Friday, March 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለአገር የሚበጀው መፍትሔ እንጂ ሴራ አይደለም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ተቆጥረው የማያልቁ ችግሮች እንዳሉ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ያሉትም አልበቃ ያሉ ይመስል በላያቸው ላይ መከመርም የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን ከችግሮቹ በላይ እያስቸገረ ያለው ዋናው ጉዳይ ለመፍትሔ ፍለጋ ከመተባበር ይልቅ፣ ማዶ ለማዶ ሆኖ ጣት የመቀሳሰርና የመወነጃጀል ሴራ መበርከቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠያቂና ሞጋች ትውልድ በመፍጠር ለዘርፈ ብዙ ጉዳዮች የጋራ መፍትሔ መፈለግ ሲገባ፣ ችግር ፈጣሪዎች ሳይቀሩ በሴራ ተጀቡነው የመፍትሔ ያለህ እያሉ ያስቸግራሉ፡፡ የአገር ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት የሚከበረውና ሕዝቡም ከዘመናት ችግሮች ደረጃ በደረጃ ሊላቀቅ የሚችለው፣ ለዘመናት የተከመሩ ችግሮችን መነሻቸውን በቅጡ በመረዳትና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መግባባት በመፍጠር ነው፡፡ አንዱ ወገን ጠያቂ ሌላው ወገን መላሽ የሚሆንበት በሴራ የተተበተበ መደናቆር ተገቶ፣ በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ብሔራዊ የምክክር መድረኮችን ማደራጀት የግድ መሆን አለበት፡፡ ለአገር ልማትና ዕድገት፣ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ፣ ለዜጎች እኩልነትና ነፃነት፣ ለተቋማት በነፃነት መደራጀት፣ ለነፃና ተዓማኒነት ላለው ምርጫና ለመሳሰሉ ጠቃሚ ተግባራት የጋራ የሆነ ጥረት ሊኖር ይገባል፡፡ ችግሮችን አብጠርጥሮ ማወቅ ለመፍትሔ ግማሽ መንገድ ነው እንደሚባለው፣ ለአገር ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሔ ሳያዋጡ፣ ለሴራ ሲሆን ግንባር ቀደም መሆን ተገቢ አይደለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ነገሮችን በማወሳሰብ ችግር ለመፍጠር ግንባር ቀደም የሆኑ፣ ከሰላማዊ ግንኙነት ይልቅ ግጭት መጠንሰስ የሚቀናቸው፣ ስህተትን ለማረም ሳይሆን ስህተት ፍለጋ ላይ የተጠመዱና በአጠቃላይ አገርን ቀውስ ውስጥ ለመክተት የሚባዝኑ በዓይነትም በቁጥርም እየጨመሩ ነው፡፡ ከአቅሟ በላይ ችግሮች የተቆለሉባት ኢትዮጵያን ከድጡ ወደ ማጡ እየገፉ ያሉ ኃይሎች አንድም ቀን ተሳስተው ለሰላም፣ ለጋራ ዕድገትና ለአብሮነት ሲማስኑ አይታዩም፡፡ በየዕለቱ የፀጥታ ሥጋትና የሕዝብ መከራ ሆነው ያሳቅቃሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለአገር ሰላም፣ ለሕዝብ ደኅንነትና ህልውና በአንድነት መቆም የሚገባቸው፣ ለአገር የማይጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ጊዜያቸውን ያባክናሉ፡፡ አገር ከመቼውም ጊዜ በላይ የህልውናዋ ጉዳይ አሳሳቢ ሲሆን፣ ግድየለሽነት ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ላይ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ሐሰተኛ ዘመቻዎች በስፋት ሲከናወኑ በአንዳንድ ወገኖች የሚታዩ ሴራዎች፣ የአገሪቱ ችግሮች ምን ያህል እየተወሳሰቡ መሄዳቸውን ያመላክታሉ፡፡ በጋራ ጉዳይ ላይ መግባባት ስላቃተ ሰከን ብሎ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ በጥፋት ላይ ጥፋት መደራረብ የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በውጭም በአገር ውስጥም ኢትዮጵያ የተከፈተባትን አደገኛ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ጥቃት በፅናት ሲጋፈጡ መታየታቸው፣ በሌሎችም ችግሮች ላይ በጋራ መረባረብ ከተቻለ ትልቅ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ማስገንዘቢያ ነው፡፡ ልብ ሊባል የሚገባውም እንዲህ ዓይነቱ የጋራ ርብርብ ጠቀሜታ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ለማውጣት በፖለቲካ፣ በፍትሕና በዴሞክራሲ መስኮች የተቋማት ግንባታ ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በደካማ መንግሥታዊ መዋቅርና ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ በማይመች የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ መውረግረግ የትም አያደርስም፡፡ አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ስብስቦች በሙሉ ለሕግ መገዛት አለባቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት መፈጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በምርጫም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠራቸው የግድ መሆን አለበት፡፡ የአባላትና የደጋፊዎቻቸውን ንቃተ ህሊና ለማጎልበት ደግሞ የሲቪክ ማኅበረሰቦች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህን ነገሮች ማሟላት ሳይቻል የይስሙላ ምርጫ ማካሄድ፣ የአገርን ጉዳይ ኃላፊነት ለማይሰማቸው ኃይሎች አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር አምባገነንነት ዳግም እንዳይመለስ በጋራ ተግቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ኢትዮጵያ ሁሉንም ወገኖች በእኩልነት የሚያስተናግድ አዲስ ሥርዓት ማነፅ የሚቻለው፣ አምባገነንነት እንደ አሜባ እየተራባ ሕዝብ የመከራ ገፈት ቀማሽ መሆኑ እንዳይቀጥል ነው፡፡ በሴራ ፖለቲካ ከሕግ በላይ መሆን መቅረት አለበት፡፡

የወቅቱ አገራዊ ጉዳዮች መዘወር ያለባቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለባቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዳዮች ልሂቃንና ባለሙያዎች መሆን ሲገባቸው፣ መፍትሔ ከማመንጨት ይልቅ ችግር በመቀፍቀፍ አገር የሚያምሱ የሴራ ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ምርጫየገባችበት ያለው የሽግግር ምዕራፍ በስኬት ተጠናቆ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት መጣል ሲገባ፣ በእያንዳንዱ ዕርምጃ መሰናክል የሚያስቀምጡ ሴረኞች አላራምድ ማለት የለባቸውም፡፡ ሽግግሩ አልጋ በአልጋ ሆኖ ያለ ምንም መሰናክል እንደማይጓዝ ቢታወቅም፣ እግር በእግር እየተከታተሉ የሚያደናቅፉት ሲበዙ ግን ዝም ማለት ትክክል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጠው ወሳኝ ምዕራፍ ውስጥ ከገባች በኋላ፣ መልካም አጋጣሚዎችን የሚያበላሹ ድርጊቶችን በይሉኝታ ወይም በቸልታ ማለፍ አደጋ አለው፡፡ ይልቁንም የተሳሳቱትን በማረም፣ በመገሰፅና አለፍ ሲልም ፊት በመንሳት የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይመረጣል፡፡ አገር የምትፈልገው ከእግር እስከ ራሷ የወረሯት ችግሮች እንዲበራከቱ ሳይሆን፣ ከችግሮቿ የሚገላግላትን መፍትሔ መሆኑን መረዳት የግድ ይላል፡፡ የማደግና ታላቅ የመሆን ዕምቅ ኃይል ያላትን ኢትዮጵያ፣ የችግር ቤተ ሙከራ ማድረግ በታሪክ እንደማያስጠይቅ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ መጪው ጊዜ ያሳስባል፡፡

ለአገር የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን በጋራ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ክስተት ሲያጋጥም በመንጋ በድጋፍና በተቃውሞ ከማራገብና ግጭት ለመቀስቀስ ከመራኮት በፊት፣ የተፈጠሩ ስህተቶችን በጋራ በማረም የተሻለ ለመሥራት መንቀሳቀስ ያስከብራል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ለዓላማቸው ስኬት ሲሉ የሚፈጥሩት አዘናጊ አጀንዳ ላይ በመንጋ በመረባረብ ጊዜ ከማጥፋት፣ እንዲሁም በሌሎች ደራሽና እንግዳ  አጀንዳዎች እንደ ገና ከመጠመድ ለአገር የሚጠቅም ጉዳይ ላይ ማተኮር ተመራጭ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የሚነሳው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በተለይ ወጣቶችና ተምረናል የሚሉ ወገኖች ንፋስ እንደሚንጠው ጀልባ የሚዋልሉት፣ ሴረኞች ሆን ብለው ወቅት እየጠበቁ በሚለቋቸው በሐሰተኛ ወሬ በታጀቡ አጀንዳዎች ምክንያት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሲያጋጥሙ መቼ? የት? ለምን? እንዴት? ወዘተ ከማለት ይልቅ፣ እንደ ድንገተኛ ጎርፍ በሚለቀቁ ሐሰተኛ ወሬዎች ተሸብሮ አገር ማሸበር የተለመደ ሆኗል፡፡ ለአገር ምንም ፋይዳ የሌላቸው ነገሮች ላይ ውሎ ማደር ከመብዛቱ የተነሳ፣ ችግሮችን ከመቅረፍ ይልቅ ማባባስ ልማድ ሆኗል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አሰልቺና አስከፊ ሁኔታ ውስጥ በቶሎ መውጣት ካልተቻለ፣ የአገር ዕጣ ፈንታ ከሥጋት ሊላቀቅ አይችልም፡፡

ኢትዮጵያ በአርምሞ ውስጥ ያሉ ልጆቿ ዝምታቸውን ሰብረው ከወጡ፣ ታላቅ የማትሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ እኩል የጋራ ቤት እንድትሆን ጠንክሮ በጋራ መሥራት ከተቻለ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በየምክንያቱ ኩርፊያና ቅያሜ የበዛባቸው ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መክሮ በአንድነት መነሳት ከተቻለ፣ ከዚህ ቀደም የተሠሩ ስህተቶች ሳይደገሙ አስደማሚ ውጤት ማግኘት ይቻላል፡፡ ለተቋማት ግንባታ ልዩ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀስ ከተቻለ፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት መሠረቱ ይጣላል፡፡ ልዩነቶችን ይዞ አብሮ መሥራት፣ መወያየት፣ መከራከር፣ መደራደር፣ ወዘተ. ከተለመደ የዘመናት ችግሮች እንደ ገለባ ይቀላሉ፡፡ ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም በላይ አገርን የሚያስቀድሙ የጋራ አጀንዳዎች ወደ ውይይት መድረኮች ብቅ ሲሉ፣ ለማመን የሚያዳግቱ ጥራት ያላቸው አገር ገንቢ ሐሳቦች በስፋት ይቀርባሉ፡፡ ለሕግ የበላይነት ከፍተኛ ክብርና ሥፍራ ሲሰጥ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት አደብ ይገዛሉ፡፡ ወጣቶች ንቃተ ህሊናቸው ሲዳብርና ከታላላቆቻቸው አርዓያነት ያላቸው ተግባሮችን ሲማሩ፣ በመንጋ መነዳትና ውድመት ውስጥ መሰማራት ታሪክ ይሆናሉ፡፡ መጠየቅ፣ መሞገትና የተሻለ ሐሳብ ማመንጨት ይለመዳል፡፡ ኢትዮጵያ የምትፈልገው ይህንን ነው፡፡ ችግር የሚቆልሉ ሴረኞች ላይ ሳይሆን መፍትሔ የሚያመነጩት ላይ ትኩረት ይደረግ፡፡ የአገር ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚሹት የጋራ መፍትሔ እንጂ ሴራ አይደለም! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው ሾሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ር) አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...

የዜጎች ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ ጥበቃ ያስፈልገዋል!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢገታም፣ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የዜጎች ሰቆቃዎች በስፋት ይሰማሉ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር...