Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዘይት እጥረትና ዋጋ መወደድ የምርት እጥረት ወይስ የአከፋፋዮች ሻጥር?

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከሚወጣባቸውና መሠረታዊ ከሚባሉ ምርቶች መካከል የምግብ ዘይት አንዱ ነው፡፡ በዓመት ከ620 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማለትም ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበትም ነው፡፡

በቅርቡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በየወሩ 52 ሚሊዮን ዶላር ለምግብ ዘይት ፍጆታዋ ወጪ ታደርጋለች፡፡ በዚህ መረጃ ሥሌት መሠረት በየወሩ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው የምግብ ዘይት ለገበያ የሚቀርብ ሲሆን፣ በግብይት ውስጥ ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው መሠረታዊ የሆኑ ፍጆታ ምርቶች አንዱ ያደርገዋል፡፡ ከፍተኛ ወጪ የሚደረግበት የምግብ ዘይት ግን በገበያ ውስጥ በተደጋጋሚ እጥረት ያለበትና ሸማቹ እጅ እንደተፈለገ የማይገባ ነው፡፡  

ይህንን የዘይት ምርት ከውጭ ከማስገባት ይልቅ ቢያንስ በአገር ውስጥ አጣርቶና አሽጎ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ ብዙም ተነሳሽነት ስላልነበር ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለምግብ ዘይት እጅግ ከፍተኛ ወጪ እንድታወጣ አስገድዷል፡፡ ለዓመታት የዘለቀውን የምግብ ዘይት የአቅርቦት ችግር ለመፍታት ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ የምግብ ዘይት በማምረት ቀድመው መንቀሳቀስ ከጀመሩት አገር በቀል ኩባንያዎች መካከል ሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ይጠቀሳል፡፡

ሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ይህንን ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ ዘይት ማምረት እስኪጀምር ድረስ፣ ድፍድፍ የፓልም ዘይት በማምጣት አጣርቶና አሽጎ ወደ ገበያ ማቅረብ የጀመረው ከታኅሳስ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡

የዘይት እጥረትና ዋጋ መወደድ የምርት እጥረት ወይስ የአከፋፋዮች ሻጥር?

በ2010 ዓ.ም. ሥራውን ሲጀምር በቀን 130 ቶን ዘይት በማምረት ቀጥሎም ወደ 230 ቶን ምርቱን በማሳደግ፣ አሁን ላይ ደግሞ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ የማስፋፊያ ግንባታ በማካሄድ በቀን 950 ቶን ድፍድፍ የፓልም ዘይት የማራጣት ደረጃ ላይ በመድረስ ወደ ማምረት ገብቷል፡፡ ለዚህም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ የሥራ ማስኬጃ ወጪ አድርጓል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ የተገነባው ይህ የዘይት ማምረቻ በዋናነት ዓላማው በተመጣጠነ ዋጋ ምርቱን ሸማቾች ጋር ማድረስና ምርቱን በማሳደግና በአገር ውስጥ የጥሬ ዕቃ ጭምር በመጠቀም ሥራውን ማስፋት ነው፡፡

ፋብሪካው አሁን የሚያመርተው ምርት ገበያውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያረጋጋ ስለመሆኑ የሚጠቅሱት የሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች፣ ዘይት በተመጣጠነ ዋጋ ኅብረተሰቡ ዘንድ ለማድረስ ድርጅታቸው እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሸሙ የዘይት ምርቱን በተለያየ መጠን በማሸግ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ለዘይት ማሸጊያ የሚሆኑ ምርቶቹንና ሌሎች ግብዓቶቹንም እዚያው ያመርታል፡፡

የሸሙ ማኔጅመንት ኮንሰልታንት ግሩፕ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍሬዘር ደበላ  ‹‹ፋብሪካችን ከውጭ የሚገባውን የፓልም ዘይት በአገር ውስጥ ለመተካት ከተቋቋሙትና አሁን ላይ እየሠሩ ከሚገኙ ፋብሪካዎች አንዱ ነው፡፡ አሁን ባለው የአገሪቱ የምግብ ዘይት ፍጆታ አንፃር ሸሙ 32 በመቶውን ማምረት የሚችል አቅም አለው›› ብለዋል፡፡

ገበያን ከማረጋጋት አንፃር እኛ ወደዚህ የማምረት ሒደት ስንገባ መንግሥትም የያዘው አቅጣጫ ነበር ያሉት አቶ ፍሬዘር፣ ከውጭ የሚገባውን የፓልም ዘይት በአገር ውስጥ ለማምረት በተሰጠውን የውጭ ምንዛሪ ድጋፍ መሠረት ወደ ሦስት ሚሊዮን ሌትር ዘይት አምርተው አፋፋዮችን በመጠበቅ ላይ እንደሆኑ ገልጽዋል፡፡

