አዲስ አበባ ሰንጋ ተራ አካባቢ የኢትዮጵያ የፋይናንስ መንደር እንዲሆን ታስቦ የፋይናንስ ተቋማትም ዋና መሥሪያ ቤታቸው በዚያው አካባቢ መገንባት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
አዋሽ ባንክና ዳሸን ባንክ በሥፍራው በገነቡት ዋና መሥሪያ ቤት ሥራ ጀምረዋል፡፡ ኅብረት፣ ዘመንና ንብ ባንኮችና ናይል ኢንሹራንስ ደግሞ የሕንፃ ግንባታቸውን እያጠናቀቁ ይገኛሉ፡፡ ሌሎችም የፋይናንስ ተቋማት በዚሁ አካባቢ በተረከቧቸው ቦታዎች የሕንፃ ግንባታዎቻቸውን እንደሚያካሂዱ ይጠበቃል፡፡
በሰንጋ ተራ በተረከቡት ቦታ የዋና መሥሪያ ቤታቸውን ሕንፃ ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረጉ ካሉት ባንኮች መካከል አንዱ እናት ባንክም ለባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የአርክቴክቸራል ዲዛይን እንዲሠራለት ባወጣው ጨረታ መሠረት አሸናፊ ኩባንያዎችን በመለየት ሸልሟል፡፡
ባንኩ ለዋናው መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ሦስት ዲዛይኖችን በመምረጥና ደረጃ በመስጠት የተረከበ ሲሆን፣ ለእነዚህ ከአንድ እስከ ሦስት ለወጡ አሸናፊዎች ቅዳሜ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ሽልማት ሰጥቷል፡፡ በዕለቱ እንደተገለጸው፣ ባንኩ የራሱ ሕንፃ ባለቤት የሚሆንበት ተግባራዊ ሥራ በቅርቡ ይጀመራል፡፡
ከሦስቱ የተመረጡ ዲዛይኖች መካከልም አንዱን በሚቀጥለው ሳምንት በመምረጥ በአሸናፊው ዲዛይን መሠረት ሕንፃውን በመገንባት የፋይናንስ ተቋማት መንደሩን ይቀላቀላል ተብሎ እየተጠበቀም ነው፡፡ ባንኩ ባካሄደው ጨረታ ከአንድ እስከ ሦስት ደረጃ ያገኙትን ዲዛይኖች የሠሩት ኤችኤም ኮንሰልታንሲ፣ ኢዮብ ክንፈ አርክቴክቸርና ሲግኒቸር የተባሉ ድርጅቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ካቀረቧቸው ዲዛይኖች አንደኛ ደረጃ የተሰጠው በኤችኤም ኮንሰልታንሲ የተሠራው ዲዛይን ነው፡፡
የእናት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ዲዛይን ለመሥራት 13 ድርጅቶች ተወዳዳሪ የነበሩ ሲሆን፣ መጨረሻ ላይ ገለልተኛ ዳኞች የመረጧቸው ሦስቱ ድርጅቶች ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በማግኘት ለሽልማት በቅተዋል፡፡
ከባንኩ ባገኘነው መረጃ መሠረት ግን በሚቀጥለው ሳምንት ኩባንያዎቹ ያቀረቡት የጨረታ መወዳደሪያ ዋጋ ከቀረበ በኋላ የመጨረሻው አሽናፊ የሚለይ መሆኑን ነው፡፡ ባንኩ ለሠንጋ ተራ አካባቢ ለዚህ ሕንፃ ግንባታ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ያገኘው ቦታ 4,375 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ነው፡፡
እናት ባንክ በአሥራ አንድ ባለራዕይ ሴቶች ሐሳብ አፍላቂነት የተጠነሰሰ ሲሆን፣ ምሥረታው ተካሄዶ ወደ ሥራ ከገባ ስምንተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ማኅበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ኢፍትሐዊነት በዘላቂነት ለመፍታት ከሚያስችለው አንዱና ዋነኛው በአካታች የፋይናንስ ሥርዓት ሴቶችን በፋይናንስ አቅም ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ በሚል ፅኑ`ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ባንክ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ ሃና፣ አሁን ደግሞ የራሱን ሕንፃ ወደ ማስገንባት ሊገባ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እናት ባንክ ሴቶችን ማዕከል አድርጎ በኢትዮጵያ በብቸኝነት የተቋቋመ ባንክ ሲሆን፣ ይህንን ፈር በመከተል ብዙዎቹ ባንኮች ለሴቶች የተለየ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
በቅዳሜው የሽልማት ፕሮግራም ላይ ባንኩን ከማደራጀት ጀምሮ ከመጀመርያዎቹ አሥራ አንድ አደራጆች መካከል አንዷ የሆኑና የመጀመርያው የባንክ የቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ያገለገሉት፣ አሁን ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በክብር እንግድነት የተገኙበት ነበር፡፡
በዕለቱ እንደተጠቀሰው፣ በአሁኑ ወቅት እናት ባንክ በተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 9.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የብድር ክምችቱም ስምንት ቢሊዮን ብር እንዲሁም የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 1.52 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከባንኩ ጠቅላላ ባለአክሲዮኖች ውስጥ 64 በመቶ፣ ከጠቅላላ አስቀማጭ 59 በመቶ እንዲሁም ከጠቅላላ ሠራተኛ 60 በመቶ ሴቶች መሆናቸውም ታውቋል፡፡