Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትመዋቅራዊ ሚዛኑን የሳተው የኢትዮጵያ ስፖርትና መሪዎቹ

መዋቅራዊ ሚዛኑን የሳተው የኢትዮጵያ ስፖርትና መሪዎቹ

ቀን:

የኦሊምፒክ ቡድኑ የሕክምና ባለሙያዎች ቅሬታ አስገብተዋል

ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አመራር ቦርድ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ በትምህርት ዝግጅት ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪና ቢያንስ አንድ ዓለም አቀፍ ቋንቋ መቻል የሚለው ቅድመ ሁኔታ በአባላቱ ዘንድ ውዝግብ መፍጠሩ ተሰማ፡፡

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ አዱላላ ሪዞርት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ፣ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ይሁንታ ያገኘውንና ከላይ የተገለጸውን ቅድመ ሁኔታ ያካተተውን መተዳደርያ ደንብ ያለምንም ተቃውሞ አፅድቆ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በቅድመ ሁኔታው አማካይነት የተፈጠረው ውዝግብ ዘርፉ በምን ዓይነት ባለሙያዎች እየተመራ እንደሆነ ማሳያ ነው በማለት ብዙዎች አስተያየታቸውን እየሰጡበት ይገኛል፡፡

በአስቸኳይ ጉባዔ ወቅት ተሳትፈው ያለምንም ተቃውሞ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የምርጫ ማስፈጸሚያ መመርያውን ጨምሮ መተዳደርያ ደንቡ እንዲፀድቅ የተስማሙ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና የክልልና ከተማ አስተዳደር የስፖርት ኮሚሽነሮች፣ አመራሮችና ሌሎችም አባላት መልሰው በትምህርት ዝግጅትና ከዓለም አቀፍ የቋንቋ ክህሎት ጋር የተያያዘው የመተዳደርያ ደንብን መቃወማቸው ትዝብት ውስጥ የሚከት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ስፖርቱ በምን ዓይነት ሙያተኞች እንደሚመራ የሚያመላክት ስለመሆኑ ጭምር ደግመው የሚገልጹ አሉ፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደሚሉት ከሆነ፣ አሁን ላይ ከዚህ ቅድመ ሁኔታ ጋር የተነሳው ውዝግብ መጀመሪያውኑ በቢሾፍቱው መድረክ መቅረብ ሲገባው፣ ደንቡ በከፊል ሳይሆን በሙሉ ድምፅ ከፀደቀ በኋላ ጉዳዩ እንደገና መነሳቱ ዘርፉ እየተመራ ያለው ለግል ጥቅም እንጂ ለስፖርቱና ለአገር ጥቅም ቅድሚያ በሚያሳቡ ግለሰቦች እንዳልሆነ ጭምር ማሳያ ነው ሲሉ ትዝብታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስቸኳይ ጉባዔ ከዚህ ቀደም ለአይኦሲ ተልኮ ይሁንታ ያገኘውን መተዳደርያ ደንብ ተቀብሎ ማፅደቁ፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ጉባዔው በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ተዘጋጅቶ የቀረበለትን የምርጫ ማስፈጸሚያ መመርያ ላይም ከተወያየ በኋላ ሦስት የምርጫ አስፈጻሚ አባላትን መሰየሙ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በመመርያው መሠረት ለፕሬዚዳንታዊና ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ምርጫ መቅረብ የሚፈልግ ሰው በትምህርት ዝግጅቱ ቢያንስ የመጀመርያ ዲግሪ ሆኖ በተጨማሪም አንድ ዓለም አቀፍ ቋንቋ መቻል እንደሚኖርበት፣ ይህ መሥፈርት ኦሊምፒያን የሆኑ አትሌቶችን እንደማይመለከት፣ አንድ ወንድና አንድ ሴት አትሌቶች በሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ውስጥ የሚካተቱ እንደሚሆንም በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል፡፡

የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ ሰኞ መጋቢት 6 ቀን በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሠራጨው መረጃ፣ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አመራር ቦርድ ከ15 የኦሊምፒክ ስፖርቶች 12 ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለዘጠኝ ቦታ ሲቀርቡ፣ የኦሊምፒክ ስፖርት ካልሆኑ 13 አሶሴሽኖች ደግሞ ለአንድ ቦታ ስድስት ዕጩ ተወዳዳሪዎች መቅረባቸውን አስታውቋል፡፡ ለምዝገባ የተቀመጠው ቀነ ገደብም በዕለቱ መጠናቀቁ ተናግሯል፡፡

በቀነ ገደቡ መሠረት ዕጩ ተወዳዳሪዎቻቸውን ያላስመዘገቡ አንዳንድ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴው ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በሚመለከት በአባላቱ የፀደቀው የምርጫ ማስፈጸሚያ መመርያ ተግባራዊ እንዳይደረግ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ጉዳይ ቀደም ሲል ሲል ከቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ዝግጅት ጋር ተያይዞ አለመግባባት ላይ እንደነበሩ ሲነገርላቸው ለቆዩት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል ልዩነቱ የበለጠ እንዲሰፋ ምክንያት ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡

ስፖርቱን በበላይነት የሚያስተዳድረው መንግሥታዊው ተቋም ስፖርት ኮሚሽን ከዚህ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫና የምርጫ ማስፈጻሚያ መመርያ ጋር ተያይዞ ማክሰኞ መጋቢት 7 ቀን ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን ሰብስቦ ማወያየቱ ተሰምቷል፡፡ በኅትመት ምክንያት የውይይቱን ዝርዝር ጉዳይ ለማካተት አልተቻለም፡፡        

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መተዳደርያ ደንብ አንቀጽ 18፣ ንዑስ አንቀጽ አራት እንዲሁም አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ አንድ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ አዲስ ምርጫ ማካሄድ እንዳለበት ቢደነግግም፣ የአገልግሎት ጊዜውን ያጠናቀቀው የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አመራር፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እስከ ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ማግስት ድረስ እንዲቆይ ከወራት በፊት በሐዋሳ ከተማ በተካሄደው የኦሊምፒክ ኮሚቴው 45ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል በመጪው ክረምት በጃፓን ቶኪዮ ለሚካሄደው ኦሊምፒክ በዝግጅት ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሕክምናው ዘርፍ እየሠሩ የሚገኙ ዶክተሮች ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቅሬታ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡

ሐኪሞቹ ሕይወት ዘላለም (ዶ/ር) እና ቃልኪዳን ዘገየ (ዶ/ር) መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያስገቡት የቅሬታ ደብዳቤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

‹‹ከፊታችን ለሚካሄደው የቶኪዮ 2020 ጨዋታ በሕክምና አገልግሎት ከተመደብንበት ቀን ጀምሮ ለተመረጡ አትሌቶችና አሠልጣኞች የሕክምና ድጋፍ እየሰጠን እንዳለ ይታወቃል፡፡ የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲያደርጉ ማመቻቸት እንዲሁም ውጤት ሰብስቦ ነፃ የሆኑ አትሌቶችን ሁለት ሆቴል ከማስገባት ጀምሮ የሆቴል ቅኝት፣ የመድኃኒት ግዥ በመፈጸም ብሎም ቡድኑ ሆቴል ከገባ በኋላ በሁለቱም ሆቴሎች እያደሩ ተገቢውን የሕክምና ዕርዳታና ክትትል በማድረግ በየልምምድ ቦታው በመገኘት አትሌቶችን በመቃኘት፣ የተለያዩ ምርመራዎችና ሕክምናዎች ሲያስፈልጉ በምንሠራበት የመንግሥትና የግል ተቋማት በመውሰድ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ በሥነ ምግብ ጉዳዮች ላይም ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር በመመካከር፣ ቡድኑ የተሻለ አገልግሎት የሚያገኝበት ነገር እየሠራን እንገኛለን፡፡

‹‹ይሁንና ሕክምናን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የተሞከረ ቢሆንም ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ቦታው ላይ ክፍተት እንዳይኖር በተቻለን መጠን ከኦሊምፒክ ኮሚቴው በሚደረግልን ድጋፍ እየሠራን እንገኛለን፡፡

‹‹ሆኖም በተለያየ ጊዜ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፣ ሴት ባለሙያ እንዲሁም የተሻልን በመሆናችንና ይህን ሁሉ የአገር ኃላፊነት ተቀብለን እየሠራን መሆኑን በመገንዘብ እንደማበረታታት፣ የሙያ ሥነ ምግባር በማይፈቅደው መልኩ ነቀፌታና ሞራልን ዝቅ የሚያደርግ ቃላትና አስተያየቶችን በመሰንዘር ሞራል የሚነካ ድርጊት ተፈጽሞብናል፡፡

‹‹ስለሆነም እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች የሥራ ተነሳሽነትን ብሎም ክፍተት የሚታይበትን የስፖርት ሕክምና አሰጣጥ ሥርዓት ስለሚያፋልስ ድርጊቱ ለምን እንደተፈጸመ ማብራርያ እንዲሰጠን እንዲሁም ከዚህ በኋላ በሥራችን ጣልቃ እንዳይገባብን የሕክምና ክትትል ከምናደርግባቸው አትሌቶችና አሠልጣኞች ፊት ስለሆነ ድርጊቱ የተፈጸመው፣ በእነዚሁ ሙያተኞችና አትሌቶች ፊት ይቅርታ ሊጠይቁን እንደሚገባ አበክረን እንጠይቃለን፡፡          

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...