Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ 285 ብሔራዊ የጥራት ደረጃዎች መፅደቃቸውን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ከብሔራዊ የደረጃ ዝግጅት ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በመሆን፣ የ285 ብሔራዊ የጥራት ደረጃዎችን በብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት ማፅደቁን አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው ማክሰኞ መጋቢት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ለብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት ያቀረባቸው 285 የጥራት ደረጃዎች ፀድቀዋል፡፡

በስድስት ዘርፎች ተዘጋጅተው ከቀረቡት 285 ደረጃዎች 148 ያህሉ አዲስ ሲሆኑ፣ 44 የሚሆኑት የተከለሱና የተቀሩት 93 ደረጃዎች በፊት የነበሩና እንዲቀጥሉ የተወሰኑ እንደሆኑ ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡ እነዚህም በግብርናና በምግብ ዝግጅት 18፣ በመሠረታዊና አጠቃላይ የደረጃ ዝግጅት 28፣ በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች 72፣ በኮንስትራክሽንና ሲቪል ኢንጂነሪንግ 79፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል 69፣ እንዲሁም በአካባቢና ጤና ደኅንነት 19 ደረጃዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን እንዳስታወቁት፣ ወቅታዊውን ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በማድረግ የጤና መስጫ ተቋማትን የተመለከቱ 13 ደረጃዎች ወጥተዋል፡፡ በወረርሽኝ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ ከመኖሩ ጋር በተያያዘ የፋይናንስ እንቅስቃሴው ወደ ዲጂታል እየተቀየረ መምጣቱን ተከትሎ፣ የፋይናንስ ተቋማት ተግባራዊ የሚያደርጓቸው 28 የፋይናንስ ዘርፉን የተመለከቱ ብሔራዊ ደረጃዎች መውጣታቸውን አክለዋል፡፡

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንፃርም የግብርና መሣሪያዎችን የተመለከቱ 51 ደረጃዎች እንደተዘጋጁ ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህም የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን፣ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ረገድ፣ እንዲሁም የግብርና ምርትን ወደ ውጭ በመላክ እንቅስቃሴ ላይ የደረጃዎቹ መውጣት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተገናኘ የተዘጋጀ አዲስ ደረጃ እንደወጣ ያስታወቀው ኤጀንሲው ከቆሻሻ መለየት፣ ማስወገድና መልሶ ከመጠቀም ጋር የተገናኙ ስድስት ደረጃዎች እንደሆኑ፣ እነዚህን ደረጃዎች ተግባራዊ በማድረግ በኩል ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበት ተገልጾ፣ ይህንንም በኅብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ በቀለም የሚገለጽ ደረጃ (ከለር ኮዲንግ) እንደተዘጋጀ ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

የፀደቁት ደረጃዎች ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው፣ የምርቶችን፣ የአገልግሎቶችንና ተያያዥ ጉዳዮችን ጥራት ከማሻሻልና ከማረጋገጥ አንፃር ለኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪውና ለንግድ የተወዳዳሪነት አቅም ለማጎልበት እንደሚረዱ የገለጹት አቶ እንዳለው፣ ከኅብረተሰቡ ጤናና ደኅንነት፣ ከአካባቢ ጥበቃና የሸማቾችን ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ጠቁመዋል፡፡

በጠቅላላው ለብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት የቀረቡት ደረጃዎች 289 እንደነበሩ ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ 285 የሚሆኑት ሲፀድቁ አራቱ ደረጃዎች እንዲዘገዩ የተደረገው ባለድርሻ አካላትን በበቂ ሁኔታ ያሳተፈ ውይይት እንዲደረግባቸው ትዕዛዝ የተሰጠባቸው ከወረቀት፣ ከፐልፕና ከተዛማጅ ምርቶች ጋር የተገናኙት ደረጃዎች እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

ደረጃን ተግባራዊ ለማድረግ ኤጀንሲው በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ በሚያስብል ሁኔታ ከ400 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የደረጃዎች አካዳሚን ገንብቶ ጨርሷል፡፡ ሁሉም ማምረቻና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደረጃን ከማስፈጸም ባለፈ በማስተዋወቅ ተግባር ላይ ትልቅ ድርሻ እንዲወጡ አካዳሚው አስተዋፅኦ እንሚያደርግ በመግለጽ፣ አካዳሚው ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተከፍቶ ለሥራ ዝግጁ እንደሚሆን አቶ እንዳለው ጨምረው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች