Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሸማቾች መብት ቀን ሲታወስ

እ.ኤ.አ. በዓመቱ ማርች 15 የዓለም የሸማቾች ቀን በሚል ይታሰባል፡፡ ነገ መጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. መሆኑ ነው፡፡ ሸማቾችም የራሳቸው ቀን ተሰይሞላቸዋል፡፡ ነገር ግን ቀኑ በኢትዮጵያ ደረጃ እንዴት እንደሚታሰብና ቀኑን አስመልክቶ ‹‹ምን ዓይነት ፋይዳ ያለው ሥራ ይሠራል›› ለሚለው መልስ የሚሆንና በተግባር የሚገለጽ ነገር አለ ለማለት አይቻልም፡፡

ኑሮ ተወደደ፣ የገበያ ሥርዓታችን ቅጥ አጣ፣ ሸማችም ኧረ ቆረቆዝን በምንልበት ጊዜ ሸማቾችንና ሸመታን የተመለከተ አንድ የምናስበው ቀን ቢኖረን መልካም ነው፡፡ በተለይ በዚህ ጊዜ ይህ ቀን ቢታወስ ሸማቾች ድምፃቸውን ለማሰማት ጥሩ አጋጣሚ ይሆንላቸው ነበር፡፡

ለማንኛውም ሸማች ሲባል እንዲህ በዋዛ የሚታይ ነገር ያለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የሸማቾች ጥበቃ የሚገለጽባቸው በርካታ እውነታዎችም አሉ፡፡ የሸማቾችን ቀን አስመልክቶ አንድ ወዳጄ በተለይ በዚህ ወቅት የሸማች ድምፅ ጎልቶ መሰማት ብሎም መደመጥ ያለበት መሆኑንና የሸማቾች መብት ምን ድረስ እንደሆነ በማጣቀስ የላከልኝ መረጃ እንደሚከተለው ነው፡፡

የሸማቾችን መብት አስመልክተው በይፋ የተናገሩት የቀድሞው ነፍሰ ሄር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ እንደነበሩ የሚታወስ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ  እ.ኤ.አ. ማርች  15  ቀን   1962   ለኮንግረስ  ባሳሙት  ንግግር፣   ‹‹ሸማች ማለት ሁላችንም ነን›› ብለዋል፡፡ የኢኮኖሚያችንን አብላጫውን የያዘው ሸማች በግሉም ሆነ በመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ   ምክንያት ተጠቃሚም ተጎጂም መሆኑን በማስታወስ የሸማቹ ድምፅ በሚገባ ያለመሰማቱን ፕሬዚዳንቱ አመልክተው ነበር፡፡

በወቅቱ ፕሬዚዳንቱ የሸማቾችን መብቶች በአራት ዋና ዋና ክፍሎች አስቀምጠዋቸዋል፡፡ እነዚህ ያቀረቡዋቸው አራት መብቶች ግን ኋላ ላይ ወደ ስምንት ዓለም አቀፍ መብቶች ደርሰው በተለይ የሠለጠነው ዓለም እየተጠቀመባቸው ነው፡፡ እነዚህን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ኢትዮጵያም ተቀብላቸዋለች፡፡

የሸማቾች መብት ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ   መሠረታዊ ፍላጎት መብት ማንኛውም ሰው ለምግብለመጠለያ፣ ለልብስ፣ ለጤናና ለትምህርት አቅርቦት ምቹ ሁኔታ ይፈጠርለታል ይላል፡፡  ከአደጋ የመጠበቅ መብት እንዳለው ማመላከቱም በዋናነት ይጠቀሳል፡፡

ሸማቹ ማንኛውንም አደጋ ከሚያደርሱበት  ምርቶችና አገልግሎቶች የመጠበቅ መብት ያለው መሆኑም በዓለም አቀፍ ድንጋጌው ሠፍሯል፡፡ መረጃ የማግኘት/የማወቅ መብት ማለትም ስለሚጠቀምባቸው ዕቃዎችና ስለሚያገኛቸው አገልግሎቶች አጠቃቀም ትክለለኛ መረጃ የማግኘት መብት አለው፡፡ ይኼው መረጃ የታመነና እንዲሁም ፈፅሞ የማያሳስት መሆን አለበት፡፡

በዓለም አቀፍ ድንጋጌ ሌላው የሸማቾች መብት ተብሎ የተደነገገው የመምረጥ መብት ነው፡፡ የተለያዩ ምርቶችንና አገልግሎቶችን የመምረጥና ዋጋ የማወዳደር እንዲሁም በቂና አስተማማኝ ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት የማግኘት መብት አለው፡፡

የመደመጥ መብት ማለትም መንግሥት በሚቀርፃቸው ፖሊሲዎች የሸማቹ ደምፅ እንዲሰማ፣ ምርቶችና አገልግሎቶች ወደ ገበያ ከመግባታቸው በፊት የሸማቹ ፍላጎት ንዲታወቅና እንዲከበርለት የማድረግ መብትም አለው፡፡

 ሸማቹ ካሳ የማግኘት መብትም አለው፡፡ ምንም እንኳን ካሳ ለደረሰ ጉዳት የሚከፈል ቢሆንም፣ ሰፋ ባለው ትርጓሜ ሸማቹ ለሸመተው ወይም ላገኘው አገልግሎት ቅሬታ ካቀረበ የከፈለውን ገንዘብ የመመለስ፣ በዚህም ምክንያት የደረሰ ጉዳት ካለ የመካስ እንዲሁም ሸማቹ በፍላጎቱ  የመለወጥ ወይም የመቀየር መብት አለው፡፡

የመማር ስለሚሸምተው መረጃ የማግኘት መብትም ሸማቹ ተሰጥቷል፡፡ ስለሚገዛው  ዕቃ ወይም አገልግሎት፣ ስለሚያገኘው ጥቅም ወይም በአጠቃቀም ምክንያት ሊደረስ የሚችል ጉዳት ካለ  በግልጽ ሊያውቅ ይገባል፡፡

ጤናማ አካባቢ የመኖር መብቱም የተጠበቀ ሊሆን ይገባል፡፡ ሸማቹ ለጤናው ተስማሚ በሆነና ለሕይወቱ አደጋ በማይደርስበት  አካባቢ የመኖር  መብት አለው፡፡ ሸማቹ ከላይ የተዘረዘሩት መብቶች ሲኖሩት፣ የሚከተሉት ግዴታዎችም ተጥለውበታል፡፡

ኢትዮጵያም ተቀብላዋለች የተባለው ሸማችን የተመለከተው ዓለም አቀፍ ድንጋጌ፣ ሸማቹ ስለሚገዛው ዕቃና አገልግሎት በቂ መረጃ ለማግኘት መጣርና በኃላፊነት  አወዳድሮ የመግዛት መብቱን መጠቀም የሚል ነው፡፡ ለፍቶ ያገኘውን ገንዘብ ጥቅም በማይሰጡት ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ እንዳያውል፣ የመጠየቅና የመረዳት ጊዜ ወስዶ የመወሰን አቅሙን የማሳደግና ተግባራዊማድረግ ግዴታ አለበት፡፡  

የሸማቹን ፍላጎት አክብሮ፣ ጠንካራ ኅብረት ፈጥሮና  ለመብቶች መከበርና ሌሎች እንዲረዱትም የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡  

ስለ አካባቢው ማወቅ ማለትም ሸማቹ የሸመተውን በሚጠቀምበት ጊዜ አካባቢው ላይ የሚያስከትለውን  ጉዳት የመረዳትና የመከላከል ኃላፊነት አለበት፡፡   

ሸማቹ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ በፍጆታ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ምክንያት ሌሎች ሰዎች ወይም ዜጎች  ላይሚደርሰውን ተፅዕኖ የመረዳት ግዴታም የዚሁ ድንጋጌ አካል ነው፡፡

ንቁ የመሆን ግዴታ ደግሞ፣ ሸማቹ ከፍ ባለ ኃላፊነትና  ስለሚገዛውቃና አገልግሎት ጥራት በንቃት መጠየቅና ማረገጋገጥ  አለበት የሚል መሆኑን አሳይቷል፡፡ ሸማችና ከሸማች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በዚህን ያህል ደረጃ ይገለጻሉ፡፡

እነዚህንና መሰል የሸማቾች መብቶችን ለመጠበቅ የወጡትን ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ የተቀበለች ሲሆን፣ በተግባር ግን አይታይም፡፡ የሸማቾችን መብት ለማስጠበቅም አልተቻለም፡፡ በመንግሥትም ረገድ የሸማቾችን መብት ለማስጠበቅ ጠንካራ ዕርምጃ አልተወሰደም፡፡ ይህ ደግሞ ሥርዓት ያጣ ገበያ እንዲሰፍን ካደረጉ ምክንያት መካከል ነው፡፡

የተሻለ ግብይት ይፈጥራል፣ የንግዱን ሥርዓት ለማስተካከል ይረዳል ተብሎ መንግሥት የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሚባል መሥሪያ ቤት አቋቁሟል፡፡

በአዋጅ የተቋቋመው ይህ ተቋም ግን በትክክል የተቋቋመለትን ዓላማ እያሳካ ስለመሆኑ መፈተሽ ይገባል፡፡

ልብ በሉ የግብይት ሥርዓቱ ቅጥ ባጣበት፣ ሕገወጥ ንግድ ሥር በሰደደበትና ሸማች ምክንያታዊ ባልሆነ ጭማሪ በሚንገላታበትና ‹‹ኧረ የመፍትሔ ያለህ!›› በሚልበት በዚህ ወቅት ብቅ ብሎ ቢያንስ አለሁ አለማለቱ አስገራሚ ነው፡፡

የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ትልቅ ሕንፃ ይዞ የመንግሥት በጀት ተመድቦለት የሚሠራ ነው፡፡ ሸማች በተማረሩበት በዚህ ወቅት ግን ድምፁን አጥፍቶ ተቀምጧል፡፡ በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን እየተጠቀመበት ስለመሆኑም ማወቅ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ተቋሙ በሕገወጥ ንግድ፣ የገበያ ሥርዓቱን በሚያዛቡና ያልተገባ የንግድ ውድድር የፈጸሙ ተቋማትንና ግለሰቦችን ለሕግ ለማቅረብ ይችላል፡፡ የራሱ የሆነ ችሎትም አለው፡፡ ሆኖም የተሰጠውን ኃላፊነት ትርጉም ባለው ሁኔታ ተወጥቷል ማለት አይቻልም፡፡ እየተወጣ ነው ብሎ መናገርም ይከብዳል፡፡

ሌላው በከተማ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የተሸሸጉ ዘይቶች ሲገኙ እንኳን ይህንን አገር ያወቀውን ጉዳይ አጣርቶ ስለጉዳዩ አልነገረንም፡፡ አዎ ሰምቻለሁ እንኳን አላለም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ካለው የንግድ ማጭበርበር አንፃር 24 ሰዓት መሥራት ያለበት ቢሆንም ይህን አላሳየንም፡፡ የተሻለ ተቋም ያስፈልገናል፡፡

ነገ በሚታሰበው የሸማች ቀን ግን በተለያዩ ዘርፎች የሸማቹን መብት የሚያስጠብቁ ጠንካራ ማኅበራት እንዲኖሩ መሞገት ቁልፍ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ሸማች መብቱ የት ድረስ እንደሆነም ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ የሸማች እሮሮ እየበዛ ይሄዳል፡፡ አሻጥረኞችም በግልጽ ተግባራቸው ይቀጥላልና እውነተኛ የሸማቾችን መብት የሚያስጠብቁ ማኅበራት ይጠናከሩ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት