Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተመድ ለትግራይ ክልል ተጨማሪ 400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያስፈልጋል አለ

ተመድ ለትግራይ ክልል ተጨማሪ 400 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያስፈልጋል አለ

ቀን:

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታዎች ማስተባበሪያ ድርጅት (ኦቻ) በትግራይ ክልል የሚከናወኑ የሰብዓዊ ድጋፍ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ፣ ተጨማሪ የ400 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ እንደሚያስፈልግ አስታወቀ፡፡

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ከመንግሥት ፈቃድ ጠይቀው ማግኘት ይኖርባቸው የነበረው አሠራር ተለውጦ፣ በኢሜል መልዕክት በማሳወቅ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን ለማሰማራት እንዲችሉ መደረጉ መልካም ጅምር መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ፣ ለሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነትና ወሳኝ ድጋፎችን ለማቅረብ ጠቃሚ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በዚህም መሠረት በርካታ ድርጅቶች የሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ መቻላቸውን በመጥቀስ ድጋፉን ማቀላጠፍ መቻሉን፣ በጠቅላላው 240 የተመድ ሠራተኞችና ከ1,000 በላይ የተመድ ሠራተኞች ያልሆኑ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢዎች በትግራይ ተሰማርተዋል ሲል አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ ሰኞ መጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች አማካይነት ለ900 ሺሕ ሰዎች አስፈላጊ የምግብ ድጋፍ መደረጉን፣ ለ700 ሰዎች ደግሞ የውኃ አቅርቦት እንደተደረገ፣ እንዲሁም ለ136,000 ሰዎች ደግሞ መጠለያ ማቅረብ እንደተቻለ ገልጿል፡፡

በየካቲት ወር የሪሊፍ ዌብ ድረ ገጽ ባስነበበው ጽሑፍ በትግራይ ክልል በተለይ የስልክ መስመሮች ክፍት ከተደረጉ በኋላ የሰብዓዊ አቅርቦት እየተሻሻለ መጥቷል ብሏል፡፡ በጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ከባድ ጉዳት በክልሉ የጤና አገልግሎት አቅርቦትና ተደራሽነት ላይ ከባድ እንቅፋት አሳድሯል ሲልም አክሏል፡፡

በትግራይ ክልል በዚያው ወር 84 የረድኤት ድርጅቶች እንደተሰማሩ የሚያትተው መግለጫው፣ በመከላከያ ሠራዊትና በትግራይ ልዩ ኃይል፣ እንዲሁም ከእነዚህ ኃይሎች ጋር የተሳሠሩ ሚሊሻዎች ውጊያ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የከባድ መሣሪያ ተኩሶች፣ አድፍጦ ማጥቃትና አጥቅቶ መሸሽ ይታያሉ ብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ልዩ ኃይሎች በክልሉ መኖራቸው፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መረጋገጡን ጠቁሟል፡፡

እነዚህ ግጭቶች በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽ ለማድረግ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ አስረድቷል፡፡ ስለዚህም የሰብዓዊ ዕርዳታ እንቅስቃሴዎች በአላማጣ፣ በመቐለ፣ በአዲግራት፣ በሽረና በኩታ ገጠም ወረዳዎች ዋና ዋና መንገዶች ላይ የታጠረ ነው ብሏል፡፡ በፀጥታ ችግር ምክንያትም የሰብዓዊ ዕርዳታ ማቅረብ ያልተቻለባቸው አካባቢዎች ማዕከላዊ ትግራይ ዞን፣ ደቡብ ምሥራቃዊና ደቡባዊ የክልሉ አካባቢዎች መሆናቸውንም ጠቅሷል፡፡

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንደደረሰ በመግለጽ፣ ጥቃቱን አድርሰዋል በተባሉት የትግራይ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ላይ የመከላከልና የማጥቃት ዕርምጃ ያወጁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፎችን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ከመንግሥታቸው ጋር ተሠልፎ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየካቲት ወር መጀመርያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹በትግራይ ክልል ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን በተወሰደው ዕርምጃ ስኬት ያስመዘገብን ቢሆንም፣ ምንም እንኳን ከፍተኛ ጥረትና ጥንቃቄ ብናደርግም፣ የደረሱት ጉዳቶችና ሞቶች በግለሰብ ደረጃ እኔን የሚያስጨንቁኝ ሲሆን፣ በተጨማሪም እዚህም ሆነ በውጭ የሚገኙ ሰላም ወዳድ ሰዎችን አሳስቧል፤›› ብለው ነበር፡፡

ስለዚህም በትግራይ ክልልና በተቀረው የአገሪቱ ክፍል የሚታዩ ሥቃዮችን ማብቃት ቀዳሚው ትኩረታቸው እንደሆነ በመግለጽ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትግራይ የሰብዓዊ መብቶች አቅርቦትን በስኬት ለማከናወን አብሯቸው እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይኼንንም ጥሪ ተከትሎ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ስምምነት የተፈጸመ ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ መንግሥት በቂ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲደርስ ነፃነት አልሰጠም ሲባል ይተች ነበር፡፡ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢዎችም መንግሥት በሚፈልጋቸው አካባቢዎች ብቻ በአጀብ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ እንደሌለበት፣ እነሱ መንግሥት ሊደርስባቸው ያልቻላቸውን አካባቢዎች ሁሉ ማዳረስ ይችሉ ዘንድ መንገዱ ሁሉ ክፍት እንዲደረግ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡

ምንም እንኳን በትግራይ ሰብዓዊ ድጋፎች እየደረሱ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ የተለያዩ የረድኤት ድርጅቶች በትግራይ ክልል ድጋፍ ማድረስ አዳጋች እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡

መንግሥት በበኩሉ ሁሉም የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢዎች ዓላማቸው ዕርዳታ ማዳረስ ብቻ እንዳልሆነና ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር በዚያ ሥፍራ በመገኘት ገንዘብ ማግኛ ያደርጉታል ብሎ እንደሚያምን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) በሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...