የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ ችሎት ይጠቀምበት የነበረውን የቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል መኖሪያ ቤትን ለጣይቱ ባህልና ትምህርት ማዕከል አስረከበ።
ጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል፣ በአንጋፋዋ ከያኒት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ከሁለት አሠርታት በፊት በአሜሪካ ተቋቁሞ በኪነ ጥበብ ላይ ሲሠራ የነበረ ነው፡፡
በቅርስነት የተመዘገበው ነባር ሕንፃ ለጣይቱ ባህልና ትምህርት ማዕከል ያስረከቡት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ የትናንቱ ትውልድ ያስቀመጣቸውን መልካም አሻራዎች እንዳይደበዝዙ፣ ከነጥንታዊነታቸው፣ ከነታሪካቸውና ከነፋይዳቸው ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ ይገባል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መካነ ቅርሱን ለማደሻ የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን የከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያሠራጨው መረጃ ያመለክታል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን፣ ሚኒስትሮችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
የቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል መኖሪያ ቤት ከ117 ዓመታት በፊት መገንባቱ ይታወቃል፡፡