንዲሠራበት የሚያደርግ ነው፡፡
ቀደም ብሎ በነበረው መመርያ መሠረት በውጭ ምንዛሪ አካውንት ከፍተው ማስቀመጥ የሚችሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ከሚያስቀምጡት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን መኪናና ሌሎች ዕቃዎችን ለመግዛት እንዲጠቀሙ ያደርግ ነበር፡፡
አሁን ግን በ30 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ዕቃ ማስመጣትን ማለትም እንደ መኪናና የመሳሰሉትን ዕቃዎች እንዳያመጡ ከልክሏል፡፡ በቀደመው መመርያ ከሚያስገቡት የውጭ ምንዛሪ 70 በመቶ ደግሞ የውጭ ምንዛሪው ለ28 ቀን እንዲቀመጥላቸው ተደርጎ የውጭ ምንዛሪውን ዕቃ እንዲያመጡበትና ሊጠቀሙበትም ይችሉ ነበር፡፡
በአዲሱ መመርያ መሠረት ግን ለ28 ቀናት ይቀመጥላቸው የነበረው አሠራር ቀርቶ፣ በውጭ ምንዛሪ ማስቀመጥና መገልገል የሚችሉበት የውጭ ምንዛሪ መጠን ወደ 45 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
ሆኖም ቀሪውን 55 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ባስገቡበት ዕለት በዕለቱ የምንዛሪ ዋጋ ለባንኮች እንዲሸጡ የሚያስገድዳቸው መመርያ ነው፡፡
ለዚህ መመርያ መሻሻል ዋነኛ ምክንያት የሆነው በዳያስፖራ አካውንት የሚቀመጠውን የውጭ ምንዛሪ የአካውንቱ ባለቤት በአግባቡ እየተጠቀመበት ካለመሆኑ ጋር የተያያዘ መሆኑን ከብሔራዊ ባንክ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች በውጭ ምንዛሪ የሚያስገቡትንና ለራሳቸው አገልግሎት እንዲጠቀሙበት የተፈቀደውን አሠራር ወደ ጎን በመተው የውጭ ምንዛሪውን ለሌሎች አሳልፈው በመስጠት ያልተገባ ተግባር እየተፈጸመ መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡
አንዳንዶች ለራሳቸው ጠቀሜታ እንዲያውሉት የተፈቀደውን ውጭ ምንዛሪ ኮሚሽን እየተቀበሉበትና ለሌሎች እያስተላለፉ ስለመሆኑ በተጨባጭ ይታይ ስለነበር ይህንን ክፍተት ለመድፈን ይህ መመርያ መውጣቱን ያክላሉ፡፡
የዚህ መመርያ መውጣት ውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል አመለካከት የሚሰነዘር ቢሆንም፣ የውጭ ምንዛሪን ለራሳቸው ለሚፈልጉት አገልግሎት አለማዋላቸው የፈጠረው ችግር እየተባባሰ በመሆኑ መመርያው መስተካከሉ አግባብ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡
የዳያስፖራ አካውንትን ሌሎች እንዲጠቀሙበት በማድረግ እየተሠራ የቆየው ያልተገባ ተግባር እየሰፋ መምጣቱ ጥቁር ገበያው ከፍ እንዲል አድርጓል የሚል እምነት ያላቸው ሌላው የባንክ ባለሙያ፣ በዳያስፖራ አካውንት ውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ የተሻሻለው መመርያ ጠበቅ ማለቱ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡
በተመሳሳይ ማንኛውም የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ቢዝነስና ተቋም የሚያገኘው ውጭ ምንዛሪ አሠራር መቀየሩም በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ አገሪቱ ካለባት የውጭ ምንዛሪ አጥረት አኳያ ላኪዎችም ሆኑ ሌሎች የአገልግሎት ተቋማት የሚያገኙትን ውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚገባ በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ የወጣው መመርያ አዎንታዊ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
ሌላው ማሻሻያ የተደረገበት መመርያ፣ ከወራት በፊት አንድ ድርጅት ወይም ተቋም ከባንክ ውጪ መያዝ የሚችለው የገንዘብ መጠን 1.5 ሚሊዮን ብር ነው የሚለውን የሚለውጥ ነው፡፡
ይህ የተሻሻለው መመርያ ከባንክ ውጪ በግለሰብ ደረጃ በጥሬ ገንዘብ መያዝ ያለበት 100 ሺሕ ብር መሆን እንዳለበት የሚደነግግ ሲሆን፣ ኩባንያዎች ደግሞ መያዝ የሚችሉት እስከ 200 ሺሕ ብር ብቻ መሆኑን ተሻሽሎ የወጣው መመርያ ያመለክታል፡፡
ይህ መመርያ በእጅ በጥሬ ገንዘብ በአንድ ጊዜ የሚያዘውን 1.5 ሚሊዮን ብር ወደ 100 ሺሕ ብርና 200 ሺሕ ብር ማውረዱ በጥሬ ገንዘብ ግብይት የሚታወቀው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ችግር ይፈጥራል የሚል መሟገቻ እንዲነሳ እያደረገ ነው፡፡
አጠቃላይም ሊባል በሚችል ደረጃ የአገሪቱ ግብይት ሥርዓት በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ሳለ፣ በአንድ ጊዜ በጥሬ ገንዘብ ከ100 እና 200 ሺሕ ብር በላይ መያዝ አይቻልም መባሉ አግባብ እንዳልሆነ ብዙዎች እየገለጹ ነው፡፡ ሰዎች ገንዘብ ሸሽገው እንዲያስቀምጡ የሚጋብዝና የጥሬ ገንዘብ እጥረት የሚፈጥር ነው ያሉም አሉ፡፡
ሥርዓቱ በጥሬ ገንዘብ የሚገበያይ መሆኑ ዕለት ተዕለት የግብይት ሥራ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚለውን ሙግት የሚያነሱ ወገኖች፣ አሁን በተፈቀደው ገንዘብ መጠን ልክ ግብይት መፈጸም ስለማይቻል አንዳንድ ቢዝነሶች ላይ ችግር ይፈጥራል የሚል አንድምታ አላቸው፡፡
የገንዘብ እንቅስቃሴውን ወደ ባንክ ለማስገባት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ፣ እንዲሁም ግብይቶች በባንክ በኩል እንዲያልፉ ለማድረግ ከባንክ ውጪ የሚያዝ ገንዘብ መቀነስ እንዳለበት ቢታመንም፣ ምን ያህሉ በባንክ እየተጠቀመ ነው የሚለው መታየት ነበረበት ይላሉ፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ ከባንክ ውጪ በግለሰብም ሆነ በኩንያዎች ደረጃ 1.5 ሚሊዮን ብር ይሁን ሲባል፣ ይህንን ያህል ገንዘብ ሰው እጅ ላይ እንዲኖር መፍቀድ እንደሌለበት ባንኮች በማኅበራቸው በኩል ሲሞግቱ የቆዩ ሲሆን፣ በወቅቱ በ1.5 ሚሊዮን ብር እንዲፀና የተደረገው የብር ኖት የመቀየር እንቅስቃሴው ላይ ችግር ሊሆን ይችላል በሚል ነበር፡፡ ውጭ ያለው ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ ያግዛል በሚል እንደነበርም ይታወሳል፡፡
በእነዚህ በተሻሻሉ መመርያዎች ዙሪያ ያነጋገርናቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ደግሞ፣ በተለይ የዳያስፖራ አካውንት አጠቃቀም ላይ የታየው ሕገወጥ አሠራር መመርያውን ለማሻሻል አስገድዷል ብለው ያምናሉ፡፡
ይህንንም ሲያብራሩ ዳያስፖራ አካውንት ከተፈቀደ ጊዜ ጀምሮ አብዛኛው የዳያስፖራ አካውንት አዋጭ የተባሉ ዕቃዎች የሚመጣባቸው ሆነዋል፡፡ ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር እነርሱ እንዲጠቀሙበት የተሰጠውን ዕድል ለሌላ መጠቀሚያ አድርገዋል፡፡ እንዲያውም የእነርሱን አካውንት የሚጠቀሙ አስመጪ ነጋዴዎች ለዳያስፖራ አካውንት ባለቤቱ ኮሚሽን እየከፈሉና ዕቃ እያስመጡበት መሆኑንም እኚሁ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ አመልክተዋል፡፡
የዳያስፖራ አካውንት በመጠቀም ዕቃ እንዲመጣበት መደረጉ ደግሞ የዳያስፖራ አካውንት ላልተፈለገ ዓላማ እየዋለ መሆኑን ያሳየ ሆኖ በመገኘቱ ይህ አካሄድ ሥር ከመስደዱ በፊት ማስተካከያ መደረጉም አግባብ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
እስካሁን በዳያስፖራ አካውንት የመጡ ዕቃዎች ሲታዩና እዚህ ሊሸጡ የሚችሉ እንደ መኪናና የቤት ዕቃዎች ሆነው መገኘትታቸው የብሔራዊ ባንክ ዕርምጃ ትክክለኛነቱን ያሳያልም ይላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ እንደገና ሌላው የጥቁር ገበያ ወደ መሆን እየተቀየረ የመጣ በመሆኑ ፈር ለማስያዝ የተሻሻለ መመርያ ስለመሆኑ ያምናሉ፡፡
መመርያው አሠራሩን ከማሻሻል በላይ የዳያስፖራ አካውንትን ተጠቅሞ መኪናና መሰል ዕቃዎች እንዳይመጡ የሚያግድ ነው፡፡
በዳያስፖራ አካውንት እየተጠቀሙ የሚገቡ ዕቃዎች በተለይ መኪኖች በመሆናቸው ተሽከርካሪዎች በገበያ ላይ በብዛት እንዲኖሩ አስችሏል፡፡ ስለዚህ ወደ ጥቁር ገበያ እየተቀየረ ያለ አደገኛ አሠራር እየሆነ መጥቶ ስለነበር ይህንን ለመቀየር የዚህ መመርያ መውጣት አግባብ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
ነገር ግን ይህ የተሻሻለው መመርያ ዳያስፖራው ለኢንዱስትሪና ለመሳሰሉ ግብዓቶች የሚጠቀምበት ዕቃ ከፈለገ አካውንቱን መጠቀም የሚቻልበት ዕድል መኖሩን እኚሁ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
በአብዛኛው የዳያስፖራ አካውንትን በመጠቀም ወደ አገር የሚገባ ዕቃም አካውንት ለከፈተው ሰው አገልግሎት የማይውልና ለሌላ አካል ቢዝነስ የሚውል መሆኑ በግልጽ ታይቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከዚህ በኃላ ምን መደረግ እንደሚኖርበት ተጨማሪ ፍተሻ የሚጠይቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁን ባለው ደረጃ ግን ብሔራዊ ባንክ ያወጣው ማሻሻያ ተግባሩን ያስቀራል የሚል እምነት አላቸው፡፡
እንዲህ ያለው መመርያ በዳያስፖራ አካውንት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ሊቀንሰው ይችላል ለሚለው ሥጋት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ይህ በሒደት የሚታይ ይሆናል፣ ሆኖም በአግባቡ ከተጠቀሙበት በማሻሻያው ለግል የሚጠቀሙበት የውጭ ምንዛሪ መጠን ስለጨመረ ይኖራል የተባለው ሥጋት ላይኖር ይችላል ሆኖም ነገሩን በሒደት ማየት ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ለላኪዎችና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ተቋማት የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምን የተመለከተው ማሻሻያ ግን፣ ላኪዎችን የበለጠ የሚያበረታታ ነው፡፡ ከሚያስገኙት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን እንዲጠቀሙበት፣ ቀሪውን 70 በመቶ ደግሞ በ28 ቀን ውስጥ መጠቀም እንደሚችሉና 28 ቀኑ ሳይለወጥ የተሻለ እንዲሠሩ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡
በእጅ የሚያዝ ገንዘብን ወደ 100 ሺሕ እና 200 ሺሕ እንዲወርድ ማድረጉ ላይ ግን የማይስማሙ ስለመሆኑ እኚሁ ባለሙያ ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ያደረገው ጥቁር ገበያ እንዳይስፋፋ ታስቦ ሊሆን እንደሚችል፣ በሌላ አንፃር ደግሞ ግብይቱን በባንክ በኩል ለማካሄድ ከጥሬ ገንዘብ ይልቅ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ገንዘብ ለማንቀሳቀስ እንዲቻል ታስቦ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል፡፡
አሁን ካለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንፃር በተለይም በጥሬ ገንዘብ መገበያየት በብርቱ በመለመዱ ኢኮኖሚው ውስጥ በእጅ መያዝ ያለበት የገንዘብ መጠን መቶ ሺሕና ሁለት መቶ ሺሕ ይሁን መባሉ በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ይህ ተፅዕኖ ደግሞ በትልልቅ ቢዝነሶች ላይ ብቻ ሳይሆን ትንንሽ ቢዝነሶችንም የሚጎዳ በመሆኑ ነው፡፡
የገንዘብ እንቅስቃሴ በባንክ መሆኑ የሚደገፍ ቢሆንም፣ አንድ ነገር ለማስተካከል ብለህ የበለጠ ኢኮኖሚውን የሚጎዳ ውሳኔ መወሰን ተገቢ እንዳልሆነም ይጠቀሳል፡፡ በሳምንት ከአምስት አካውንት በላይ ማንቀሳቀስ አይቻልም እየተባለ እንደገና በእጅ የሚያዘው ገንዘብ 100 ሺሕና 200 ሺሕ ብር ብቻ ነው መባሉ የሚፈጥረው ጫና ቀላል እንደማይሆን ይገልጻሉ፡፡
ዲጂታል የክፍያ ዘዴዎችን እናስርፅ እየተባለ በእጅ የሚያዝ ገንዘብ መጠን ይነስ መባል የለበትም በማለት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ይሞግታሉ፡፡ የባንክ ባለሙያዎች ሰዎች እጃቸው ላይ ገንዘብ እንዳያሳድሩ ካልሠሩ ችግር ሊሆን ይችላልም ይላሉ፡፡
የገንዘብ እንቅስቃሴ በባንክ በኩል መሆን እንዳለበት ወደ ዲጂታል የክፍያ ዘዴ መሸጋገር እንደሚገባ የሚታመን በመሆኑ ይህንን ለማድረግ በእጅ የሚያዝ ገንዘብ መጠን መቀነስ የግድ ስለመሆኑ የባንክ ባለሙያው ያምኑበታል፡፡