ኮሮና ቫይረስ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ተሠግቷል
በመላ ኢትዮጵያ መሰጠት የጀመረው አስትራዜኔካ የተባለው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት፣ ቀደም ሲል በወጣው የክትባት መርሐ ግብር መሠረት እየተሰጠ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ማክሰኞ መጋቢት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ክትባቱ ከደም መርጋት በሽታ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው የዓለም ጤና ድርጅት፣ የአውሮፓ ኅብረትና የእንግሊዝ የመድኃኒት ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን አረጋግጠዋል ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ትብብር ውስጥ አስትራዜኔካ ክትባትን በመጠቀም ላይ ካሉት አሥር የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ሚኒስትሯ አመልክተው፣ አንዳንድ የአውሮፓ አገሮችም ይህንኑ ክትባት ሲጠቀሙ ቆይተው በመካከሉ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ከደም መርጋት ጋር ተያያዥነት አለው በሚል ከመከተብ ተቆጥበው እንደነበር አስረድተዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ሊያ ማብራሪያ፣ ይህ ዓይነቱን መረጃ ለማጥራት በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉት ተመራማሪዎችና የሕክምና ቡድኖች ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እያካሄዱ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማቱ ክትባቱ የደም መርጋት በሽታ እንደማያስከትል፣ በዚህም የተነሳ በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በብዙ አገሮች ዘንድ በመሰጠት ላይ እንደሆነ፣ በአውሮፓ ብቻ እስካሁን ከአሥር ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ክትባቱን እንደወሰዱ፣ ስለዚህ በኢትዮጵያም የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ተጓዳኝ ችግሮች እንዳይኖሩ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ ክትባት የመስጠት ሥራ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
‹‹እስከ ታኅሳስ 2014 ዓ.ም. ድረስ ሃያ በመቶ የሚሆኑትን ማኅበረሰቦች ለመከተብ ሥራዎች የሚቀጥሉ ቢሆንም፣ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም አጠቃላይ ማኅበረሰቦችን የክትባቱ ተደራሽ ለማድረግ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ለዚህ መፍትሔው የኮቪድ-19 መከላከያ ዘዴዎችን አጠናክሮ መቀጠል ነው፤›› ብለዋል፡፡
ወረርሽኙ ከተከሰተ አንድ ዓመት ቢሆነውም ብዙ ፈተናዎች እንዳስከተለ፣ ነገር ግን መንግሥትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመንቀሳቀሳቸው ችግሩ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በከፍተኛ መጠን መቀነስና አሁን ካለበት ደረጃ ላይ መድረስ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ በተለይም ባለፉት ሳምንታት ወረርሽኙ በጣም እየተሠራጨ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ወረርሽኙ እንደተከሰተ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች አሥር በመቶ በታች እንደነበር፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ወደ 17 በመቶ ወይም በአማካይ ከአንድ መቶ ሰዎች መካከል 17 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው መረጃዎቹ መጠቆማቸውን ገልጸዋል፡፡ እስካለፈው ቅዳሜ በነበሩ አሥር ቀናት ውስጥ ከ12,000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በምርመራ መመዝገቡን፣ እንዲሁም የፅኑ ሕሙማን ቁጥር ከ450 በላይ መድረሱንና ሌሎች 149 ወገኖች ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
ከዚህም ሌላ በአገር አቀፍ ደረጃ ለኮቪድ-19 ታማሚዎች የሚውሉ ክፍሎች መሙላት፣ በዚህም የተነሳ የመተንፈሻ መሣሪያዎች መያዝና የሕክምና መገልገያ እጥረቶች ማጋጠማቸውን፣ ይህንንም ለሚመለከታቸው ሁሉ በወቅቱ እንዲያውቁት ቢደረግም የመከላከሉ ሥራ ግን የተፈለገውን ያህል ለውጥ ሊያመጣ አለመቻሉ አሳሳቢ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የሚያስጨንቅ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ አስቀድሞ እያንዳንዱ ግለሰብና ባለድርሻ አካላት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው፣ ከዚህ አኳያ በጤናው ዘርፍ የሕክምና አካላትን የማጠናከር ሥራ የሚቀጥል ሲሆን፣ በአንፃሩ ደግሞ ማኅበረሰቡ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት የጥንቃቄ ዘዴዎችን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ በተለይ በትራንስፖርት ዘርፍ ከተፈቀደው በላይ አለመጫን፣ ተጓዢዎች አፍና አፍንጫቸውን በማስክ መሸፈን የግድ እንዲጠቀሙ፣ አገልግሎት ሰጪና የመዝናኛ ተቋማት ማስክ ላላደረጉ ደንበኞቻቸው አገልግሎት ከመስጠት እንዲታቀቡ፣ ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡
በተለይም በእምነት ተቋማት ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ሲታይ በርካታ ምዕመናን የሚሰበሰቡባቸው እንደ መሆናቸው መጠን ማስክ ማድረግ የማይበረታታበት፣ እንዲያውም አንዳንዴ እንዳያደርጉ የሚከለከሉበት ሁኔታ መኖሩን መረጃዎች እንደሚያሳዩ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ሕዝቡን ከወረርሽኙ መታደግና መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት ቢሆንም፣ ይህ ኃላፊነት በተለይ በእምነት ተቋማቱ ላይ ጠንከር ብሎ መታየት እንዳለበት ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡
በትምህርት ተቋማት የተሻለ ነገር እየታየ ቢሆንም ይኸው የተሻለው ነገር መጠናከርና የመማር ማስተማሩ ሥራ ማስክ በማድረግና ማኅበራዊ ርቀትን በመጠበቅ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ፣ ከሚኒስትሯ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የእንግሊዝና የስዊድን ኩባንያ ከኦክስፎድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጋር የሠሩት አስትራዜኔካ የተባለው የኮቪድ-19 ክትባት የደም መርጋት ያስከትላል በሚል ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ ስፔንና ኔዘርላንድን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ክትባቱን ለጊዜው ከመስጠት መቆጠባቸው ይታወቃል፡፡ ካናዳን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ደግሞ አስትራዜኔካ ክትባት ውጤታማና ደኅንነት የተጠበቀ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ደግሞ በቅርቡ በኮቫክስ የተለገሳትን 2.2 ሚሊዮን አስትራዜኔካ ክትባት ከቅዳሜ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለሕክምና ባለሙያዎችና ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች መስጠት መጀመሯ ይታወሳል፡፡