ዘይት ማምረቻውን ጨምሮ ስድስት ፋብሪካዎችን በአንድነት የያዘው የሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋ ሚካኤል ግኡሽ በበኩላቸው፣ በድሬዳዋ የሸሙ ግሩፕ መንደር ውስጥ ያሉት ስድስቱም ፋብሪካዎች መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን የሚያመርቱ በመሆናቸው ዘይትን ጨምሮ ሌሎች ምርቶቹን በተመጣጠነ ዋጋ እያቀረበ ይገኛል፡፡

ስድስቱ ማምረቻዎች ደረቅ ሳሙና፣ ፈሳሽ ሳሙና፣ የምግብ ዘይት፣ የሳሙና ጥሬ ዕቃ፣ ማርጋሪንና የመሳሰሉት ምርቶች የሚመረቱባቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጭንቅ ውስጥ የከተታት መሠረታዊ የሆኑ ምርቶ መወደድ በመሆኑ ይህንን ለማረጋጋት 24 ሰዓት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች አሉን ያሉት አቶ ተስፋ ሚካኤል፣ በተለይም ዘይት ትኩረት ተሰጥቶት መንግሥት ገበያ እንዲያረጋጉ ኃላፊነት ስለሰጣቸው በሊትር ከ40 እስከ 42 ብር ሊሸጥ የሚችል የፓልም ዘይት አምርተው እያቀረቡ መሆኑን አክለዋል፡፡

 ፋብሪካው በዚህን ያህል ደረጃ በማምረት ላይ ሲሆን፣ በተመጣጠነ ዋጋ ኅብረተሰቡ ዘንድ ለማድረስ ግን አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች መሠራት አለበት ይላሉ፡፡ በመሀል የሚገቡ የትራንስፖርት የሥርጭት ችግሮች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ተስፋ ሚካኤል፣ ይህንን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማኔጅ የሚያደርጋቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ፋብሪካቸው ግን በማምረቱ ረገድ 24 ሰዓት ዝግጁ መሆኑንና አሁን ላይ በመንግሥት ትዕዛዝ የተመረተ ከሦስት ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት እጃቸው ላይ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ በማምረት አቅማቸው ልክ እያመረቱ ሲሆን፣ እንደውም ሥጋት ያለው የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት ያጋጥም ይሆን ወይ የሚለው መሆኑንና ለዚህም የመንግሥት ድጋፍ ሊለያቸው እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገር ደረጃ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ለመታደግ ኩባንያው የሚያመርታቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ባሻገር በቅርቡም ዋጋ ለማረጋጋት ያግዛል ያለውን አንድ ትልቅ ፕሮጀክት በመንደፍ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ ናቸው፡፡  

ፕሮጀክቱ አስቤዛ ኢትዮጵያ ሪቴሊንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በኩል የሚተገበር ሲሆን፣ በአገሪቱ መካከለኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች አስቤዛን የማቅረብ ሥራ ያከናውናል፡፡ በኦላይን በመታገዝ ምርቶችን የሚያቀርብ በመሆኑ በገበያ ውስጥ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ሥራ ያከናውናል ብለዋል፡፡  

ሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ተያያዥ የሆኑ ምርቶችን በአንድ ቦታ ላይ በማመጋገብ የሚሠራው ሥራ ኩባንያው በዋናነት የያዘውን ምርቱን በተመጣጠነ ዋጋ የማቅረብ ዕድል እንደሰጠው የሚናገሩት የሥራ ኃላፊዎቹ ይናራሉ፡፡

ኩባንያው በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ የተለያዩ ማምረቻዎችን በመጠቀም ሳሙና ማሸጊያ፣ ሌብሊንግ፣ የዘይት ማሸጊያ፣ የፈሳሽ ሳሙና መያዣ እዚያው ያመርታል፡፡ ዋና ዋና የምርት ግብዓቶቹ እዚያው መመረት መቻላቸው የተሻለ በሚባል ዋጋ ምርቱን ለማቅረብ ይረዳል ተብሏል፡፡

ከዚህ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው ከዘይት ማምረቻው የሚያገኘውን ተረፈ ምርት ኩባንያው የሚታወቅበትን የደረቅና ፈሳሽ ሳሙና ለማምረት ያስቻለው ሲሆን፣ ከውጭ ያስመጣ የነበረውንም ጥሬ ዕቃ አስቀርቶለታል፡፡  

ለሳሙና ዋነኛ የሆነውን ጥሬ ዕቃ እዚያው ማምረት መጀመሩ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሳሙና አምራቾች ለማቅረብ አስችሎታል፡፡  

የሸሙ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ወጋየሁ ንጋቱ እንደገለጹትም፣ እንደ ዋነኛ ጥሬ ዕቃውን እዚህ ማምረት በመቻሉ በውጭ ምንዛሪ ይገባ የነበረውን ምርት ማስቀረት አስችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወደ 150 የሳሙና ማምረቻዎች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ወጋየሁ፣ አብዛኞቹ ሳሙና ማምረቻዎችም ይህንኑ የጥሬ ዕቃ ከእነርሱ የሚገዙ በመሆኑ የዚህ ምርት መጀመር አጠቃላይ ኢንዱስትሪውን እየጠቀመ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

በድሬዳዋ የሚገኙት ስድስቱ የተለያዩ ምርቶች ማምረቻዎች ተመጋግበው መሥራታቸው ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ከማስቻሉም በላይ ኩባንያው መሠረታዊ ፍጆታ ምርቶች ላይ አተኩሮ የሚሠራ በመሆኑ ሸማቾች የገበያ አማራጭ እንዲኖራቸው ያስቻለ አሠራርም ይከተላል፡፡

ለዚህ እንደ ማሳያ የሚጠቀሰው፣ ፈሳሽ ሳሙና የምርት ደረጃው ሳይለወጥ  በአንድ ሌትር የፕላስቲክ እሽግ በጠንካራ ፕላስቲክ እሽግ ሲቀርብ በማሸጊያዎቹ ልዩነት ብቻ በአንድ ሌትር ፈሳሽ ሳሙና እስከ አሥር ብር የዋጋ ልዩነት ይኖረዋል፡፡ ይህም ኅብረተሰቡ ተመሳሳይ የሆነን ምርት ማሸጊያው ቢለያይም በአቅሙ እንዲገዛ ማስቻሉ ነው፡፡

እንደ ኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ የዘይቱንም ሆነ ሌሎች ምርቶችን ከዚህም በላይ ማምረት ቢችልም ኩባንያው አሁን ያለውን አቅሙን በአግባቡ ለመጠቀምና ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራዎችን ለመሥራት የቦታ ጥበት አለበት፡፡  

ኩባንያው ተመጋጋቢ የማረቻዎች አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ላቀረበው የቦታ ጥያቄ እስካሁን አዎንታዊ መልስ ባለማግኘቱ የበለጠ መሥራት እንዳላስቻለው ተገልጿል፡፡ የሚፈልገውን ቦታ ለማግኘት ቃል የተገባለት ቢሆንም ተፈጻሚ አልሆነም፡፡

በተለይ የዘይት ፋብሪካው በዚህ የቦታ መጠን ላይ ተገድቦ መቅረት አልነበረበትም ያሉት አቶ ተስፋሚካኤል ተጨማሪ ማስፋፊያ ለማካሄድ 22 ሔክታር መሬት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ይህ ከተሟላ አሁንም ከዚህ የበለጠ እንደሚሠሩና የተገባላቸው ቃል እንዲተገበርም ጠይቀዋል፡፡

የማመረቻ ምርቱን የሥራ ሒደት በተመለከተ በተደረገው የመስክ ምልከታ ላይ እንደተገለጸው፣ ሸሙ በተለይ በዘይት ማምረት ሥራ ላይ ትልቁ ህልሙ የፓልም ዘይትን አጣርቶ ማቅረብ ሳይሆን፣ ይህን ለተወሰነ ጊዜ ሠርቶበት ዋና ግቡ የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃን ተጠቅሞ ዘይት ማምረት ነው፡፡ እንደ ለውዝና ሌሎች የቅባት እህሎችን ተጠቅሞ ጥራት ያለው ምርት በማምረት በዘርፉ የተሻለ ውጤት የማምጣት ዓላማ አለው፡፡ ለዚህም የተለያዩ ቅድመ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከሁሉም አቅጣጫ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የዘይት ማምረቻው ከፀሐይ የሚፈልገውን ኃይል እንዲያገኝ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡

በተለይ የዘይት ገበያን ከማረጋጋት አንፃር የጀመረውን ሥራ ከግብ ለማድረስ ያለማቋረጥ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ ለጥሬ ዕቃ አቅርቦት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ግድ ስለመሆኑም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

አሁን እየተሠራ ባለው ሥራ በርካታ ሊትር ዘይት ማምረት ከተቻለ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ ስለሚቻል መንግሥት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቱን እየተከታተለ ማቅረብ ቢያቀርብ አሁን የሚታየውን የዘይት እጥረትና ገበያ ማስተካከል እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡

ሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እ.ኤ.አ. ከ1993 ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ እንቅስቃሴ የጀመረ ድርጅት ነው፡፡ በተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ላይ ተሰማርቶ ከ30 ዓመታት በላይ የቆየ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የፓልም ዘይትን አጣርቶ በመሸጥ በኩል ፈር ቀዳጅ ድርጅት ነው፡፡ እንደ ሸሙ ኮርፖሬት፣  አዲስ ኩባንያ እየተቋቋመ ነው፡፡ 15 ኩባንያዎች ሥራ ላይ ያሉ ሲሆን፣ በቅርቡ ከፕሮጀክት አልፈው ወደ ሥራ የሚገቡ ተጨማሪ አምስት ፋብሪካዎች ግሩፑን ይቀላቀላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች