Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ሞትና ከባድ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ የጦር መኮንኖች ተከሰሱ

በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ሞትና ከባድ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ የጦር መኮንኖች ተከሰሱ

ቀን:

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት ላይ አጠቃላይ የሰሜን ዕዝ የግንኙነት መስመር (ሬዲዮ መገናኛ ድርን) በመበጣጠስ ግንኙነት እንዲቋረጥና አማራጮች ሁሉ እንዳይሠሩ በማድረግ፣ በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ ሞት፣ ከባድ አካላዊና ቁሳዊ ጉዳቶች አድርሰዋል የተባሉ 21 ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ መጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመከላከያ ሠራዊት አባል በነበሩት 21 ከፍተኛ መኮንኖች ላይ ክሱን ያቀረበው፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሽብርተኝነትና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ክሳቸውን በችሎት ተገኝተው የተከታተሉት ሰባት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ናቸው፡፡

በመከላከያ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽንና ኤሌክትሮኒክስ ሳይበር ዋና መምርያ ኃላፊ የነበሩትን ሜጀር ጄኔራል ገብረ መድኅን ፈቃዱ ኃይሌ (ወዲ ነጮን) ጨምሮ፣ በችሎት የተገኙት ኮሎኔል ገብረ ሕይወት ደስታ፣ ሌተና ኮሎኔል ዮሐንስ በቀለ፣ ሌተና ኮሎኔል ብርሃነ ሊቃኖስ፣ ሻምበል ብርሃነ ገብሩ፣ ሻለቃ ገብረ እግዚአብሔር ግርማይና ኮሎኔል ዘነበ ታመነ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ተከሳሾች አልቀረቡም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ክስ የመሠረተባቸው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ እና ለ)፣ አንቀጽ 35 እና አንቀጽ 247 (ሀ እና መ) ሥር የተደነገገውን ‹‹የአገር መከላከያ ኃይልን መጉዳት›› የሚለውን በመተላለፍ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል በማለት ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ፈጽመውታል ያለውን በክስ ዝርዝሩ እንዳብራራው፣ ተከሳሾቹ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖችና በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ላይ የተሰማሩ ነበሩ፡፡ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባላትና በፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ላይ የነበሩ አባላት፣ ከመንግሥት ሥልጣን ላይ ሲነሱ በማኩረፍ በመቀሌ ከተማ ተሸሽገዋል፡፡ ‹‹የፌዴራል መንግሥት በአደገኛ አመራሮች እጅ ስለወደቀ፣ በማንኛውም መንገድ በማስወገድ ሥልጣንን መመለስ አለብን፤›› በማለት፣ ኢሕገ መንግሥታዊ የሆነ የትግራይ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮማንድ ማቋቋማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ የተቋቋመው ‹‹የትግራይ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮማንድ›› በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ፣ የኮሚቴውን ውሳኔ እንዲፈጽምና ጥቃቱን በሚፈጽምበት ወቅት፣ መከላከያ ሠራዊቱ እርስ በርሱ እንዳይገናኝና ጥቃቱ እንዳይቀለበስ የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት የሚገናኝባቸው የሬዲዮ ግንኙቶች እንዲቋረጡ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ በዝርዝር ገልጿል፡፡

‹‹በሰሜን ዕዝ የሚገኘው የጦር መሣሪያ በሙሉ የእኛ ነው፤›› የሚል አስተሳሰብ በመያዝ፣ ከወታደራዊ ኮማንድና ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተልዕኮ በመቀበል፣ ለአገር መከላከያ ሠራዊት በታቀደው የግንኙነት መስመር ላይ የተንኮል ሥራ ለመፈጸም በማሰብ፣ ‹‹ለኢንስፔክሽን ሥራ›› በማለት፣ ወደ ሰሜን ዕዝ ሔደው የመገናኛ መኰንኖችን ሰብስበውና በየክፍለ ጦሩ እየተዟዟሩ የፕሮግራም ሙሌትና የሚሞሪ ባትሪ ቅየራ መከናወን ካለበት ጊዜ ቀደም ብለው፣ የሰሜን ዕዝን እስከ ክፍለ ጦር ያለውን በሙሉ በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲቀየር ማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

በሥራ ላይ የነበረውን የሬዲዮ ሙሌት (ፕሮግራም) ከጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲቀየርና በአዲስ ሙሌት (ፕሮግራም) እንዲሞላ በማድረግ፣ የሰሜን ዕዝ የሬዲዮ ግንኙነት ድር (ኔትወርክ) እንዲቋረጥ በማድረግ፣ የሚያስተሳስራቸውን የጋራ መስመር ፕሮግራም በመቀየር፣ አንደኛው ክፍለ ጦር ከሌላኛው ጋር እንዳይገናኝ ማድረጋቸውንም ጠቁሟል፡፡

ከትግራይ ማዕከላዊ ዕዝ ኮማንድ የሬዲዮ ግንኙነት ጋር መስመሩን በማመሳሰል፣ የመከላከያ ሚስጥር መልዕክት እንዲደርሳቸውና እንዲሰማቸው በማድረግ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ የግንኙነት ድር (ኔትወርክ) እንዲቋረጥ ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አክሏል፡፡

ተከሳሾቹ ለረዥም ርቀት የሬዲዮ ፕሮግራሚንግ ሥራ የሚያገለግለውን (ፍልገን) ኮምፒዩተር ከሁሉም ክፍለ ጦሮችና ከሰሜን ዕዝ በመውሰድ፣ እያንዳንዱ ክፍለ ጦርን በቀጥታ ወደ ማዕከል የሚያስተሳስር ሙሌት እንዳይኖር ማድረጋቸውንና የሰሜን ዕዝ ያልሆነ ሠራዊት መግባቢያ ኮድና ሰነድ በትግርኛ ቋንቋ በማዘጋጀት፣ በሁሉም ክፍለ ጦሮች ውስጥ ላሉ የሕወሓት ሰዎች በማደልና የራሳቸውን ግንኙነት በመዘርጋት፣ የዕለቱ የሬዲዮ ተረኛ ኦፕሬተርንና የጥበቃ አባላትን በማገት፣ በትግርኛ ተናጋሪዎች ቀይሮ ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆኑትን በማስገደል፣ የግንኙነት ቁሳቁሶችን ወስደው የሰሜን ዕዝ የግንኙነት ድርን (ኔትወርክ) በመበጣጠስና የሬዲዮ ግንኙነት እንዲቋረጥ በማድረግ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በክሱ በዝርዝር እንዳስቀመጠው፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት አደረጃጀትና አወቃቀር፣ የአገሪቱን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተዋጽኦን መሠረት ያደረገና ኢትዮጵያን የሚመስል፣ የአገር መከላከያ ለመገንባት የተቀመጠ ቢሆንም፣ ያንን በመጣስ የኮሙዩኒኬሽን ኤሌክትኒክስ ሳይበር ዋና መምርያ የሰው ኃይል አደረጃጀት ላይ፣ ከስትራቴጂክ እስከ ታክቲክ የሙያ ክፍል ያሉትን አመራሮች የአንድ ብሔር ተወላጆች እንዲሆኑ በማሰብ፣ ከማዕከል ዋና መምርያ ኃላፊ እስከ ሰሜን ዕዝ ክፍለ ጦሮች፣ ብርጌዶች፣ ሻለቃዎች፣ የመገናኛ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ እንዲሆኑ ማድረጋቸውንም አብራርቷል፡፡

ይህንንም በማድረግ ኢትዮጵያን የማተራመስ ሐሳብ ለማስፈጸም ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ መከላከያ ለሥራ ያሰማራቸውን የግንኙነት ቴክኖሎጂዎች ለትግራይ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮማንድ በማስታጠቅ፣ የመከላከያ የግንኙነት ማቴሪያል ግምጃ ቤቶችን ባዶ እንዲሆኑና ለክፍለ ጦሮች ድጋፍ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡

ተከሳሾቹ ‹‹ትግራይ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮማንድ›› ብለው ባደራጁት ሕገወጥ የታጠቀ ኃይል በከፈተው ጦርነት፣ በኢትዮጵያ ሕዝብና በመከላከያ ሠራዊት አባላት ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ቀውስ ማስከተላቸውንም በክሱ አብራርቷል፡፡

ሜጀር ጄኔራል ገብረ መድኅን ፈቃዱ (ወዲ ነጮ) በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽንን ኤሌክትሮኒክስ ሳይበር ዋና መምርያ ኃላፊ መሆናቸውን በክሱ የጠቀሰው ዓቃቤ ሕግ፣ ሕዝብና መንግሥት የሰጣቸውን አደራ ወደ ጎን በመተው፣ በሠራዊቱ ውስጥ የነበራቸውን የግንኙነት ሥርዓት ሆን ብለው ከላይ እስከ ታች እንዲበጣጠስ በማሰብ፣ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም. ከሌሎቹ ተከሳሾች ጋር ‹‹ለኢንስፔክሽን ሥራ›› በሚል ምክንያት ወደ ሰሜን ዕዝ ሄደው፣ የብሔር ዝርዝር ማስረጃ (ዳታ) ከሁሉም ክፍለ ጦሮች እንዲቀርብ ካደረጉና ሁሉም የሬዲዮኖች የሚሞሪ ባትሪ ፕሮግራም ሙሌት እንዲቀየር ማድረጋቸውን በክሱ ገልጿል፡፡

ለሬዲዮኖች ሚሞሪ ባትሪ ፕሮግራም (ሙሌት) ሲሞስ ባትሪ ከማዕከል ወደ ሰሜን ዕዝ በመላክ፣ የነበረውን ሙሌት (ፕሮግራም) ከጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በመቀየርና በአዲስ ሙሌት እንዲሞላ በማድረግ፣ አንድ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ብቻ ለይቶ በማሰባሰብና በማደራጀት የግንኙነት ድርን (ኔትወርክ) መበጣጠሳቸውን አብራርቷል፡፡ ከቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር እየተገናኙ ሚስጥራዊ ውይይቶችን ያደርጉ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡ አቶ ጌታቸው የሚሰጧቸውን ተልዕኮ በመቀበል ከሚመሩት ክፍል ውጪ የሆኑ ሰዎች ወደ መቀሌና አሶሳ በመላክ፣ ከመንግሥት ካዝና ወጪ እየተደረገ እንዲከፈላቸው በማድረግ የተሰጣቸውን ኃላፊነትና አስተማማኝ ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ ፈጣን፣ ከማንኛውም የሳይበር ጥቀት የተጠበቀ የዕዝ ቁጥጥር ሥርዓት እንዲዘረጋና አቅም እንዲኖር ማድረግ ሲገባቸው፣ ይኼንን ባለማድረግና የሰሜን ዕዝ ሥር ክፍለ ጦሮች እንዳይገናኙ በማድረግና የተንኮል ሥራ በመሥራት፣ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት እንዲጠቃ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡

ተከሳሾቹ በአጠቃላይ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ‹‹የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ›› ብለው ላደራጁት ሕወገጥ የታጠቀ ኃይል አሳልፈው በመስጠት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሞቱና ከባድ ቁሳዊና አካላዊ ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ተከሳሾች የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 2(2) እና 22 (3) ድንጋጌን በመተላለፍም መያዝ ከሚፈቀድላቸው ውጪ ብዛት ያላቸው የጦር ሜዳ መነጽሮች፣ ጂፒኤስና የጦር መሣሪያዎች ይዘው በመገኘታቸውም ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...